ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወደ 2000 ገደማ ሰዎች በአዲስ አበባ ይገኛሉ
እሑድ፣ ኅዳር 24 2010በኦሮሞ-ሶማሌ ክልሎች የድንበር ግጭት ከጅጅጋ እና አካባቢዋ ተፈናቅለው በአንድ የግል ኮሌጅ ውስጥ የተጠለሉ ወደ 2000 ገደማ ሰዎች የአዲስ አበባ አስተዳደር ቋሚ ማረፊያ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ተፈናቃዮቹ በአዲስ አበባ ከተማ ጎተራ አካባቢ በሚገኘው የሪፍት ቫሊ ኮሌጅ ተጠልለዋል። ኮሌጁ ቅጥር ግቢውን ከመስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለተፈናቃዮቹ መጠለያ በማድረጉ ምክንያት ማስተማር አልጀመረም።
"ጅጅጋ እና ከዛው አካባቢ ግጭቱ እንደተፈጠረ የወጡ ናቸው።" የሚለው ደረጄ ጌታቸው ከተፈናቃዮቹ መካከል አንዱ ነው። ደረጄ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ያቋቋሙት ኮሚቴ አባልም ነው። ኮሚቴው አንገብጋቢ ችግር ያለባቸው በኮሌጁ የቀድሞ መማሪያ ክፍሎች መኝታ እንዲያገኙ ያመቻቻል። ደረጄ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ የተጠለሉት በተለያዩ ጊዜያት የተፈናቀሉ መሆናቸውን ተናግሯል።
ተፈናቃዮቹ ያቋቋሙት ኮሚቴ ተወካዮች እንደሚሉት በኮሌጁ ከተጠለሉ መካከል ሕፃናት እና አረጋውያን ይገኙበታል። 80 ከመቶው ግን ወጣቶች ናቸው። "እዚህ ግቢ ውስጥ ከ600 በላይ ሰው ነው እየኖረ ያለው።" የሚለው ደረጄ የመማሪያ እና የቤተ-ሙከራ ክፍሎች የተፈናቃዮች መጠለያ መሆናቸውን ተናግሯል።
አሁን በሪፍት ቫሊ ኮሌጅ የተጠለሉት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት "ወደ ትውልድ ቀያችሁ ሒዱ" በመባላቸው አዲስ አበባ መድረሳቸውን ይናገራሉ። ለንግድ ሥራ ወደ ጅጅጋ ከተማ አቅንቶ የነበረው እና በግጭቱ የተፈናቀለው ብርሃኑ ግርማ ከኮሚቴ አባላቱ መካከል አንዱ ነው። "ኦቦ ድንቁ ሰው እንደሚረዱ ማንም ሰው ያውቃል። ከዚያ በግል ነው ሔደን ያስቸገርናቸው። ለ10 ሰው ነው መጀመሪያ የፈቀዱ። ከዚያ በኋላ ወሬው ተሰማ። ከተማ ውስጥ ተበትኖ ያለው ሰው ምን ያቁመው?" የሚለው ብርሃኑ አሁን ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ እነርሱ እየመጡ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።
"አሁን 2003 አባወራ ተመዝግቧል። ከዚህ ውስጥ የቅርብ ዘመድ ያለው ሰው እዛ ማደር አይችልም። ራሳችን ያወጣንው ሕግ ነው። መውደቂያ የሌለው፣ ዘመድ የሌለው እዛ ግዴታ መቆየት ስላለበት ድንኳን ተተክሎ ኮምፒውተሮች ከመማሪያ ክፍሎች ሜዳ ላይ ወጥተው ነው ሰው የገባበት" ሲል ያክላል።
አንድ ብርድ ልብስ እና አንድ ፍራሽ ለሁለት ለመጠቀም ተገደናል የሚሉት ተፈናቃዮች ከብዛታቸው አኳያ የጤና ሥጋት እንዳለባቸው ገልጠዋል። ለተፈናቃዮቹ ከምግብ እና ሥራ በላይ መጠለያ አንገብጋቢው ጉዳይ ሆኖባቸዋል። መጠለያ መሥጠት የነበረበት የአዲስ አበባ አስተዳደር ነበር የሚለው ብርሐኑ መረጃው ቢደርሳቸውም ቸልተኛ ሆነዋል ሲል ይወቅሳል።
"መረጃም አላቸው፤ ከሚዲያም ተደውሎላቸው ሲጠየቁ ሰምተናል። ከተለያዩ ቢሮዎችም መጥተው አይተውን ሔደዋል። ግን መልስ አልሰጡም። አሁንም እና የምጠይቀው ይኸን ነው። ያሳርፉን። መጠለያ እንዲሰጡን ነው የምንፈልገው ሕዝቡም የሚለው ይኸን ነው።"
"አሁን ያለንበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው" የሚሉት አቶ ደረጄ "አሁን ያለንበት የግለሰብ ቤት ነው። ትምህርት ቤቱን ለሥራ ይፈልጉታል። ይኸ ሰው እየረዳን ያለው ትሕትና ስለተሰማው ብቻ ነው።" ሲሉ ይናገራሉ።በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች መካከል በተቀሰቀሰው የድንበር ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ንብረት ወድሟል። በርካቶችም ተፈናቅለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በግጭቱ እጃቸው አለበት ብሎ የጠረጠራቸውን 103 ሰዎች አስሪያለሁ ማለቱ አይዘነጋም።
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ