1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀብር ስነ-ስርዓት የተካሄደው ለ28 ሟቾች ነው

ዓርብ፣ መስከረም 5 2010

መስከረም 2 ቀን በአወዳይ ከተማ በነበረ ተቃውሞ እና ግጭት የተገደሉ የሶማሌ ክልል ተወላጆች የቀብር ስነ-ስርዓት ዛሬ በጅግጅጋ ተፈጽሟል፡፡ የሶማሌ ክልል ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የአንድ ሳምንት ሀዘን አውጇል፡፡

https://p.dw.com/p/2k4ru
Symbolbild Kerze Flamme
ምስል Colourbox

የቀብር ስነ-ስርዓት የተካሄደው ለ28 ሟቾች ነው

ዛሬ ግብዓተ መሬታቸው የተፈጸመው የ28 ሟቾች ቢሆንም የሶማሌ ክልል ግን በአጠቃላይ 50 ገደማ የክልሉ ተወላጆች መሞታቸውን ከቀናት በፊት አስታውቆ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ በአወዳይ የሞቱት 18 ብቻ መሆናቸውን እና ከእነዚህም ውስጥ ስድስቱ የኦሮሞ ተወላጆች መሆናቸውን መግለጹ የሚታወስ ነው።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሀሙድ በዛሬው የቀብር ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት መስከረም 2 በአወዳይ ግጭት ወቅት ወደ 300 የሚደርሱ የሶማሌ ተወላጆች በአካባቢው ኦሮሞ ተወላጆች ከጥቃት መዳናቸውን አስታውሰዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልልን እና የአካባቢው አመራሮች እንደዚሁም የጸጥታ ኃያሎች ግን ዝምታን መርጠዋል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ “ይህን ጥቃት የፈጸሙት እና በማህበራዊ ድረ ገጽ የሚያስተጋቡት አካላት አሁን ያለውን ስርዓት የሚቃወሙ እና ህዝባችንን የሚጠሉ ናቸው” ብለዋል፡፡ “በሶማሌ ክልል የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው” ሲሉ የክልላቸው መንግስትን አቋም በንግግራቸው ግልጽ አድርገዋል፡፡“ ከፌደራል መንግስት እና ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር ግጭቱ በዘላቂነት የሚፈታበትን መንገድ በጋራ እንሰራለን” ብለዋል፡፡

 

ዮሐንስ ገብረ ዝግዚአብሔር

ኂሩት መለሰ