1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ  ጥሪ

ሰኞ፣ ሐምሌ 30 2010

የቤተ ክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በድርጊቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል። ሰሞኑን በሶማሌ ክልል 7 አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውን እና የካህናት ህይወት ማለፉ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ተነግሯል። መንግሥት ያለ አበሳው ለሚገደለው እና ለሚዘረፈው ህዝብ በአስቸኳይ እንዲደርስም ጥሪ ቀርቧል።

https://p.dw.com/p/32hNe
Äthiopien Synode |
ምስል DW/Getachew Tedla

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥሪ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፣በሶማሌ ክልል ርዕሰ ከተማ ጅጅጋ እና ሌሎች ከተሞች በህብረተሰቡ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ፣ ዘረፋ እና አብያተ ክርስቲያናት በቃጠሎ እንዲወድሙ መደረጉን እንዲሁም ሰዎችም መፈናቀላቸውን አወገዘች። የቤተ ክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በድርጊቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል። ባለፈው ቅዳሜ 7አብያተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸው እና ትናንትም ተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን እና የካህናት ህይወት ማለፉ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ተነግሯል። መንግሥት ያለ አበሳው ለሚገደለው እና ለሚዘረፈው ህዝብ በአስቸኳይ እንዲደርስም ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጥሪ አቅርበዋል። ከአካባቢው የመጡ የዓይን እማኝ ደግሞ ችግሩ ዛሬም እንዳልተወገደ እና ህጻናትን ጨምሮ ነዋሪዎች የሚበሉት እና የሚጠጡት እንደሌላቸው ተናግረዋል። ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ  የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሕመድ ሽዴን ጠቅሶ  እንዳስታወቀው፣ ክልሉ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የመከላከያ ሰራዊት እና የፌድራል ፖሊስ ወደ ክልሉ ገብቶ ሰላም እንዲያስከብር ታዟል።የአዲስ አበባው ወኪላችን ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ  ዝርዝር ዘገባ አለው።

ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ 
ኂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ