በሃማስ የታገቱ ጥቂት እስራኤላዉያን ተለቀቁ
ዓርብ፣ ኅዳር 14 2016ለአራት ቀናት የሚቆየውንም የተኩስ አቁም ተከትሎ በእስራኤልና በሃማስ መካከል የታጋች እና እስረኛ ልዉዉጥ እየተካሄደ ነዉ። እርዳታ ወደ ጋዛ ሰርጥ መግባት መጀመሩም ተገልጿል። በስምምነቱ መሠረት ዛሬ ህጻናትን ጨምሮ 13 የእስራኤል ታጋቾች በግብፅ በኩል ለዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት መሰጠታቸዉን የእስራኤል ቴሌቭዥን ዘግባል። በግብፅ ራፋህ የድንበር በኩል የእስራኤል ወታደራዊ ኃይሎች በሄሊኮፕተር ተቀብለው አስፈላጊውን የማንነት ማረጋገጫ ያደርጋሉ፤ በመቀጠልም የሕክምና ምርመራ ከተደረገላቸዉ በኃላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደሚገኛኑ ተገልጿል። ይለቀቃሉ ከተባሉ 13 ታጋቾች በተጨማሪ ሌላ ታግተዉ የነበሩ 10 የታይላንድ ዜጎችም መለቀቃቸዉ ተመልክቷል። እስካሁን የተለቀቁት የእስራኤል ኃጋቾች ማንነት አልተገለፀም። በሚቀጥሉት ደቂቃዎc እና ሰዓታት ይፋ እንደሚነገር ይጠበቃል። እስራኤል በእስር ከያዘቻቸው በሺዎች ከሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን መካከል የተወሰኑት ዛሬ እንደሚለቀቁ ይጠበቃል። ከእስራኤል በኩል የሚለቀቁት ፍልስጤማዉያን፤ መካከል ታዳጊ ህጻናት እና ወጣቶች እንደሆኑ ተገልጿል። በእስራኤል ታስረዉ የነበሩት እነዚህ ፍልስጤማዉያን በእስራኤል ፀጥታ ሃይላት ላይ ድንጋይ በመወርወር ወይም የኃይል ጥቃት በማድረስ ተይዘዉ የነበሩ ናቸዉ፤ ተብሏል። እስራኤል እና ሃማስ የተለዋወጥዋቸዉ እስረኞችም ሆኖ ታጎቾች እስካሁን በይፋ አልወጡም የዓለም አይኖች ትኩረታቸዉን መካከለኛዉ ምስራቅ ላይ እንዳደረጉ ነዉ።
በሌላ በኩል እስራኤል እና ሐማስ መካከል የሚካሄደው ጦርነት ለቀናቶች ለማቆም እና ታጋቾችን ለመልቀቅ ከስምምነት መድረሱን ተከትሎ ወደ ጋዛ የሚገባው የሰብዓዊ እርዳታ መጠን እየጨመረ መሆኑ ተዘግቧል። ስምምነቱ ተፈጻሚ ከሆነበት ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ቢያንስ 60 የሰብዓዊ ቁሳቁስ እና ምግብ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባታቸዉ ተነግሯል። ግብጽ በበኩልዋ በየቀኑ 130 ሺህ ሊትር ነዳጅ ወደ ጋዛ እንደሚገባ አስታዉቃለች። በሚቀጥሉት አራት ቀናት ወደ ጋዛ 200 የሚጠጉ የሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንደሚገቡ ይጠበቃል። ይሁንና ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚሆነዉ እርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማዉያን በቂ መሆኑ አጠራጣሪ ተብሏል።
የእስራኤል ጦር ሰራዊት ቃል አቀባይ ፍልስጤማዉያን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ እንዳይመለሱ ሲል ጥሪ ዛሬ አደረገ። እንደ ጦር ሰራዊቱ ቃል አቀባይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለቀናቶች ተደረገ እንጂ ጦርነቱ አልቆመም፤ ወደ ሰሜናዊ ጋዛ እንዳትመለሱ ሲል ለፍልስጤማዉያን ጥሪ አቅርቧል። ይሁንና ተጨማሪ ታጋቾች የሚለቀቁ ከሆነ የተኩስ አቁም ቀናቶች ከአራት ቀናቱ ሊጨምር እንደሚችል ተመልክቷል።
አዜብ ታደሰ
ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር