በሶማሌ ክልል ድርቅ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለከፋ ችግር አጋልጧል ተባለ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 25 2013በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ከ2.1 ሚልየን የሚልቅ ህዝብ ለከፋ ችግር መጋለጡን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ በተከሰተው ድርቅ እንስሳት እየሞቱ መሆናቸውም ተገልጿል።
የሶማሌ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዱልፈታህ ሼክ ቢሂ ለዶይቼ ቬለ በስልክ በሰጡት መረጃ በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ከ2.1 ሚልየን የሚበልጥ ህዝብ ለችግር ተጋልጧል ብለዋል።
ኃላፊው ደረጃው ቢለያይም በክልሉ ባሉ አስራ አንድ ዞኖች ድርቁ መከሰቱን ገልፀው ሁኔታው አሁን ካለበት በላይ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ጠቋሚ መረጃዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች አንዱ በሆነው የሲቲ ዞን የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ተጠሪ አቶ ኤልያስ አደም በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ድርቁ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉን እና እንስሳት በተለይ ፍየሎች እየሞቱ መሆናቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዱልፈታህ የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመቋቋም ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ለተለያዩ አካላት ጥሪ ማቅረባቸውን ጠቁመው በቀጣይ ችግሩ ከከፋ በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ዕቅዶች የተያዘ በጀት ጭምር ወደ ድርቅ መከላከል ሊዞር እንደሚችል ክልሉ መወሰኑን አስረድተዋል።
በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ላጋጠመው የውሀ እና የእንስሳት መኖ ችግር ለመቅረፍ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የሚፈለገውን ያክል አለመሆናቸው ተገልጿል።
መሳይ ተክሉ
ታምራት ዲንሳ