1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙስና በኢትዮጵያ መብትን መገዳደሩ ተገለጠ

ዓርብ፣ ኅዳር 9 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ ጎሰኝነትን፣ ሃይማኖትንና ትውውቅን መሰረት አድርጎ የሚፈፀም ሙስና መንሰራፋት፦ መብት በገንዘብ የሚገዛበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረጉን አንድ የሲቪክ ድርጅት ተናገረ። 7 አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙን ትናንት የገለፀው መንግሥት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ «ሙስና የሀገር የደኅንነት ሥጋት ሆኗል» ብሏል።

https://p.dw.com/p/4Jkgv
Symbolbild | Justiz
ምስል fikmik/YAY Images/IMAGO

ኢትዮጵያ ውስጥ ጎሰኝነትን፣ ሃይማኖትን እና ትውውቅን መሰረት አድርጎ የሚፈፀም ሙስና መንሰራፋት፦ መብት በገንዘብ የሚገዛበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረጉን በዘርፉ ላይ የሚሠራ የሲቪክ ድርጅት ተናገረ። 7 አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙን ትናንት የገለፀው መንግሥት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ «ሙስና የሀገር የደኅንነት ሥጋት ሆኗል» ብሏል። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው በሙስና ላይ የሚሠራው ዓለም አቀፍ ተቋም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ሙስናን በተመለከተ የአመለካከት መሻሻል አድርጋለች ይላል። ይህ መሬት ላይ የተስፋፋውን የሙስና ወንጀል በትክክል እንደማይገልጽ ግን ያነጋገርናቸው ድርጊቱን በመከላከል ላይ የሚሠራ ድርጅት የሥራ ኃላፊ ገልፀዋል።

ሙስና በኢትዮጵያ

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ፣ ድምፃቸውንም እንዳንጠቀም የጠየቁን ሰው «የጎሳ እና ሃይማኖት መዛመድን መነሻ ያደረገ ጥልፍልፍ የሙስና ወንጀል ከሚገመተው በላይ ተንሰራፍቷል» ይላሉ። ይህም «አንድም ሀቀኛ ሠራተኞችን በሌላ በኩል ለሙስናው ድርጊት ሰዎችን ካሰባሰበው ማንነት ውጪ የሆኑትን ለማጥቃት እና ለሥራ መበደል ምክንያት ሆኗል» ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ሀብት እና ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡ በ2002 ዓ.ም ሕግ ቢወጣም የሙስና ወንጀል ተባብሶ መቀጠሉን ብዙ ሰዎች በምሬት በየእለቱ ይናገራሉ። ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የተባለውና ሙስናን በመከላከል ላይ የሚሠራው ተቋም ዋና ዳሬክተር አቶ ሳሙኤል ካሳሁን ይህንኑ ያረጋግጣሉ። «ሙስና ከእለት እለት እየጨመረ እየባሰ ያለበት ሁኔታ ነው የሚታየው። በሃይማኖትና በሌሎች መነሻ ሙስና መፈፀም፣ በልጣን መባለግ ከእለት እለት እየገዘፈ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው። አገልግሎት አሰጣጡ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየዘቀጠ ይገኛል» ብለዋል። አንዳንድ ተመልካቾችና ታዛቢዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ሕግጋትን፣ መመሪያና ደንቦችን በመጠቀም ጭምር የሀገርና የሕዝብ ሀብት በገፍ ይመዘበር ነበር፣ አሁንም ይመዘበራል።

Hände übergeben Euros
ወደ ኋላ ተገልብጦ የተዘረጋ እጅ ዩሮ ገንዘቦችን ሲቀበል የሚያሳይ የሙስና ተግባርምስል picture-alliance/U.Baumgarten

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት 7 አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን በሚገልፀው መግለጫ ላይ ይህ ችግር መኖሩን የሚያመለክት ሀሳብ ጠቅሰዋል። «በአንድ በኩል የመንግሥት ሕግጋት፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሠራሮች ለሙስና ያላቸውን ተጋላጭነት የማጥፋት ሥራ ይሠራል» በማለት። አቶ ሳሙኤል በዚህ አይስማሙም። «ከሙስና ጋር ተያይዘው ጠንከር ጠንከር ያሉ ሕግ የሚመስሉ ነገሮች አሉ። ግን አተገባበራቸው እጅግ በጣም ደካማ ነው።»

መንግሥት በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጠው አቅጣጫ የሙስና ተዋንያንን የማጋለጥና በሕግ የመጠየቅን አስፈላጊነት ነው። ሕዝብ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከመሬት ጋር በተያያዙ አሠራሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በሽያጭና ግዥ ሂደቶች፣ በፍትሕ አደባባዮች፣ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ የሕዝብ ተቋማት በሚያጋጥመው ሙስና መማረሩን መንግሥት አምኖ ተቀብሏል። የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ኢትዮጵያ ከባድ ሙሰኞችን እንደ ቻይና በስቅላት ልትቀጣ ይገባል ይላሉ የችግሩን አስከፊነት በማንሳት። «ኮሚቴ ማቋቋም ብቻ ችግሩን ይቀንሰዋል፣ ብሎም ይፈታዋል ብየ አላምንም። እነ ቻይና እንዳደረጉት አስተማሪ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል" ብለዋል። መንግሥት «የሙስና ተዋንያን ሁሉ ሙስናን እርም እንዲሉ የሚያደርግ ርምጃ ያስፈልጋል» ብሏል። ይህ አቋም እውን ተፈፃሚ ይሆን ይሆን?» ችሎታን መሰረት ያላደረገ አሠራር፣ በዘር፣ በሃይማኖት ተቧድነው አይነኬነታቸው አዳብረው ለመንግሥትም ሥጋት ሆነው ነው ይህንን የሚሠረት። ከመንግሥት ወገን ጨከን ማለት ይጠይቃል በማለት አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል።

ሰለሞን ሙጬ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ