የትግራይ የጦር ጉዳተኞች ስሞታ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 25 2015በትግራይ ለሚገኙ ተሰናባች የሠራዊት አባላት አስፈላጊውን የሙያዊ ስልጠናና የድህረ ጦርነት ስነልቡናዊ የምክር አገልግሎት ተሰጥቷቸው ሊሰናበቱ እንደሚገባ የትግራይ ማሕበረሰብ አባላት ተናገሩ። አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ (DW) የሰጡ የተሰናባች እና በጦርነት የተጎዱ የሠራዊቱ አባላትን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት ወገኖች የሠራዊቱ አባላት በየጊዜው የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኙ ይገባል ብለዋል። ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር ዝርዝር ዘገባ አጠናቅሯል።
የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት ተግባራዊ እስኪሆን በየካምፑ የሚገኙ የጦር ጉዳተኞች የመድኃኒት፣ የምግብ እና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንገብ ሦስት ጊዜ ቅሬታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል። በቅርቡ ደግሞ ከሠራዊቱ የተቀነሱ አባላት ተገቢው ድጋፍ እና ማቋቋሚያ ይደረግልን ሲሉ በሰላማዊ ሰልፍ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
አማኑኤል ዓለማየሁ በ1986 ከሠራዊቱ የተቀነሰ ሲሆን አሁን በግል ሥራ ላይ ይገኛል። ካለፈው ልምዱ እና እንደ አንድ ሁኔታውን በቅርበት እንደሚከታተል ሰው የሠራዊቱን አባላት ጥያቄ እንዲህ ይገልጸዋል።
"ከዚህ ቀደም ሰፍ የወጡት የሰራዊቱ አባላት ጥያቄ ተገቢ የብ፣ አልባሳት እና የሕክምና የመሳሰሉት ችግሮቻቸው እንዲፈቱላቸው የሚጠይቁ ናቸው። "
አቶ ሸዊት ገብረ እግዚአብሔር በመቐለ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ እና የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ አባል ናቸው። በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በኩል ሐብት በማሰባሰብ ለጦር ጉዳተኞቹ ምግብ እና አስፈላጊውን እርዳታ በማድረግም ይታወቃሉ።"የአካል ጉዳተኛ የሆኑ የሰራዊቱ አባላት ከፍተኛ የሕክምና አገልግሎት እና የምግብ አቅርቦት ችግር አባቸው።"የተሰናባቾቹ ጥያቄ ከተራ የኑሮ ድጎማ እስከ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት ሁኔታ ግልጽነት የጎደለው ስለመሆኑ አቶ አማኑኤል አስረድተዋል።
በቅርቡ የተካሄደው የተሰናባቾች ሰላማዊ ሰልፍ የህወሓት አመራሮችን ክፉኛ የተቸም እንደነበረም የዓይን እማኙ አቶ አማኑኤል ይናገራሉ።
" ሰልፈኞቹ ካሰሟቸው መፈክሮች ትልቅ ፖለቲካዊ ትጉም ያለው ነው። ለምሳሌ ካሰሙት መፈክር አመራሮቹ እኛን ለበረንዳ አዳሪነት ዳርገው እነሱ በዊስኪ ይራጫሉ፤ የሚል ይገኝበታል። ይህ አመራሩ ሃላፊነቱን እንዳልተወጣ የሚገልጽ ነው።"
አቶ አማኑኤል ከዚህም ሌላ በፕሪቶሪያው ውል መሰረት የሚደረጉ የሠራዊት መሰናበቶች ተገቢው ሙያዊ እና ስነልቡናዊ ስልጠናን ባካተተ መልኩ መሆን አለበት ባይ ናቸው።
በጉዳዩ ላይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ፕረስ ሰክረታሪ እና ከዚህ ቀደም ሰልፈኞቹን በአካል አነጋግረዋቸው የነበሩትን አቶ አማኑኤል አሰፋን አነጋግረናቸዋል። እንደእሳቸው አገላለጽ «ከዚህ በፊት የአካል ጉዳተኞች ያነሱዋቸው የምግብ እና ሕክምና ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ ነው፤» ሆኖም ግን «ምን ተፈታ ምን ቀረ ግን ዝርዝር መረጃ የለኝም» ብለዋል።
በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ ያካሄዱትን በተመለከተ ደግሞ « ሰልፈኞቹ ጦርነቱ እየተካሄደ በነበረበት ጊዜ በተለያዩ ጉዳቶች ተሰናብተው የነበሩ ሲሆን፤ አሁን በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት መሰናበት ለጀመሩት ትንሽ የስንቅ እና የጉዞ ገንዘብ እንደተሰጣቸው ሁሉ ለኛም ይሰጠን የሚል ጥያቄ ነው ያነሱት። ጥያቄው ትክክል በመሆኑ በየሚኖሩበት አካባቢ ተገቢው ድጋፍ ይደረጋል» ብለዋል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ