ሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሶማሌ ክልል
ዓርብ፣ ነሐሴ 19 2009ከሰሞኑም አንድ የክልሉ የስራ ሀላፊ ከ500 ሽህ በላይ የአሜሪካን ዶላር ይዘዉ ከጅጅጋ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ በቁጥጥር ስር መዋላቸዉንም አመልክተዋል።
የፖሊስ መኮንን ሆነዉ ለ10 አመታት ያገለገሉትና በአሁኑ ጊዜ በስደት የሚኖሩት ሻለቃ ዓሊ ሰሚራ ዚጋድ እንደገለፁት በሶማሌ ክልል ለህዝብ ልማት መዋል ይገባዉ የነበረ በርካታ ገንዘብ በክልሉ ባለስልጣናት ይመዘበራል ። በክልሉ ባለስልጣናት ወደ መሀል አገርና ወደ ጎረቤት ሀገር ዶላር ማዘዋወርም የተለመደ ስራ ነዉ ሲሉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
የሶማሌ ህብረተሰብ የኢኮኖሚና የማህበረሰብ ልማት ማህበር በመባል የሚታወቀዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የቦርድ አባል የሆኑ ግለሰብ ከትናንትና ወዲያ ከ500 ሽህ በላይ የአሜሪካን ዶላርና በሺወች የሚቆጠር የኢትዮጵያ ብር ይዘዉ ከጅጅጋ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ ቦርደዴ ከተማ ላይ በፖሊስ መያዛቸዉ በክልሉ ለሚፈፀመዉ ሙስና ማሳያ ነዉ ብለዋል።
አቶ አበኔ አረብ ኑር የተባሉት እኝህ ግለሰብ ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር ቅርበት ያላቸዉ ናቸዉ ተብሏል።ከዚህ የተነሳ ገንዘቡ ምናልባትም ለስብሰባ አዲስ አበባ ለሚገኙት ለክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ለማቀበል ሳይሆን አይቀርም ሲሉ የፖሊስ መኮንኑ አስረተድዋል።
እንደ ሻለቃ አሊ ገለፃ በክልሉ ከሚፈጸመዉ ሙስና በተጨማሪ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ በክልሉ የወንጀል ምርምራ ሀላፊ ሆነዉ በሰሩበት ወቅት ለማረጋገጥ ችያለሁ ይላሉ።።ይህንን በመቃወምም ካለፈዉ አመት ጀምሮ ሀገራቸዉን ትተዉ በስደት እንደሚገኙ አብራርተዋል።ክልሉ በአንድ ግለሰብ የበላይነት ወድቋልም ይላሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት በሌሎች የመንግስትና የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች የጀመረዉን የሙስና ዘመቻ በክልሉ ተግባራዊ ማድረግ አለበት ሲሉም መኮንኑ አሳስበዋል።
በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት የሶማሌ ክልልና የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሀላፊወችን ለማነጋገር በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም።
ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ