1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድሐ አገሮችን ሮሮ ማን ይሰማል?

ረቡዕ፣ የካቲት 29 2015

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት "በትንሹ ያደጉ" የሚባሉ 46 ደሐ አገሮች ጉባኤ በቃጣር በመካሔድ ላይ ይገኛል። የድሆቹ አገራት መሪዎች እና ባለሥልጣናት በቃጣሩ ስብሰባ ሮሯቸውን እያሰሙ ነው። ይኸ ቡድን ከተመሠረተ አምስት አስርት ዓመታት ቢሻገርም ይኸ ነው የሚባል ለውጥ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ነዋሪዎች ላሏቸው አገራት አልታየም።

https://p.dw.com/p/4OPJ4
Katar, Doha | UN LDC5 Konferenz
ምስል Amiri Diwan of the State of Qatar/Handout/AA/picture alliance

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድሐ አገሮችን ሮሮ ማን ይሰማል?

የኢትዮጵያ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋን ጨምሮ "በትንሹ ያደጉ" የሚባሉት አገሮች መሪዎች እና ባለሥልጣናት የሚሳተፉበት የዶሐ ጉባኤ ሮሮ የተጫነው፤ ወቀሳም የበረታበት ሆኖ ታይቷል። ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሔደው ጉባኤ የናጠጡት አገራት ተወካዮች፣ እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች ጭምር የተገኙበት ቢሆንም ከፍ ብሎ የተሰማው የድሆቹ ሮሮ ነበር። ይኸ ጉባኤ በአስር ዓመት አንድ ጊዜ የሚካሔድ ሲሆን የዘንድሮው ከጎርጎሮሳዊው 2021 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ የተገፋ ነው።

በቃጣር ቅንጡ አዳራሾች የካቲት 26 ቀን 22015 የተጀመረው ጉባኤ ከአምስት ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች ቢኖሩትም ዋንኛ ትኩረቱ የከባቢ አየር ለውጥ ዳፋ የበረታባቸው፣ ግጭት የማያጣቸው፤ ብርቱ ድህነት የተጫናቸው አገራት ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት "the least developed countries" የሚል ጎራ አበጅቶላቸዋል። የዶሐውን ጉባኤ በተባባሪ ሊቀ-መንበርነት የመሩት የማላዊው ፕሬዝደንት ላዛረስ ማካርቲ ቻክዌራ “በዚህ የተገኘንው በትንሹ ያደጉ ከሚለው ጎራ ወጥተን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ መቀላቀላችንን የምናረጋግጥበትን መንገድ ለማግኘት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። 

ይኸ ፕሬዝደንት ላዛረስ ማካርቲ ቻክዌራ የተመኙት ጉዳይ ግን እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ መፍትሔ አይመስልም። በመድረኩ ንግግር ያደረጉ የደሐ አገራት መሪዎች እና ሚኒስትሮች ሐሳብም ይኸንንው የሚጠቁም ነው። በትንሹ ያደጉ አገሮች ቡድን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተፈጠረ ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላም መፍትሔ እንደሌለ የተናገሩት የኢትዮጵያ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ "ለውጥ ያስፈልጋል" ሲሉ ተደምጠዋል። 

"ከምሥረታው ጀምሮ የእያንዳንዱ በትንሹ ያደጉ አገሮች አባል ፍላጎት መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት እና ከቡድኑ መውጣት ነበር። ይሁንና ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላ ከቡድኑ የመውጣት ሒደት ዘገምተኛ መሆኑን መታዘብ እና ብዙዎቻችን ራሳችንን እዚሁ ምድብ ውስጥ ማግኘታችን ልብ የሚሰብር ነው" ያሉት ዶክተር ፍጹም "ይኸ መለወጥ አለበት። ለውጡም ፈጣን ሊሆን ይገባል" ሲሉ ወትውተዋል። 

ድህነት የበረታባቸው “በትንሹ ያደጉ አገራት” እነማን ናቸው?

ኢትዮጵያን ጨምሮ 33 የአፍሪቃ አገራት “በትንሹ ያደጉ አገራት” ከሚባለው ምድብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን በዚሁ ምድብ ውስጥ ይገኛሉ። ምድቡ ከእስያ አፍጋኒስታን እና ባንግላዴሽን ጨምሮ ዘጠኝ፤ ከካሪቢያን ሒይቲ ከፓሲፊክ ኪሪባቲ፣ ሶሎሞን ደሴቶች እና ቱቫሉን ያካትታል። የምድቡ አባላት ከድህነት ባሻገር አንድ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ግጭት የጠናባቸው መሆናቸው ሊሆን ይችላል። ከአፍሪቃ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ለዚህ እንደ ማሳያ ሊነሱ ይችላሉ። የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ፉዋስቲን አርካንጅ ቱዋዴራ አገራቸው ያላትን የተፈጥሮ ሐብት እየጠቀሱ ድህነቷን ማስረዳት ግን ፈታኝ ይሆንባቸዋል። 

“በትንሹ ያደጉ አገራት”
ኢትዮጵያን ጨምሮ 33 የአፍሪቃ አገራት “በትንሹ ያደጉ አገራት” ከሚባለው ምድብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን በዚሁ ምድብ ውስጥ ይገኛሉ።

ፕሬዝደንት ቱዋዴራ “ወርቅ፣ ዳይመንድ፣ ኮባልት፣ ነዳጅ፣ ዩራኒየምን ጨምሮ ከ470 በላይ ማዕድናት፣ ለግብርና አመቺ የሆነ ከ15 ሚሊዮን ሔክታር በላይ ያልታረሰ መሬት፣ 2.5 ሚሊዮን ሔክታር ደን ያላት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ነጻነቷን ካገኘች ከ60 ዓመታት በኋላ ከዓለም ድሐ አገሮች አንዷ መሆኗን እንዴት ማስረዳት እና መረዳት ይቻላል?” ሲሉ ለዶሐው ጉባኤ ተሳታፊዎች ጥያቄ ሰንዝረዋል። 

ፕሬዝደንቱ በዶሐው ስብሰባ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ለገጠማት ቀውስ ጣታቸውን በስም ሳይጠቅሱ "አንዳንድ" ባሏቸው ምዕራባውያን አገራት እና ኩባንያዎች ላይ ቀስረዋል። ቱዋዴራ እንደሚሉት ማዕከላዊ አፍሪቃን የሚያብጡትን "የታጠቁ አሸባሪ ቡድኖች" በገንዘብ የሚደግፉት "አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ወይም ኩባንያዎቻቸው" ናቸው። በዚህም አገሪቱ አለመረጋጋት ሰፍኖባት "ለስልታዊ ዘረፋ" ተዳርጋለች። 

"ላለፉት ሶስት ዓመታት የማዕከላዊ አፍሪቃ ቁልፍ አጋር የሆኑት የአውሮጳ ኅብረት፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ በአንዳንድ ምዕራባውያን ኃያላን ጫና የበጀት ድጋፋቸውን አቋርጠዋል። በዚህም ቀጣዊ እና ስልታዊውን የኃይል ትግል ለመደገፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን አሳይተዋል" ያሉት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ክሳቸው መገናኛ ብዙኃንን ጭምር የተመለከተ ነበር።

"የአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የሐሰተኛ መረጃ እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ቁርጠኛ ባለወረቶችን በማሸሽ መንግሥት በትምህርት፣ በግብርና፣ በኢነርጂ፣ በመጓጓዣ እና በጤና ዘርፎች ሥራዎች ለማከናወን ያለውን ሐብት እና ዕድል ነጥቀዋል። በዚህም ምክንያት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሕዝቦች ታጋቾች ናቸው" ሲሉ ተደምጠዋል። 

የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ፉዋስቲን አርካንጅ ቱዋዴራ
የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ፉዋስቲን አርካንጅ ቱዋዴራ በዶሐው ስብሰባ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ለገጠማት ቀውስ ጣታቸውን በስም ሳይጠቅሱ "አንዳንድ" ባሏቸው ምዕራባውያን አገራት እና ኩባንያዎች ላይ ቀስረዋል። ምስል Präsidentschaft der Republik Ruanda

ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ላለፉት አስርት ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት በተጣለባት የጦር መሣሪያ ግዢ ማዕቀብ ሥር ትገኛለች። ፕሬዝደንቱ በጦር መሣሪያ እና በዳይመንድ ንግድ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ይሻሉ። ለዚህም የዶሐው ስብሰባ ተሳታፊዎችን ድጋፍ ጠይቀዋል። ይሁንና አገሪቱ የአውሮጳ ኅብረት ማዕቀብ ከጣለበት ቫግነር የተባለ የሩሲያ ወታደራዊ ቅጥረኛ የግል ኩባንያ ጋር ያላት ግንኙነት ጥርስ ውስጥ ከቷታል። 

የተባበሩት መንግሥታት 77ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝደንት ቻባ ኮሮሺ እንዳሉት ግን ማዕከላዊ አፍሪቃን  እረፍት የነሳት ግጭትበሌሎች አገሮች ጭምር ተጽዕኖ ያሳደረ ጉዳይ ነው። ቻባ ኮሮሺ "ወረርሽኙ ከመቀስቀሱ በፊት እንኳ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትንሹ ያደጉ አገራት ግጭቶች የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ተጽዕኖዎችን በሚያባብሱ ግጭቶች ውስጥ ነበሩ። የዚያኑ ያክል አሳሳቢ የሚሆነው ደግሞ በዚህ አስር ዓመት መጨረሻ የውኃ ፍላጎት ከአቅርቦቱ በ40 በመቶ የላቀ ይሆናል። በ2030 ብዙ መሠራት እንዳለበት ግልጽ ነው" ሲሉ ተናግረዋል። 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “በትንሹ ያደጉ” በሚላቸው 46 አገራት 1.1 ቢሊዮን ሕዝብ ይኖራል። ይኸ ማለት ከዓለም ሕዝብ 14 በመቶው የእነዚህ አገራት ነዋሪ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የሰነዷቸው መረጃዎች ድህነት ግፋ ሲልም ረሐብ በገራቱ መበርታቱን የሚያሳዩ ናቸው።

በቀን በአማካኝ ከ1.9 ዶላር ወይም ከ102 ብር በታች በሆነ ገቢ ሕይወታቸውን የሚገፉ እና እጅግ ደሐ ከሚባሉ መካከል ግማሹ “በትንሹ ያደጉ” በተባሉ አገራት እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ጉባኤ (UNCTAD) ይፋ ያደረገው ሰነድ ይጠቁማል። አገራቱም ከዓለም ኤኮኖሚ ያላቸው ድርሻ 1.3 በመቶ ብቻ ነው።

ጉባኤው የዶሐው ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ “በትንሹ ያደጉ” በሚባሉት አገሮች ከሚኖሩ ሰዎች 37 በመቶው የምግብ ማብሰያ ቴክኖሎጂዎች እንደሌለው፤ 65 በመቶው ደግሞ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደማያገኝ ያሳያል። በጎርጎሮሳዊው 2021 ከመላው ዓለም ሕዝብ 768 ሚሊዮን የተመጣጠነ ምግብ እጦት ገጥሞት ነበር። ከዚህ ውስጥ 34 በመቶው “በትንሹ ያደጉ” በሚባሉት አገራት የሚኖር ነው። ከእነዚህ 46 አገራት ዜጎች 22 በመቶው ንጽህናው የተጠበቀ የመጸዳጃ አገልግሎት የለውም፤ 33 በመቶው ደሕንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውኃ አገልግሎት አያገኝም። እነዚህ ቁጥሮች 46ቱ አገሮች “በትንሹ ያደጉ” ከሚባሉ ይልቅ ደሐ የሚለው የበለጠ እንደሚገልጻቸው ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። 

 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “ዛሬ በማደግ ላይ የሚገኙ 25 አገራት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆን ገቢያቸውን የሚያውሉት ትምህርት ቤት ለመገንባት፣ ሕዝቦቻቸውን ለመመገብ፣ ለሴቶች እና ልጃገረዶች ዕድሎችን ለማስፋፋት አይደለም— ለዕዳ ክፍያ እንጂ" ሲሉ ተናግረዋል። ምስል Karim Jaafar/AFP/Getty Images

ከተደራራቢ ቀውሶች ግብግብ የገጠሙ የደሀ አገራት መሪዎች በጉባኤው መፍትሔ ያሻዋል ብለው በተደጋጋሚ ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ የብድር አከፋፈል ሽግሽግ ነው። የናጠጡትን በአባልነት ያቀፈው የኤኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት (OECD) መረጃ እንደሚያሳየው በጎርጎሮሳዊው 2021 ምዕራባውያን አገራት 185 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እና ብድር ሰጥተዋል። ለደሐ አገራት የሚሰጠው የልማት እገዛ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ከሚከተላቸው መንገዶች አንዱ ነው። ይሁንና "በትንሹ ያደጉ" የሚባሉት አገሮች በተሰጣቸው ድጋፍ ይኸ ነው የሚባል ለውጥ አላሳዩም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለእነዚህ ደሐ አገሮች የተሻለ የንግድ ዕድል እና ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ገንዘብ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት "በትንሹ ያደጉ አገሮች" የተባለውን ቡድን ቢፈጥርም የየአገራቱ መሪዎች እና ሚኒስትሮች እንደሚሉት ግን ችግሮቻቸው እየተደራረቡ በርትተዋል። የከባቢ አየር ለውጥ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተራዘመ ዳፋ እና በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ሰበብ የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ መናር የደሆቹን ዕዳ አባብሶታል።

“ዛሬ በማደግ ላይ የሚገኙ 25 አገራት ከ20 በመቶ በላይ የሚሆን ገቢያቸውን የሚያውሉት ትምህርት ቤት ለመገንባት፣ ሕዝቦቻቸውን ለመመገብ፣ ለሴቶች እና ልጃገረዶች ዕድሎችን ለማስፋፋት አይደለም— ለዕዳ ክፍያ እንጂ" ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጉዳዩ መፍትሔ እንደሚሻ በመድረኩ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ