1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብርቱ የበጀት ክፍተትና ቢሊዮን ብሮችን የሚጠይቁት የመንግስት ፕሮጀክቶች

እሑድ፣ ግንቦት 27 2015

ከፍተኛ የበጀት ክፍተት ገጥሞኛል ያለው እና በበርካታ ጫና ውስጥ ተሰንጎ የሚገኘው መንግስት በሰፋፊ እርሻዎች ስኬታማ እንደሆነ፤ ብሎም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘቦችን የሚጠይቁ ግዙፍ ፕሮጄክቶችን ለመተግበር እየጣረ መሆኑን ይገልጻል ።

https://p.dw.com/p/4S8cX
Äthiopien Farmer und Farmland
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ሣምንታዊ የእንወያይ መሰናዶ

የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የበጀት ክፍተት እንደገጠመው ዐሳውቋል ። አንዳንድ ክልሎች ለመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ መክፈል ጭምር ተስኗቸዋል ። ደሞዝ ባለመከፈሉ እና ሠራተኞች ሥራ በማቆማቸው የተነሳም የመንግሥት ተቋማት ሙሉ በሙሉና በከፊል አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎች እንደሚገኙም ተዘግቧል ። የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ ያነሱ ሠራተኞች ለችግራቸው መፍትኄ ሳይሆን እስር እየገጠማቸው መሆኑም ተገልጿል ። መንግሥት ገጠመኝ ያለው የበጀት ክፍተት 194.6 ቢሊዮን ብር ይጠጋል ብሏል ። በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ 28 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ ማድረሱንም ይፋ አድርጓል ። ጦርነቱ ግን አሰላለፉን ቀይሮም አማራ እና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ አሁንም ቀጥሏል ። የቀጥታ በጀት ድጋፍ ያደርጉ የነበሩ የውጭ ሃገራት በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ ድጋፉቸውን ወደ ሰብአዊ ተደራሽነት ላይ ማዞራቸው ለክፍተቱ አስተዋጽኦ እንዳለው ይነገራል ። በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ብርቱ በደል እየፈጸመ ነው ያሉት መንግስት የውጭ ምንዛሬ እጥረት አይሎበት የኤኮኖሚ ጫና እንዲበረታበት በሚል የገንዘብ እቀባ ዘመቻ ከጀመሩ ሰነባብተዋል ። በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ተሰንጎ የሚገኘው መንግስት በሰፋፊ እርሻዎች ስኬታማ እንደሆነ፤ ብሎም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ገንዘቦችን የሚጠይቁ ግዙፍ ፕሮጄክቶችን ለመተግበር እየጣረ መሆኑን ይገልጻል ። «ብርቱ የበጀት ክፍተትና ቢሊዮን ብሮችን የሚጠይቁት የመንግስት ፕሮጀክቶች» የውይይት ርእሳችን ነው ። በውይይቱ 4 እንግዶች ተሳታፊ ናቸው። 

ከከፍተኛው የበጀት ክፍተት በተጨማሪ የሸቀጦች እና ፍጆታዎች ዋጋ ንሯል
ከከፍተኛው የበጀት ክፍተት በተጨማሪ የሸቀጦች እና ፍጆታዎች ዋጋ ንሯልምስል Alemenew Mekonnen/DW
  1.  ኢሜረተስ ፕሮፌሰር ዳንኤል ተፈራ፤ ኢኮኖሚክስ ምሁር
  2. ፕሮፌሰር መንግሥቱ ከተማ፤ የኤኮኖሚክስ ባለሞያዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ
  3.  ዶ/ር ደገላ ኤርጌኖ፤ በሲቪል ሠርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ መምህር እንዲሁም ናቸው።

በዚህ ውይይት ተካፋይ እንዲሆኑ ለገንዘብ ሚንስትር እና ምክትላቸው በእጅ ስልካቸው እንዲሁም በጠቅላይ ሚንስትሩ ለተቋቋመው «ብሔራዊ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ጉባኤ» አባል በተደጋጋሚ ብንደውልም አልተነሳልንም ። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወ/ሮ ፀሐይ በቀለም በውይይቱ ለመሳተፍ ቃል ገብተው በዕለቱ ግን ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተደጋጋሚ ስንደውልም አላነሱም።

ሙሉውን ውይይት በድምፅ ማድመጥ ይቻላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti