1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ገዢ ፓርቲ ፖለቲከኞች ዉዝግብ እንደቀጠለ ነዉ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 23 2016

በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት የተቋቋመው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደርን ለማዳከምና ለማፍረስ እየተሸረበ ነዉ ሲል አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ፅ/ቤት የአስተዳደሩን ውሳኔዎች በሚፃረሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። ህወሓት በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የተደረጉ ሹምሽሮችን ተቃውሟል።

https://p.dw.com/p/4k4Qx
ጌታቸዉ ረዳ፤  የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት
ጌታቸዉ ረዳ፤ የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ምስል Million H. Silase/DW

የትግራይ ገዢ ፓርቲ ፖለቲከኞች ዉዝግብ እንደቀጠለ ነዉ

የትግራይ ገዢ ፓርቲ ፖለቲከኞች ዉዝግብ እንደቀጠለ ነዉ

በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሰረት የተቋቋመው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደርን ለማዳከምና ለማፍረስ እየተሸረበ ነዉ ሲል አስተዳደሩ ትላንት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ፅሕፈት ቤት እንዳለው የአስተዳደሩን ውሳኔዎች በሚፃረሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።ህወሓት በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የተደረጉ ሹምሽሮችን ተቃውሟል። በትግራይ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው ልዩነቶች የሚያሰፋ መግለጫው ማሰራጨት እንዲቆም ጠይቀዋል። 

ህወሓት ላይ የተፈጠረው ክፍፍል እየተካረረ ባለበት በአሁኑ ወቅት፥ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የደቡብ ምስራቅ እና የሰሜን ምዕራብ ዞን አስተዳዳሪዎች መቀየራቸው ተከትሎ ሌላ ውዝግብ ተፈጥሯል። በተለይም የሰሜን ምዕራብ ዞን የህወሓት አመራሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ ከህወሓት የታገደው ሐይል በፀረ ዴሞክራሲ አካሄድ አመራሮች ከሓላፊነት እያነሳ ነው በማለት ተቃውመዋል። ይህ ተከትሎ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ትላንት ማታ የፅሑፍ መግለጫ ያወጣው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የተቋቋመው በትግራይ ያለው አስተዳደር ለማፍረስ በስም ባልጠቀሰው ሐይል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ አስታውቋል።

የተቋቋመው አስተዳደር ተግባራቱ እንዳይፈፅም ዕንቅፋት ሲፈጥር ቆየ ያለው ሐይል፥ አሁን ላይ በባሰ ሁኔታ ሕግና ስርዓት መሰረት አድርጎ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የሰጠው የስራ ምደባ ተግባራዊ እንዳይሆን የቆየ ኔትዎርኩ ተጠቅሞ እያደናቀፈ ይገኛል ሲል ከሷል። ይህንኑ ሐይል የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ያደረገው የስራ ምደባ ተቀባይነት የለውም፣ ሕጋዊ አይደለም የሚል መግለጫ ከማውጣት በዘለለ የዞንና ወረዳ አመራሮች በመሰብሰብ መንግስት እንዳይኖር እና ስርዓት አልባነት እንዲሰፍን እየሰራ ነው ሲል ወቅሷል። የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት የወለደው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ለማፍረስ እየተሞከረ ነው ያለው መግለጫው ይህ ተግባር ህዝቡ ሊታገለው ይገባል ሲል አክሎ ገልጿል። የመንግስት ውሳኔዎች ለማደናቀፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ላይም ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ትላንት ማታ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

መቀሌ ከተማ
መቀሌ ከተማ ምስል Million H. Selassie/DW

በዚህ የሁለቱ አካላት ልዩነት ዙርያ አስተያየታቸው ያጋሩን የሕግ ምሁሩ አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ አካሄዱ የፕሪቶርያው ስምምነት ለአደጋ የሚያጋልጥና የትግራይ ህዝብ ጥቅም ለጎን የገፋ ብለውታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ የሰጡት በትግራይ የሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መሪዎች የትግራይ ህዝብ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ባለበት፣ ተፈናቃዮች ባልተመለሱበት፣ የወጣቶች ስደት እና መከራ በበዛበት በዚህ ወቅት የትግራይ መሪዎች ይህንኑ ችግር ከመፍታት ይልቅ ወደልዩነት እና ክፍፍል መግባታቸውን እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል። ይህ ችግር ለመፍታት ደግሞ ከመሪዎቹ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው፣ ከሁለቱም በኩል መልካም ምላሽ ማግኘታቸው ጠቁመዋል። ይሁንና ልዩነት የሚያሰፋ እና ክፍፍል የሚፈጥር መግለጫ ከመስጠት እንዲቆጠቡ የሃይማኖት መሪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

ንቡረዕድ ጉደፋ መርሐ "መሪዎቻችን በገባችሁልን ቃል መሰረት፥ አባቶቻችን አትስጉ ወደ ግጭት አንገባም፣ ልዩነታችን በንግግር እንፈታለን ባላችሁት መሰረት ቃላችሁ እንድትጠብቁ አደራ በማለት፥ ልዩነቱ የሚያባብሱ መግለጫዎች ከመስጠት እንድትቆጠቡ ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ዛሬ በዓብይዓዲ በርካታ ህዝብ የተሳተፈበት ህዝባዊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም በአክሱም እና ዓድዋ ከተሞች ህዝባዊ ውይይቶች እንደሚቀጥሉ ተነግሯል። በቀጠለው ውዝግብ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እና ከህወሓት ወገን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ