ቱሪዝም በላሊበላ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 17 2015የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ በላሊበላ የነበረው የውጪ ጎብኝዎች ቁጥር መቀነሱና የሰሜኑ ጦርነት የፈጠረው ጫና ለላሊበላ የቱሪዝም እንቅስቃሴ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖበት ቆይቷል፡፡
አሁን ሁኔታዎች እየተሸሻሉ በመምጠታቸው ግን ተዳክሞና ሥራው ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት እያሳየ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ፣ ነዋሪዎችና በአስጎብኝነት የተሰማሩ ግለሰቦች ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል፡፡
አቶ ቸኮለ ታዘበው የተባሉ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ የቱሪስቱ ቁጥር የተፈለገውን ያክል ባይሆንም እንቅስቃሴው መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
“ ከጦርነቱ በፊት የነበረውን ያክል (ቱሪስት) ባይመጣም መብራቱ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የመጠጥ ውሀውም ስለተተካከለ፣ የቱሪስት ፍሰቱ አነስተኛ ቢሆንም … ደህና ነው” ብለዋል፡፡
182 አባላት ያሉትን የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት አስጎብኝ ማህበር ሊቀመንበር አቶ እስታሉ ቀለሙ በበኩላቸው የቱሪስቱ ፍሰት እንደቀድሞው ባይሆንም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መጀመሩንና አንዳንድ የማህበሩ አባላት ወደ ስራ እየተሰማሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
“… መጀመሪያ ኮቪድ በኋላም ጦርነቱ እንደተከሰተ ያሉን 182 አባላት ከስራ ውጪ ሆነን ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገን ነው ቆየን ላለፉት ሶስት ዓመታት፣ ጦርነቱ ከቆመ በኋላ ወጣ ገባ ማለት ተችሏል፣ አሁንም ቢሆን ወደ ስራ ለመመለስ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ያን ክል የተጠናከረ ባለመሆኑ በችግር ውስጥ ነው ያለነው፣ አሁን ሁኔታዎች እየተመቻቹ በመምጣታቸው የተወሰኑ ልጆች በተወሰነ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት፣ 182 አስጎብኝ ስለሆነ ላሊበላ ላይ ያለ ሁሉም ስራ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ ግን የለም፡፡” ነው ያሉት፡፡
በከተማዋ የመዘና ሪዞርትና ስፓ ባለቤት አቶ ዮሐንስ አሰፋ ከሰላም ስምምነቱና በከተማዋ ከአንድ ዓመት በላይ ተቋርጠው የነበሩ የኤሌክትሪክና ውሀ አገልግሎቶች ከተጀመሩ በኋላ የአውሮፓ ቱሪስቶች መምጣት መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ፣ “መብራት መጥቶልናል፣ ውሀም በበቂ እየገባልን ነው ያለው፣ እኛም ሆቴሎቻችን አዘጋጅተን መጪውን እንግዳ እየተጠባበቅን ነው፣ ቱሪስቱም ቢሆን እንደድሮው በገፍ ባይመጣም እየመጣ ነው ያለው፣ ጥቂትም ቢሆን፣ ጀርመኖች፣ ሰፔኖች፣ ዩጎዝላቭ አካባቢ ያሉ አካባቢዎች እየገቡ ነው ያሉት፡፡” ብለዋል፡፡
የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴም አሁን ያለው ሁኔታ በመልካም ጅምር ላይ እንደሆነ በስልክ ነግረውናል፡፡
“ ተዘግተው የነበሩ (አገልግሎት ሰጪ ተቋማት) በሙሉ አሁን ሥራ ለመጀመር ተፍ ተፍ እያሉ ነው ያሉት፣ ተስፋ ሰጪ ነው ቱሪስቶችም እየመጡ ናቸው፣ የሰላም ስምምነቱ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው ማለት ይቻላል፣ ከመብራት መምጣቱና ከሰላም ስምምነቱ ጋር ተያይዞ የቱሪስቱ ቁጥር ይጨምራል የሚል ግምት አለን” ሲሉ ገልጠዋል፡፡
ሥራ ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ ቢሆኑም የስነልቦና ስልጠናና የፋይናንስ ድጋፍ ብንጠይቅም ከተማ አስተዳደሩ ሊፈቅድ አልቻለም ሲሉ የአስጎብኚ ማህበሩ ሊቀመንበር ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የባህልነ ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊው አቶ አዲሴ ግን “የስልጠናም ሆነ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል በጀት የለንም” የሚል ቁርጥ ያለ ምላሽ ነው የሰጡት፡፡
ባለፉት 3 ዓመታት የኮሮና ቫይረስ በአስከተለው ጫናና በጦርነቱ ሰበብ የላሊበላን አብያተ ክርስቲያት ከሚጎበኙ 120 ሺህ ያህል ጎብኝዎች 750 ሚሊዮን ብር ገቢ ማጣቱን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ አብራረተዋል፡፡
በቅዱስ ላሊበላ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው እንደተገነቡ የሚነገርላቸው 11 የላሊበላ አብተ ክርስቲያናት የሚገኙት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ ከተማ ውስጥ ነው፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ