1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣት ስራ አጥነት በሀዋሳ

ዓርብ፣ ጥር 27 2014

በኢትዮጰያ የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ በአነስተኛ የሥራ ፈጠራዎች ለሚንቀሳቀሱ ወጣቶች መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየገለፀ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በመንግሥት ተቋማት የሥራ ቅጥር ማግኘት እጅግ አዳጋች ነው የሚሉት ወጣቶች ከዛ ይልቅ በወጣቶች በተመቻቸው የሥራ ፈጠራ እድል አማካኝነት ለመደራጀት መሞከራቸውን ይናገራሉ፡፡

https://p.dw.com/p/46WZb
Äthiopien Hawassa | Jungendlich suchen Arbeit
ምስል hewangizaw Wegayehu/DW

ወጣት ስራ አጥነት በሀዋሳ

ከፌዴራሉ የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በኢትዮጲያ የሥራ አጥ ዜጎች ቁጥር ከ10 ሚሊዮን ተሻግሯል፡፡ በየዓመቱም እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ወጣቶች ሥራ ለመሥራት ወደሚያስችላቸው የእድሜ ክልል ይቀላቀላሉ፡፡ በተለይም ሀዋሳን በመሳሰሉ የአገሪቱ ትላልቅ ከተሞች በአማካኝ ከ23 እስከ 25 በመቶ የሚሆነው ከተሜ ቋሚ የሚለው መተዳደሪያ እንደሌለው ነው የሚነገረው፡፡ይህን ዘገባ ለመስራት በሀዋሳ ከተማ እምብርት ላይ በአንድ የመንገድ ዳር የሥራ የማስታወቂያ ቦርድ አቅራቢያ ምልከታ አድርጌያለሁ ፡፡ በዚህ ሥፍራ እጅብ ብለው የቆሙ ወጣቶች በማስታወቂያ ሠሌዳው ላይ ክፍት የሥራ ቦታዎችን ይመለከታሉ፡፡ በዚሁ ሥፍራ ያነጋገርኳቸው ወጣቶች የኮሌጅ ትምህርታቸውን ቢያጠናቅቁም ሥራ ማግኘት ግን አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልፀውልኛል፡፡በኢትዮጰያ የሚታየውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ በአነስተኛ የሥራ ፈጠራዎች ለሚንቀሳቀሱ ወጣቶች መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየገለፀ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በመንግሥት ተቋማት የሥራ ቅጥር ማግኘት እጅግ አዳጋች ነው የሚሉት ወጣቶች ከዛ ይልቅ በወጣቶች በተመቻቸው የሥራ ፈጠራ እድል አማካኝነት ለመደራጀት መሞከራቸውን ይናገራሉ፡፡ ያም ቢሆን በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች በትውውቅ የሚሠራ በመሆኑ ሊሳካላቸው እንዳልቻለ ነው የገለፁት፡፡


ወ/ሮ አገረፂዎን አበባ በሲዳማ ክልል የሥራ ክህሎትና ኢንተርኘራይዞች ልማት ቢሮ ሃላፊ ናቸው፡፡ በአብዛኞቹ ወጣቶች ዘንድ ከሙያዊ የክህሎት ዘርፎች ይልቅ በንድፈ ሀሳብ ተኮር ትምህርቶች ማለፋቸው ለሥራ ፈላጊዎች ቁጥር ማሻቀብ ምክንያት እየሆነ ይገኛል ይላሉ ። ያም ሆኖ ቢሯቸው በዚህ ዓመት 110 ሺህ ሥራ ፈላጊዎችን በመለየት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የሚናገሩት ወይዘሮ አገረፂዎን በዚህም ቀደም ሲል በሥራ ፈላጊዎች ልየታ ላይ የሚታዩ አድሏዊ አሠራሮችንና መጠቃቀሞችን ለማስቀረት ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ቀደም ባሉት ጊዜያት የተለያዩ አደረጃጀቶችን ሲያዋቅር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በተያዘው ዓመት መግቢያ ላይ የሥራ ክህሎት ሚኒስቴር በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ በሚኒስቴር ደረጃ ያዋቀረው ተቋም ከሥራ ፈላጊው ዜጋ ሥፋት አንፃር ከበድ ያለ ሃላፊነት እንዲወድቅበት አድርጎታል፡፡
በያዝነው ሳምንት መጨረሻ በሀዋሳ ከተማ በተዘጋጀው የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ የተሳተፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል የሥራ አጥነት ችግር የዞረ ድምር ውጤት ነው ይላሉ፡፡ ያም ሆኖ አሁን የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ በአገር አቀፉ ደረጃ ለሚገኙ 1 ሺህ 800 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አዳዲስ የሥርዓት ትምህርት ቀረጻዎችን ጨምሮ የለውጥ ማሻሻያ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ በመንግሥት እየተወሰዱ ናቸው የተባሉትን የለውጥ ማሻሻያዎች በበጎ እንደሚመለከቷቸው ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም በመንግስት በኩል በቂ ድጋፍ መደረግ ይገባል ይላሉ፡፡ የሥራ አጥነት ችግር የሙያ ክህሎት ከሠለጠኑ ወጣቶች ይልቅ በንድፈ ሀሳባዊ ተኮር የትምህርት ዘርፍ ያለፉ ወጣቶች ይበልጥ ለችግሩ ተጋላጭ እንደሆኑ ይታመናል፡፡ የሲዳማ ክልል የሥራ ክህሎትና ኢንተርኘራይዞች ልማት ቢሮ ሃላፊዋ ወይዘሮ አገረፂዎን አበበ ቢሯቸው በተያዘው ዓመት ከሙያ ሠልጣኞች በተጨማሪ ለድግሪ ምሩቃን ትኩረት እንደሚሰጥ ነው የገለፁት፡፡በኢትዮጱያ አሁን ያለው የሥራ አጥነት ምጣኔ ከቦተ ቦታ አንፃራዊ ልዩነት እንዳለው ይነገራል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሥራ እድሎች እያሉ የሠራተኞች እጥረት የሚያጋጥምበትና በአንፃሩ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በቂ ሠራተኞች እያሉ የሥራ እድሉ የሌለበት ሁኔታ እንደሚታይ ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል ይጠቅሳሉ ፡፡ መሥሪያቤታቸው ይህን ልዩነት ለማጥበብ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የሠው ሐይል ሥምሪት ተግባራዋ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ ነው ሚኒስትሯ የገለፁት ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ