1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መቅዲሹ፤ በቦምብ ፍንዳታ የተገደሉት ቁጥር 300 ገደማ ደረሰ

ሰኞ፣ ጥቅምት 6 2010

ቅዳሜ ዕለት በሶማሊያ ዋና ከተማ መቃዲሹ በቦምብ ፍንዳታ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነዉ። ዘገባዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ276 ከፍ ሊል እንደሚችል ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/2lrWH
Somalia Mehr als 260 Tote nach Doppel-Anschlag in Mogadischu
ምስል Reuters/F. Omar

 ሶማሊያ ካጋጠሟት ጥቃቶች ከፍተኛ ነዉ በተባለዉ የቅዳሜዉ የቦምብ ፍንዳታ ሕይወታቸዉን ያጡ ሰዎች ቀብር እየተፈጸመ ባለበት በዚህ ዕለት ነዉ የሟቾቹ ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል መንግሥት ያመለከተዉ። ወዳጅ ዘመዶቻቸዉን ያጡ ሶማሊያዉያን ጭንቀትም ከፍ ብሏል። መቃዲሹ ዉስጥ ሀኪም ቤቶች ማንነታቸዉን መለየት እስኪያዳግት ድረስ መጎዳታቸዉ በተገለጸዉ ቁስለኞች ተጨናንቀዋል። በጥቃቱ 300 የሚሆኑ ሰዎች የተጎዱ ሲሆን፤ ከ70 የሚበልጡት ጉዳታቸዉ አስጊ እንደሆነ እና በዛሬዉ ዕለት ወደ ቱርክ ለህክምና መላካቸዉ ተገልጿል። የሶማሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር መሀዲ አህመድ ጉለይድ ቱርክ ተመሳሳይ ትብብር ለሀገራቸዉ ስታደርግ የመጀመሪያዋ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
«የቱርክ ወንድሞቻችን  አዉሮፕላን በመላክ የቆሰሉ ሶማሌያዉያን ወደቱርክ ሄደዉ የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በቅድሚያ የቆሰሉት 70 ሰዎች ወደቱርክ ከተጓጓዙ በኋላ አዉሮፕላኑ በድጋሚ ተጨማሪ ተጎጂዎችን ለመዉሰድ ይመለሳል። በዚህ አዉሮፕላን የህክምና ቁሳቁስም አቅርቦትም ጭኖ የላከልን የቱርክ መንግሥትን እናመሰግናለን።»
የተጎዱትን የማጓጓዙን ሥራ ለማስተባበርም የቱርክ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አህመድ ደሚርካንም ወደሶማሊያ መጓዛቸዉን የቱርክ መንግሥታዊ የዜና ወኪል አመልክቷል። የቱርክ ቀይ ጨረቃ በጎ ፈቃደኞች እና የህክምና ባለሙያዎችም አብረዉ ተጉዘዋል። መንግሥት ለጥቃቱ አሸባብን ተጠያቂ ቢያደርግም እስካሁን ከቡድኑ የተሰማ ነገር የለም። 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ