1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሷ ፕሬዚደንት እና የሐረር ድምጾች

ዓርብ፣ ጥቅምት 16 2011

አምባሳደር ሣኅለወርቅ ዘውዴ አዲሷ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ኾነው መመረጣቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዋነኛ መነጋገሪያ ለመኾን አፍታም አልፈጀበትም ነበር። ሐረር በመጠጥ ውኃ እጦት እና በቁሻሻ ሙሊት መጥፎ ጠረን ለወራት መሰቃየቷ በየአቅጣጫው ቁጣን ቀስቅሷል። ክልሉ የውኃ እጦት ችግሩን በከፊል መቅረፉን ቢገልጥም፤ ነዋሪዎች አኹንም እያማረሩ ነው።

https://p.dw.com/p/37G2D
Äthiopien Addis Abeba neue Präsidentin Sahle-Work Zewde
ምስል Getty Images/AFP/E. Soteras

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

አምባሳደር ሣኅለወርቅ ዘውዴ አዲሷ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ኾነው መመረጣቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዋነኛ መነጋገሪያ ለመኾን አፍታም አልፈጀበትም ነበር። አብዛኛው አስተያየት ሰጪ በሀገሪቱ ሴት ርእሰ-ብሔር መመረጣቸው እጅግ እንዳስደሰተው ገልጧል።  ለረዥም ዓመታት በውጭ ሃገራት የዲፕሎማትነት ሞያ የሕይወት ዘመን ብቃት ያካበቱ ባለሞያን በፕሬዚደንትነት መሾም አቅማቸውን አይመጥንም የሚሉ ድምጾችም ተበራክተዋል። ሐረር በመጠጥ ውኃ እጦት እና በቁሻሻ ሙሊት መጥፎ ጠረን ለወራት መሰቃየቷ በየአቅጣጫው ቁጣን ቀስቅሷል። ክልሉ የውኃ እጦት ችግሩን በከፊል መቅረፉን ቢገልጥም፤ ነዋሪዎች አኹንም እያማረሩ ነው።

አምባሳደር ሣኅለወርቅ ዘውዴ አዲሷ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ኾነው እንደሚመረጡ መነገር የጀመረው የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች እንደራሴዎች ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን፣ 2011 ዓም ካካሄዱት ስብሰባ ዋዜማ ጀምሮ ነበር። ሸዋንጌ አቡ በፌስቡክ ገጹ ላይ ረቡዕ ምሽት ባወጣው ጽሑፍ አምባሳደሯ እንደሚመረጡ ቀድሞ ጠቅሶ ነበር። «ክብርት አምሳደር ሣኅለወርቅ ዘውዴ በነገው እለት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሆኖው ይሾማሉ» ይላል የሸዋንጌ ጽሑፍ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የአፍሪቃ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ተሹመው በማገልገል ላይ የነበሩት የ68 ዓመቷ አምባሳደር  ሣኅለወርቅ ፕሬዚደንት ኾነው መመረጣቸውን በርካቶች አወድሰዋል። «አምባሳደር ሣኅለወርቅ ዘውዴ 4ኛዋ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በመሆን ተሾሙ ይሄ ለሴቶች ማዘን አይደለም ይሄ ለሴቶች ስልጣን ማካፈል ብቻ አደለም። ለነገ ሴት እህቶቻችን ለሚመጡት ሴት ልጆቻቸን ያልተከለከለ ምናብ ያልታጠረ ህልም ማውረስ ነው» ሲል መልእክቱን ያስተላለፈው ዳንኤል ተስፋዬ ነው። አምባሳደር ሣኅለወርቅ ዘውዴ በምክር ቤት ባሠሙት ንግግር ተመሳሳይ መልእክት አስተላልፏል።

«ትናንት ሴት ልጆቻችሁን ከወንዶች ባላነሰ ኹኔታ ትልቅ ደረጃ  እንደሚደርሱ፤ ለራሳቸውም ለቤተሰቦቻቸውም እናም ለወገኖቻቸውም ተስፋ ምልክት እንደሚኾኑ ሳትታክቱ አቅማችሁ በፈቀደ፤ በጸሎት፣ በሞራል እንዲኹም አቅማችሁ በፈቀደው ኹሉም ፍቅር የሰጣችሁ የደገፋችሁ ወላጆች እኔ የዚህ ድጋፍ ውጤት ስለኾንኩ እንኳን ደስ አላችሁ።»

Äthiopien Addis Abeba neue Präsidentin Sahle-Work Zewde
ምስል Getty Images/AFP/E. Soteras

አምባሳደር ሣኅለወርቅ ዘውዴን ከድሮ ጀምሮ የሚያውቋቸው ሰው ለDW በእንግሊዝኛ በሰጡት አስተያየት ደስታቸውን እንዲህ ነበር የገለጡት። «ምን ያኽል ደስ እንዳለኝ ልነግርህ አልችልም። ምክንያቱም ሴት ርእሰ-ብሔር ስላለን ብቻ አይደልም፤ እሳቸው ማስመሰል የሌለባቸው ናቸው። ስለእሳቸው ዐውቃለሁ። ስለቀድሞ ማንነታቸው ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ እጅግ በጣም በጣም ኩራት ይሰማኛል። ደህና ሁኑ

አምባሳደር ሣኅለወርቅ ዘውዴ ፕሬዚዳንት ኾነው የተመረጡት የሥልጣን መልቀቂያ ያቀረቡት ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን በመተካት ነው። ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከአምስት ዓመታት አገልግሎት በኋላ የፕሬዚደንትነት ዘመናቸው ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት እየቀረ ለምን ኃላፊነታቸውን ማስረከብ እንደፈለጉ የተጠቀሰ ነገር የለም።

መልቲ ዳ ሣልቫኖ በትዊተር ገጿ የዶክተር ሙላቱ ተሾመ ሥልጣን የለቀቁበት ምክንያት  እንዲገለጥ ጠይቃለች። «ሕዝብ የማወቅ መብት አለው። የቀድሞው ርእሰ-ብሔር ሙላቱ ተሾመ ሥልጣናቸውን የለቀቁት ለምንድን ነው ስትል በእንግሊዝኛ ጽፋለች። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ሥልጣን በለቀቁበት ወቅት ሥልጣን ያስረከቡበትን ምክንያት እንዲህ ገልጠዋል። «ዛሬ ሀገራችን የፈነጠቀውን ተሥፋ ማስቀጠል የሚችሉ፤ ቁርጠኝነትን የተላበሱ አመራር ማግኘቷ እንደዜጋም በልቤ የተለየ ደስታ ፈጥሮብኛል። በዚህም መሠረት ይዤ የቆየሁትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ውሳኔ ላይ የደረስኩ ስለኾነ የተከበረው ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንትነት ኃላፊነቴ እንዲያሰናብተን እጠይቃለሁ። ኢትዮጵያ ሀገራችን በሕዝቦቿ አንድነት ለዘለዓለም  ትኑር።»

ሕይወት እምሻው ፌስቡክ ላይ ያሰፈረችው አስተያየት፦ «ለወጣቱ ትውልድ ለማስረከብ የሚለው ሰበብ ነው በሳቅ ያፍነከነከኝ እኔ…! ጊዜው የሚጠይቀውን ትግል ማድረግ ስላልቻልኩ የምትለዋ አዲሷ ሰበብ ትሻል ነበር» ይላል።

Äthiopien Mulatu Teshome ist neuer Präsident
ምስል Elias Asmare/AFP/Getty Images

በፕሬዚዳንትነት ሹመቱ የተደሰቱ በርካቶች የመኾናቸውን ያኽል ጥያቄ ያነሱም ብዙ ናቸው። መሥፍን አማን አርጋው ትዊተር ላይ ያሠፈረው ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል። «ከሞያው ጋር ሆድና ጀርባ ሆነው በዓለም አቀፍ መድረኮች መሸማቀቂያ ያደረጉ ሰወችን በውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ሃላፊነት አስቀምጦ፣ በስራው ልምድም ሆነ ውጤታማነት የመጀመሪያ ረድፍ ተብለው ከሚጠቀሱ የሃገራችን ዲፕሎማቶች አንዷን፣ ያውም ከትልቅ ዓለማቀፍ ሃላፊነት ላይ ጠርቶ፣ "የሪፖብሊኩ ፕሬዝዳንት" የሚል እዚህ ግባ የማይባል ኃላፊነት ላይ መሾም የእውቀት ብክነትነው። ነገሩን የበለጠ አስቂኝ የሚያደርገው የፌደራል የስልጣን ሃላፊነቶችን ለማመጣጠን እንደተወሰደ ርምጃ ተደርጎ መቅረቡ ነው። ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት ነው፣ ያለው ያገሬ ሰው»

የዞን ጠዘኝ ጦማሪያን አባል ሶሊያና ሽመልስ፦ «ክብርት ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የፕሬዘዳንትነት ሃላፊነትን ሲቀበሉ የሚናውን ገደብ እና አቅም የራሳቸውን የሥራ ልምድና ለአገር ማድረግ የሚፈልጉትን አስተዋፅዖ መዝነውና ከግምት ውስጥ አስገብተው ነው። ክብርት ፕሬዘዳንትን ከአቅማቸው በታች ኃላፊነት ወሰዱ የምትሉ ሰዎች በተዘዋዋሪ (ሙገሳ ሽፋን) ከራሳቸው ይልቅ እኔ ነኝ የማውቅላቸው እያላችሁ እንደሆነ ታውቋችኃል ብላለች።

«አወድሱ ብሎ ጽሑፍ? ቁልቁለት» ሲል የሶሊያና ጽሑፍን የተቸው ክፍለየሱስ አበበ ነው። ሮቤል ንጉሤ እዛው ትዊተር ላይ በሰጠው አስተያየት፦ «ዝም ብሎ አወድሱማ አይሠራም። ፕሬዝዳንቷም ቢሆን ካላቸው አቅም አንፃር [የዶክተር ሙላቱ ተሾመን] ወንበር መረከባቸው አይመጥንም መባሉ ዉሀ የሚቋጥር ነዉ። ብቻ ዝም ብሎ ነገሮችን ፆታዊ ማድረጉ ደግም አይደል» ብሏል።

ዩስቱስ ካንግዋጌ፦ «ለአፍሪቃ የሴቶች እኩልነትን በተመለከተ ከወሬ ይልቅ ድርጊት እንዲቀድም መንገድ ቀያጅ ወሳኝ ወቅት ነው። ለአሁኑም ኾነ ለወደፊቱ አስደናቂ ተግባር» ሲል ሹመቱን አድቋል። መንሡር ረሺድ ሺፋ ደግሞ፦ «ደስ የሚል ዜና! ለኢትዮጵያችን ድም አጥፍታ የሠራችው እናት ፕሬዝዳንት ሆነችልን! ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ!!» ሲል አድናቆቱን ገልጧል።

Straßenszene in Harar, Äthiopien
ምስል Z. Abubeker/AFP/Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች የሚለው የትዊተር ገጽ፦ «ሣኅለ-ወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ርእሰ-ብሔር ኾነው ተመረጡ፤ ያም በአፍሪቃ ብቸኛዋ ርእሰ-ብሔር ያደርጋቸዋል» ሲል ጽፏል። አምባሳደር ሣኅለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ከፍተኛ ሥልጣን ያገኙ ሴት መሪ ናቸው ሲሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ለተሰጡ አስተያየት ምላሽ የሚመስል ጽሑፍ ኄኖክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትዊተር ላይ አስፍሯል።  «ኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች ወደ አመራሩ መምጣታቸው ከፈጠረው ስሜት አንጻር፤ በሺህ ሰባት መቶዎቹ ዘመን ራስ ሥኁል ሚካኤል በዘመነ-መሣፍንት ሥልጣኑ ማማ ላይ ከመውጣታቸው በፊት እጅግ ኃይለኛዋ የኢትዮጵያ መሪ ንግሥተ-ነገሥት ምንትዋብ ታሪክ እነሆሲል ይነበባል።  ስለ ንግሥቲቱ የሚያትት ሌላ ጽሑፍም ኄኖክ አያይዟል። 

የDW የፌስቡክ ገጽ ላይ ከተሰጡ በርካታ አስተያየቶች መካከል ቀጣዮቹ ይገኙበታል። «እንኳን ሴት ሚዎቿ ሀገራችን እምየ ኢትዮጵያም ከዉስጥ በሌለ ከአንገት በላይ በሆነ መደመር በሚል የዉሸት ዲስኩር ታላቅ ፈተና ገጥሟታል፤ እኛን ያሳሰበን ይህ ነዉ» የዓለሙ አበበ አስተያየት ነው።

 ዮናስ ክብረት፦ «የአምባሳደ ሣኅለወርቅ ሹመት ወይዘሮዋ ከነበራቸው የውጭ ጉዳይ እውቀት አንፃር ብክነት አይሆንም ወይሲል ጠይቋል።

ጤና ደስታ፦ «ጥሩ ልምድና ዕውቀት ያላቸው የሴት ፕሬዝዳንት መመረጣቸው ለሴቶች ክብርና ደስታ ሊሰማን ይገባል። መልካም ዘመን ይሁንላቸው» ብላለች። ዓሊ ሐሞድ፦ «ለሴት እኅቶቻችን አንኳን ደስ አላችሁ» ሲል በአጭሩ አስተያየቱን አስፍሯል።

ሌላው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሳምንቱ እጅግ መነጋገሪያ ኾኖ የቆየው የሐረር ከተማ የውኃ እጦት እና ኅብረተሰቡ በቁሻሻ ሙሊት መጥፎ ጠረን ለወራት እንደሚሰቃይ መግለጡ ነው። በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ዐሥር ሚሊዮን ካልተከፈለን ውኃው ወደ ሐረር እንዲሄድ አንፈቅድም አሉ መባሉን በተመለከተ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየቶች እንዲሰነዝሩ አድርጓል።

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

ቃሪያ በሚጥሚጣ የተባለ አስተያየት ሰጪ በDW የፌስቡክ ገጽ ላይ ቀጣዩን ጽሑፍ አስፍሯል። «የአንድን ከተማ ወኃ ማገድ ወንጀል ብቻ ሳይሆን -ሰብአዊ ድርጊት ነው! መንግሥትም ለአንዲት ደቂቃም ቢሆን ጆሮ-ዳባ ሊለው የሚገባ ጉዳይ መሆን አልነበረበትም! ያሳዝናል» ይላል።

ሌላ ለDW አስተያየታቸውን በድምፅ የሰጡ የሐረር ከተማ ነዋሪ የኮሌጅ መምሕር፤ በከተማዪቱ የተፈጠረው ችግር ኅብረተሰቡ ጠየቀ የተባለውን ገንዘብ በመክፈል ብቻ የማይፈታ መኾኑን አክለዋል። ማንነታቸውን ሳንገልጥ ድምፃቸውን ቀይረን ያሰማነው መልእክት እንዲህ ይላል። «በድርድር አይፈታም። ቆሻሻው ተመልሶ ይኸው እና ታመን ተኝተናል። ጥያቄው የገንዘብ አይመስለኝም እኔ። አሁን እኮ ለምሳሌ መንግሥት ኃይል አልባ ኾኗል።  መንግሥት አኹን በጉልበት በማስፈጸም ምናምን አይደለም። ያልሠራቸውን እዳ እንዲህ እዳ ተከምሮበት ያላደረገውን፤ የጋራ የተፈጥሮ ሐብትን አለመጠቀም፤ ቀድሞ ማሰብ የነበረበትን፤ 27 ዓመት የተዘራው የዚህ የዘር እና የጥላቻ  እንትኖች ጠቅላላ አሁን ላለው ላለው ነገር ዳርገውናል። 10 ሚሊዮን ብር ዛሬ ቢከፈል እኔ አይታየኝም። ቢለቀቅ ምንም መፍትኄ አያመጣም።»

ይኽን የበርካቶች ሮሮ የኾነ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች የመጠጥ ውኃ ችግር በተመለከተ በከፊል መፍትኄ አግኝቷል ሲሉ የሐረሪ ክልል ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ለDW ተናግረዋል።  «ጥሩ ጅምር ነው» ያለችው ሎቭድ ሙን፦ «ግን በአሁኑ ሰአት በርሜሎችና ጀሪካኖቻችን ከዝናብ ባገኘነው ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ተሞልተዋል ፈጣሪ ይመስገን» ብላለች።  ዕውነት ዘሪሁን ደግሞ፦ «ግን ውሃው እኮ ዛሬም አልተለቀቀም ትላንት ከተስማሙ ዛሬ እንኳን ማግኘት ነበረብን» ብሏል። «የሃረር ከተማ ነዋሪ ለለውጡ ሲባል እንዴት ስድስት ወር ይጠማ?» ሲል ያጠየቀው ደግሞ ተስፋ ዓለሙ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti