ብዙዎችን ያፈናቀለው የሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልሎች ግጭት
የጎሳ ግጭት በመቶ ሺዎችን አፈናቀለ
በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዚያት በተፈጠረ ግጭት የተነሳ አስከፊ የሕዝብ መፈናቀል ተከስቷል። በጎሳዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት እና ያስከተለው መፈናቀል በቀዳሚነት የጎዳው የኦሮሞ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆችን ነው። በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት እነዚህ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ ለመቀበል እየሞከሩ እና የወደፊቱ እጣ ፈንታቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ።
ከጎሳ ግጭት መሸሽ
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በቆለቺ ኮረብታዎች መካከል ለተፈናቃዮች ሁለት መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ። ቀደም ብሎ በተሰራው የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ በ2015 ዓም በድርቅ እና በጎሳ ግጭት ሰበብ የተፈናቀሉ እያንዳንዳቸው ከስድስት እስከ 10 አባላት ያላቸው 5,300 የሶማሌ ቤተሰቦች ይኖራሉ። በአዲሱ መጠለያ ጣቢያ ደግሞ ባለፈው መስከረም በተከሰተው የጎሳ ግጭት የተፈናቀሉ 3,850 ሰዎች ከለላ አግኝተዋል።
የፖሊስ ጭካኔ
ይህ የሶማሌ ተወላጅ እንደሚለው ፣ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ፊቱ ላይ ተተኩሶበታል፣ ከዚያ መሬት ላይ እንደወደቀ ፖሊስ በቀጠለው ተኩስ ፊቱ ላይ ጥይት የተዋቸው ብዙ ጠባሳዎች ይታያሉ። ብዙዎቹ ተፈናቃይ ሶማሌዎች ለተፈጠረው ቀውስ እና ደም መፍሰስ የክልሉን ልዩ ፖሊስ ኃይል ተጠያቂ ያደርጋሉ።
በየቦታው የመጠለያ ጣቢያዎች ተተክለዋል
ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉት እነዚህ ሶማሌዎች አሁን በአንድ ከድሬዳዋ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ የእጓለ ማውታን ውስጥ ተጠለዋል። አንዳንዶች በሕይወት ለመትረፋቸው ጣልቃ የገቡትን የኢትዮጵያ ፌዴራል ወታደሮችን ያመሠግናሉ። ይሁን እንጂ፣ ይህ ርምጃ ብቻውን እዚያ እንዲቆዩ በቂ እንዳልሆነ አንዱ ተፈናቃይ ገልጿል፣ ምክንያቱም፣ ፌዴራሉ መንግሥት ወታደሮቹን ሰላም እንዲያስጠብቁ የላካቸው ኃይላት በአካባቢው አንድ ሳምንት ወይም አንድ ወር ቆይተው በሚመለሱበት ጊዜ እንደገና ተመሳሳይ ጥቃት ሊደርስባቸው ስለሚችል በኦሮሚያ ክልል መቆየቱ አስጊ መሆኑን አመልክቷል።
ኦሮሞዎችም ተፈናቅለዋል
በጎሳው ግጭት እንደተፈናቀሉ ከሚገመቱት ከ200,000 እስከ 400,000 ሰዎች መካከል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆችም ይገኙባቸዋል። በአወዳይ ከተማ በተነሳው የኦሮሞ ዓመፅ በርካታ የሶማሌ ነጋዴዎች ከተገደሉ በኋላ ነበር የተባረሩት። ከሐረር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ባሉ መጋዘኖች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ወደ 3,500 የሚጠጉ የኦሮሞ ተወላጆች ተጠለዋል።
የግዳጅ እና የኃይል ተግባር የታከለበት መፈናቀል
በኢንዱስትሪው ፓርክ ውስጥ የተጠለለው ይህ የኦሮሞ ተወላጅ ከሶማሌ ክልል በተባረረበት ወቅት ከአንድ የሶማሌ ፖሊስ ጋር በተደባደበበት ጊዜ ፖሊሱ አፍንጫውን እንደነከሰው ይናገራል። የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት እንደሚሉት፣ የኦሮሞ ተወላጆች ከአካባቢው እንዲነሱ የተደረጉት በአወዳይ በተፈፀመው ግድያ ሰበብ አፀፋ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል ሲባል ነው፣ በነርሱ አባባል በክልሉ በነበረው የጎሳ ግጭት ሰበብ አንድም የኦሮሞ ተወላጅ አልሞተም ፣ ተፈናቃይ የኦሮሞ ተወላጆች ግን ይህን አነጋገር በፍፁም አይቀበሉትም።
ክስ እና መላ ምት
የሁለቱም ክልሎች መንግሥታት ፖሊሶቻቸው በግጭቱ ተሳትፈዋል መባሉን በማስተባበል፣ አንዱ ሌላኛውን ወገን ዘግናኝ ሴራ አካሂዷል በሚል ይከሳሉ። በፌዴራል ደረጃ ፣ መንግሥት //// ግጭቱን ለማስቆም በቂ ርምጃ አልወሰደም ወይም ሆን ብሎ እንዳላየ አልፏል፣ እንዲያውም ከፋፍሎ መግዛትን የመሰለ የራሱን ፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት ሲል ግጭቱን አባብሷል ሲል ይወቀሳል። ሌላው የሚሰማው አማራጭ ሀሳብ ደግሞ ግጭቱ በጣም የተስፋፋውን ግጭት የማስቆም አቅም የለውም የሚለው ነው።
ቀሪው ግጭቱ የተወው ጠባሳ እና ስቃይ ነው
በመጠለያው ያሉ ተፈናቃዮች ዕለታዊ ኑሯቸውን ለመምራት ይሞክራሉ። አንድ እናት ልጇን ታጥባለች። ሌሎች ግን ምንም ነገር እንዳልሆነ ኑሮን መምራቱ ከብዷቸዋል። «ላዬ ላይ ቤንዚን አርከፍክፈው ለኮሱት» ትላለች በጡቶችዋ፣ በሆዷ፣ በአንገቷ እና እጆችዋ ላይ ጠባሳ ያላት የ28 ዓመቷ ሁሳይዳ መሀመድ። ይህን ያደረጉት የሶማሌ ወጣት ወንዶች ነበሩ።
ቤተሰቦች ተለያይተዋል
በግጭቱ ሰበብ በተፈጠረው ግርግር ባልና ሚስቶች ተለያይተዋል። ልጆች ጠፍተዋል። ለቤተሰብ ካለው ታማኝነት ይልቅ የጎሳው ጥላቻ አይሏል። ከሶማሌ ክልል ከመባረሯ በፊት እቤቷ አምጥተው የጣሉላትን አንድ ህፃን የያዘችው ፋጢማ የህፃኑ እናት ከአንድ ከኦሮሞ ተወላጅ ጋር የተጋባች እንደነበረች ትናገራለች፣ በመቀጠልም « የራሴ ሶስት ልጆች ስላሉኝ ህፃኑን ማሳደግ ቀላል አይሆንም።»ትላለች።
ቤት አልባ መሆን እና ግራ መጋባት
በድሬዳዋ ከተማ ያሉት ተፈናቃዮች መኖሪያ ቤታቸውን መቼ ማየት እንደሚችሉ የሚያውቅ የለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉም ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ስለሆነ ወደየቤቱ መመለስ እንዲችል ለማድረግ ቃል ገብቷል። ይሁን እንጂ፣ በመወዛገብ ላይ ያሉት የሁለቱ ክልሎች ትብብር ስለሚያስፈልግ ይህ በቅርቡ እውን የሚሆን አይመስልም። በርካታ የኦሮሞ እና የሶማሌ ተወላጆችም ወደነበሩበት መመለሱ አስተማማኝ አይደለም ባዮች ናቸው። AT/JJ/HM