1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውጥረት ያጠላበት የሶማሊያ የጸጥታ ይዞታ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 23 2013

እሁድ ዕለት የፕሬዝደንት መሐመድ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ኃይሎች መደራደሩን ትተው በጠመንጃ ቃታ ሲፈታተሹ ዜጎች ያ ከዓመታት በፊት ሲያሸብራቸው የኖረው የጦር አበጋዞጥ የእርስ በርስ ውጊያ ዳግም የማገርሸቱ ምልክት አድርገው ነው የወሰዱት።

https://p.dw.com/p/3sneS
Somalia Gewalt zwischen Regierung und Opposition
ምስል Farah Abdi Warsameh/AP Photo/picture alliance

«የምርጫ መጓተት የፈጠረው ስጋት»

ሶማሊያውያን መሐመድ ፎርማጆ ይሏቸዋል። የሶማሊያው ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ የዳሮድ ንዑስ ጎሳ ከሆነው ከማርሃን ነገድ ነው የተወለዱት። እሳቸው የተገኙበት ማኅበረሰብ ጁባላንድ ውስጥ ትልቁ ጎሳ ነው። ቤተሰቦቻቸው የሶማሊያ የመጀመሪያ መሆኑ የሚነገርለት የሶማሊያ የወጣቶች ሊግ ደጋፊዎች ነበሩ። በሶማሊያ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበሩት መሐመድ በጎርጎሪዮሳዊው 1991 ዓ,ም የእርስ በርስ ጦርነት በሀገሪቱ ሲጀመር ይማሩባት በነበረችው ዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቁ። በቆይታቸውም በሪፐብሊካን ፓርቲ አባልነት ተመዝግበዋል። ከጎርጎሪዮሳዊው 2019 ነሐሴ ወር በፊት የአሜሪካ ዜግነት ቢኖራቸውም በይፋ ዜግነታቸውን መልሰው የሶማሊያ ዜግነታቸውን አጽንተዋል። የ59 ዓመቱ ሶማሊያዊ ፖለቲከኛ የታዮ ፓርቲ መሥራችና ሊቀመንበርም ናቸው። ከጎርጎሪዮሳዊው 2010 ኅዳር ወር ጀምሮ እስከ ቀጣዩ ዓመት ሰኔ ወር ድረስ ለስምንት ወር ገደማ ማለት ነው የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። በቀጣይም ከጎርጎሪዮሳዊው 2017 የካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮም የሶማሊያ ዘጠነኛ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጠዋል። ከያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የካቲት ስምንት ጀምሮ ይፋዊ የሥልጣን ዘመናቸው ቢያበቃም በጊዜያዊ ፕሬዝደንትነት በመንበራቸው እስከ ዛሬ ይገኛሉ። ፌደራል ፓርላማውም የሥልጣን ዘመኑ ባለፈው ታኅሣስ በማብቃቱ ሀገሪቱ አሁን ሕጋዊና በንቃት የሚንቀሳቀስ ብሔራዊ መንግሥት የላትም ማለት ይቻላል። በዚህ ምክንያትም በሶማሊያ ምርጫ አለመካሄዱ ውጥረትና ውዝግብ ፈጥሯል። የፕሬዝደንቱ የሥልጣን ዘመን በማብቃቱም የፑንትላንድ እና የጁባላንድ ፌደራል ግዛት ፕሬዝደንቶች እንዲሁም የእጩ ፕሬዝደንቶች ምክር ቤት የመሐመድ ፎርማጆን የሶማሊያ ፕሬዝደንት እውቅና ነፍገዋል።

መሐመድ ፎርማጆ ግን እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ምርጫው እስኪደረግ ድረስ የሥልጣን ዘመናቸው እንዲራዘም ሲሞግቱ ቆይተዋል። ቀደም ባሉት ወራት ምርጫው ሊመራባቸውን የሚገባ ደንቦችን ለመቅረጽ ውይይቶች ቢካሄዱም ያስገኙት ውጤት የለም። ውዝግቡ አድጎም በጦር ኃይሉ ውስጥ የፕሬዝደንቱ ደጋፊዎችና እሳቸውን ከሚቃወሙት ጎን የተሰለፉት መሣሪያቸውን አንስተው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በጦርነት ስትተራመስ ኖራ ለጥቂት ዓመታት መጠነኛ እፎይታ አግኝታ የነበረችው የአፍሪቃው ቀንድ ሀገር  ዋና ከተማ መቅዲሹ ላይ ሰሞኑን ለዳግም የእርስ በርስ ውጊያ ተፋጥጠዋል። ስጋት የገባቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም ጓዛቸውን እየሸከፉ ቤታቸውን ጥለው ሽሽት መጀመሪያቸው በዚህ ሳምንት ታይቷል። አብዲ ነጂብ ጋሪ ነጂ ነው። ፖለቲከኞቹ ለሕዝብ ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም ብለው ሲጋጩ ዜጎች ለችግር ተዳርገናል ይላል።

«በዚህ አስፈሪ ግጭት ተደናግጠናል። ለጊዜው ተኩስ የለም ሆኖም የተቀናቃኞቹ ወታደሮች በየቦታው በቅርብ ርቀት ስለሚገኙ በማንኛውም ሰዓት ዳግም ሊጀመር ይችላል። ፖለቲከኞቹ ለሕዝቡ ጥቅም ብለው አይደለም የሚፋለሙት፤ ለራሳቸው ብለው ነው። ጋሪ ነጂ ነኝ፤ በዚህ ግጭት ምክንያት በቂ ገቢ አላገኝም። አስፈሪ ነው።»

Somalia Gewalt zwischen Regierung und Opposition
ምስል Farah Abdi Warsameh/AP Photo/picture alliance

የስምንት ልጆች እናት የሆኑት አሾ ኖርም ከሞመት መሰንበት ብለው ልጆቻቸውን ይዘው መሰደድን መርጠዋል።

«በወታደሮቻችን መካከል የተነሳው ግጭት ከነልጆቻችን ቤታችንን ጥለን እንድንሰደድ አድርጎናል። የምንሸሸው ከውጭ ወራሪዎች ሳይሆን ከራሳችን ሰዎች ነው። በእጃችን ምንም የለም። በተባራሪ ጥይት ከምንሞት ቤታችንን ጥለን ከመሰደድ የተሻለ አማራጭ የለንም።»

እሁድ ዕለት የፕሬዝደንት መሐመድ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ኃይሎች መደራደሩን ትተው በጠመንጃ ቃታ ሲፈታተሹ ዜጎች ያ ከዓመታት በፊት ሲያሸብራቸው የኖረው የጦር አበጋዞጥ የእርስ በርስ ውጊያ ዳግም የማገርሸቱ ምልክት አድርገው ነው የወሰዱት። የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሀሰን ሼኽ መሐመድ እሁድ ዕለት የፎርማጆ ታማኝ ኃይሎች መኖሪያ ቤታቸው ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቢናገሩም መንግሥት ክሱን አጣጥሏል። እንደውም የተደራጁ ታጣቂዎች ሊያደርሱባቸው የነበረውን አደጋ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዳከሸፉም ገልጿል። በከተማዋ ያሉ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ቢዘጉም በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች ሕይወት እንደወትሮው መቀጠሏን የሚወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

በመቃዲሹ ዋና ጎዳናዎች ላይ በሁለት ጎራ ተከፍሎ የታየው የኃይል ፍተሻ በሀገሪቱ የተፈጠረውን አስጊ ሁኔታ ያንጸባርቃል ይላሉ በዓለም አቀፉ የቀውስ ሁኔታዎች ተከታታይ ቡድን የሶማሊያ ጉዳይ ከፍተኛ ተንታኝ ኦማር መሐመድ።

«ሶማሊያ ውስጥ የምንገኘው በጣም ውጥረት በሞላበት ሁኔታ ነው። ማብቂያ የሌለው በሚመስል መጓተት የምርጫ አዙሪት ውስጥ መጓተት አለ። የአሁኑ ፓርላማ እና አስፈጻሚው ክፍል በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሥልጣን ዘመናቸው አብቅቷል። ይኽ ደግሞ ለተቃዋሚው ወገን ትልቅ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።»

እንዲህ ያለው ውዝግብ የዛሬ 30 ዓመትም ቢሆን ሶማሊያን በጎሳ ግጭት አመሳቅሎ፤ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የከተተ እንደነበርም ኦማር መሐመድ አስታውሰዋል። ሶማሊያን መንግሥት አልባ አድርጎ ያጎሳቆላት ጦርነት መነሻው አምባገንን መሪ ለማስወገድ በሚል የተጫረው የጎሳ ግጭት ነበር። ኦማር መሐመድ እንደሚሉትም ያ ግጭት ትርምስ በሀገሪቱ እና ዜጎቿ ላይ ያስከተለው ቁስለት ዛሬም ገና አላገገም። እናም አሁን በዚቺው ልማደኛ ሀገር ተመሳሳይ ግጭት ከጀመረ ቀድሞ የታየው መከራ ሁሉ ዳግም መመለሱ እንደማይቀር ያሳስባሉ። በዚያም ላይ የሶማሊያ ጉዳይ ፖለቲካ ተንታኙ እንደሚሉት በዚህ መሀል አሸባብ ራሱን ሊያጠናክርም ይችላል። ምክንያቱን አሸባብን እንዲከላከል የሠለጠነው የሀገሪቱ የፀጥታ በሁለት ጎራ ተከፍሎ እርስ በራሱ ተፋጥጧል። እናም ኦማር መሐመድ አሁን የውጭ አደራዳሪ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ይሰጣሉ።

በሳምንቱ አጋማሽ ለተቀናቃኞቻቸው ዳግም የውይይት በር የከፈቱት መሐመድ አብዱላሂ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ የመቃዲሹ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ሲማጸኑ ታይተዋል። ፕሬዝደንቱ የሀገሪቱ ምክር ቤት አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ማረጋገጫ እንዲሰጥ እንደሚጠይቁ በመግለጽም በሀገሪቱ አደገኛ የፖለቲካ አመጽ የቀሰቀሰውን የእሳቸውን የሥልጣን ጊዜ ለሁለት ዓመት የማራዘም ዕቅድ እንደተውትም ይፋ አድርገዋል። የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ጎራ ለይወተው መታኮስ ከጀመሩ በኋላ የሥልጣን ዘመናቸውን ለሁለት ዓመት ያራዘሙት መሐመድ አብዱላሂ አንዳች መፍትሄ እንዲያቀርቡ ብዙ ተጠብቀውና ግፊቱ ጸንቶባቸው ረቡዕ ዕለት ምርጫው እንደሚካሄድ ገልጸው ለድርድር ዳግም ጥሪ አቅርበዋል።

Somalia Präsident Mohamed Abdullahi Mohamed
ምስል Riccardo Savi/Getty Images for Concordia Summit

«የሶማሊያ ፌደራላዊ መንግሥት በውይይት፤ ሰጥቶ በመቀበልና ድርድር ያምናል እነዚህም ወሳኝ አማራጮች መሆናቸውንም ይቀበላል። በመሆኑም መስከረም 17 ቀን 2020 ዓ,ም የተደረሰውን ስምምነት እና ምርጫውን በተመለከተ የባይደዋ ቴክኒካል ኮሚቴ ያቀረበውን ምክረ ሀሳብ በማክበር ወደ ውይይት ጠረጴዛ መመለስ ይሻል። በመሆኑን የመስከረም 17ቱ ስምምነት ፈራሚዎች በሙሉ የተጠቀሰውን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሥራ ላይ ለማዋል ባስቸኳይ በአንድነት እንድትሰበሰቡም ጥሪዬን አቀርባለሁ። »

ፕሬዝደንቱ አቋማቸውን ለመለወጥም ሆነ ለማለዘብ የተገደዱት ይደግፏቸው የነበሩ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ጓዶቻቸው ሳይቀሩ በጽኑ ከተቃወሟቸው በኋላ እንደሆነ ነው የተነገረው። የፕሬዝደንቱን የሥልጣን ዘመን ማራዘም አጥብቀው ከተቃወሙት አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሐመድ ሁሴን ሮቤ በተቀሰቀሰው ግጭት ማዘናቸውን በመግለጽ የጸጥታ ኃይሎች ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና የመቅዲሹ ነዋሪዎችን ደህንነት እንዲጠብቁ ተማጽነዋል። በፎርማጆ ላይ ጫናው በሀገር ውስጥ ብቻ አላበቃም።

መቃዲሹ የሚገኙት የብሪታንያ ኤምባሲና የአውሮጳ ሕብረት ልዑካን በጥቃቱ የተሰማቸውን ስጋት ሲገልጹ፤ በሶማሊያ የተመድ ተልዕኮ በበኩሉ «አመጽ መፍትሄ አይደለም» የሚል መልእክቱን በትዊተር አስነብቧል። በተፈጠረው ውጥረት ስጋት እንዳደረባቸው ያመለከቱት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ባለድርሻ አካላት ሁሉ ባስቸኳይ ድርድሩን እንዲጀምሩ ተማጽነዋል። በሁኔታው ስጋቱን የገለጸው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ማዕቀብና የይለፍ ክልከላን ጨምሮ አስፈላጊ ያላቸውን አማራጮች አዘጋጅቼ እየተጠባበኩ ሲል አስጠንቅቋል።

በዚህ ውዝግብ እና ፍጥጫ አደጋ ላይ የሚወድቀው ምርጫው ብቻ ሳይሆን ሶማሊያን እንደ ሀገር የመገንባቱ የዓመታት ሂደት ሁሉ ውኃ እንደሚበላው ነው የሚገመተው። በጎርጎሪዮሳዊው 1991 ዓ,ም ፕሬዝደንት መሐመድ ዚያድ ባሬ ከሥልጣን ከተወገዱ አንስቶ ሶማሊያ የተረጋጋ መንግሥት መመሥረት አልቻለችም። ከጎርጎዮሪዮሳዊው 2000 ዓ,ም ወዲህ መላ ሀገሪቱን ማስተዳደር የሚችል ሥልጣን ያለው የሽግግር መንግሥታት በተከታታይ ለመመሥረት ተሞክሮ ከሽፈዋል። የዛሬ ዘጠኝ ዓመት እያዘገመም ቢሆን የቀጠለው ሂደት ተቋማትን መሥርቶ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ በመቻሉ የሶማሊያ አዲስ የፌደራል መንግሥት ተመሠረተና ከ20 ዓመታት በኋላ ዓለም አቀፍ እውቅና አገኘ። ይኽም ሆኖ የሽግግሩ ሕገ መንግሥት ምሉዕ ባለመሆኑ ብዙ የመደራደሪያ ጉዳዮችና ክፍተቶች ነበሩበት።

በጎርጎሪዮሳዊው 2012 እና 2016 መካከልም የሶማሊያ ፌደራል ሪፑብሊክ ቅርጽ እየያዘ መጥቶ ለከፍተኛ የፖለቲካ ውይይቶች መንገድ ከፈተ። የሶማሊያን ውስጠ ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ፕሬዝደንት መሐመድ ፎርማጆ የተመቻቸውን የፖለቲካ ሜዳ ወደቀድሞው ገጽታው መልሰውታል በማለት ይከሷቸዋል። ድርጊታቸውንም ገና ባልጠናው የሶማሊያ ጊዜያዊ ሕገመንግሥት ላይ የተቃጣ ጥቃት አድርገው ነው የሚወስዱት። ለዚህም ነው ብዙ የተለፋበትን የሶማሊያ መንግሥት የመገንባት ሂደት በማበላሸት ተጠያቂ የሚያደርጓቸው። ለዚህ ኃላፊነት ለጎደለው ሙከራቸውም የመፍትሄው አካል መሆን አይችሉም በሚል ወደ ጎን እንዲገረጉ ሀሳብ የሚሰነዝሩም አሉ። የሶማሊያን ጉዳይ በቅርብ ከሚያጠኑት አንዱ ማቲው ብራይደን ሶማሊያን ከእርስ በርስ ግጭትም ሆነ ከአሸባብ ጥቃት ለመከላከል ለምታደርገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ በጀት መድቦ የሚረዳው የአውሮጳ ሕብረት በሀገሪቱ የተፈጠረውን አደገኛ ሁኔታ እንደየምርጫ ውዝግብ ብቻ ሳይሆን አደገኛ ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ቀውስ እንደሚያመጣ ገልጾ አቋሙን ሊያሳይ ይገባል ነው ያሉት። የሥልጣን ዘመናቸው አብቅቶ በራሳቸው መንገድ ለማራዘም የሞከሩት ፎርማጆንም ከእንግዲህ እንደተራ ዜጋ ካልሆነ በቀር ሥልጣን ላይ እንዳለ ፕሬዝደንት ሊቆጥራቸው አይገባም ሲሉም ይሞግታሉ። የእስከዛሬው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ፕሬዝደንት መሐመድ ሥልጣንን ወደ አንድ ግለሰብ ቁጥጥር ሥር ለማምጣት ባደረጉት ሙከራም ወደ ኋላ እንዲመለስ ሆኗል በማለትም አጥብቀው ወቅሰዋል። 

Somalia Gewalt zwischen Regierung und Opposition
ምስል Farah Abdi Warsameh/AP Photo/picture alliance

አሁን ፕሬዝደንት መሐመድ በደረሰባቸው ግፊትና ጫና ወደ ድርድሩ ፊታቸውን አዙረዋል፤ ምርጫም ባስቸኳይ እንዲካሄድ ዝግጁነታቸውን አሳውቀዋል። ተቃዋሚዎቻቸው በጥንቃቄ ጥሪያቸውን በአዎንታ የተቀበሉት መስለዋል። ፕሬዝደንታዊ እጩ የሆኑት የዋድጅር ፖለቲካ ፓርቲ መሪ አብዱራህማን አብዲሹኩር ምንም እንኳን ወደ ድርድር ተመለሱ ቢሉም ፎርማጆ ምን ለወደፊቱ ያሰቡት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም ነው የሚሉት። የፓርቲያቸው አቋምን ሲገልጹ፣ «ሁሉን አቀፍ ስምምነት ላይ መድረስ እንዲቻል ውይይቱ ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት ማካተት ይኖርበታል። በዚህም አስቸጋሪና አንገብጋቢ ለሚባሉ ጉዳዮች መፍትሄ ለማምጣት ይረዳል።» ብለዋል። በእሳቸው ግምትም ፕሬዝደንቱ ሥልጣናቸውን ለሁለት ዓመት ለማራዘም ያቀዱትን ከምር አልተውትም፤ እንደውም ከታዕታይ ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ጋር በመሻረክ ምክንያት ፈልገው በመስከረም የተደረሰውን ስምምነት የመጣል ድብቅ አጀንዳ ሳይዙ አይቀርም የሚል ስጋታቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል። ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ጉዳዩ ሰላማዊ ዜጎችንም ጥርጥር ውስጥ የከተተ ይመስላል። ሀሰን አሊ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ቡድን ለይቶ ተኩስ ሲጀመር ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ ከተገደዱ የመቃዲሹ ነዋሪዎች አንዱ ነው።

Somalia Mogadischu Selbstmordanschlag Polizei
ምስል Sadak Mohamed/AA/picture alliance

«በከተማዋ በእነዚህ ቀናት የሚሆነው ሁሉ በእውነት አለመታደል ነው። እንዲህ ያለው ነገር እንዳይደርስ መደረግ ነበረበት። ተራ ሰዎችን እና ትምህር ቤቶችና የንግዱን ዘርፍ ቸምሮ የሲቪል ተቋማትን ሳይቀሩ የነካ እንዲህ ያለው አመፅ ሊወገዝ የሚገባው ነው። ምርጫውን በተመለከተ መፍትሄ ያጣውን ጉዳይ ያስተካከለው በፖለቲካው ላይ የታየው አዲስ ለውጥና ተጨማሪ ጥቃት መቆሙ መልካም ዜና ነው። የማዕከላዊውን መንግሥት መሪዎችና የየክልሉ መንግሥታት ወደ ሰላማዊ ሽግግር በጋራ እንዲመጡ እጠይቃለሁ።»

የሶማሊያ ዜጎች ጎሳን አስቀድመው በፖለቲካው በሚሳተፉ የራሳቸው ሰዎች እምቢ ባይነት ለበርካታ ዓመታት የተፈጠሩባት ምድር ሲኦል ሆናባቸው ኖራለች። በቅርቡ ደግሞ እፎይታ አግኝተው ለመኖር እየጀመሩ ነበር። ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በማስተናገድ በምትታወቀው ሀገር ቀለሙን ገፍተውበት ወደትውልድ ሀገራቸው ተመልሰው ለተሻለ አስተዳደር ተስፋ የተጣለባቸው ፕሬዝደንት አሁኑ ለዳግም ግጭትና ስደት መንስኤ ሆነውበት ተጨንቋል። አሁንም ስለድርድር ቢወራም ቀን አልተቆረጠም። የሶማሊያም የነገ እጣ ፈንታ አለየለትም።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሀመድ