1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወቅታዊ ሁኔታ

ሐሙስ፣ መስከረም 9 2017

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጋር በቀጣናዊ ሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን ተወያይተዋል። ኢጋድ በሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መከበር ላይ ግልጽ አቋም እንዳለውና ይህም የድርጅቱ አባል ሃገራት እና መንግሥታት መሪዎች ያረጋገጡት መሆኑን ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4krVW
የአፍሪቃ ቀንድ መሪዎች
የወቅቱ የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት መሪዎች ከአንድ ዓመት በፊት መቃዲሹ ሶማሊያ ውስጥ በተካሄደ ጉባኤ ላይ በሕብረት ቆመው። ፎቶ ከማኅደርምስል Ethiopian PM Office

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወቅታዊ ሁኔታ

 

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ግንኙነት መሻከር፣ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት፣ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት መቀዛቀዝ፣ የግብጽ በአካባቢው እያደገ የመጣ ግልጽ እንቅስቃሴ ሁኔታዎች እየተቀያየሩበት ያለው የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል ? 

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ የሶማሊያ ጉብኝት 

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ጋር ባደረጉት ሰሞነኛ ውይይት ሶማሊያ ቀጠናዊ መረጋጋትንና ደህንነትን በመቅረጽ ረገድ የምትጫወተውን ሚና ጠቅሰው ሀገሪቱ ወደ ዘላቂ ሰላም እና እድገት በምታደርገው ጥረት ድርጅቱ ከጎኗ እንደሚቆም፣ የሀገሪቱ መንግሥት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረትም መደገፉን እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

«የኢጋድ አቋም በጣም ግልፅ ነው። በጥር ወር የተካሄደውን የሃገራት እና የመንግሥታት መሪዎች ስብሰባ ካስታወሳችሁ የሶማሊያን ሪፐብሊክ ሉዓላዊነት፣ ግዛት እና አንድነት መከበርን በግልጽ ያስቀመጠ ነበር። ያ የየሃገራቱ መሪዎች ውሳኔ ነው። በነገራችን ላይ ኢጋድ በዚህ ጉዳይ ላይ የየሃገራት መሪዎችን እና መንግሥታትን በመጥራት የመጀመሪያው ድርጅት ነው። ስለዚህ ይህ በዓለም አቀፍ መርሆች እና እሴቶች መሠረት በጣም ግልጽ ስለሆነ በጣም ደስተኛ ነኝ።»

የአፍሪቃ ቀንድ ብሎም የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሁኔታ ወዴት እያመራ ነው? 

የአፍሪቃ ቀንድ ብሎም የምሥራቅ አፍሪቃ ቀጣና ሁኔታ ወዴት እያመራ ነው? ጉልህ የሚባል የፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ አለ ማለት ይቻላል? ካለስ ምንድን ነው? የሚለውን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩን ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ ጠይቀናቸው። «ባለፉት ሁለት ዓመታት ሊባል በሚችል መልኩ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እያየን ነው በቀጣናው። የጂኦ ፖለቲካው ሽኩቻ አካል ነው።» ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የግንኙነት መሻከርን ለማርገብ በቱርክ አሸማጋይነት የተጀመረው ጥረት የት ሊደርስ ይችላል? ተጨባጭ ውጤት የሚኖረው ነው ? 

« ከመነሻው ቱርክ በአደራዳሪነቷ ላይ ጥያቄ ይነሳል። ምክንያቱም ከሶማሊያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመለች። ምን ያህል ገለልተኛ ሆና ልታሸማግል ትችላለች ውጥረቱ እንዲረግብ የሚለውን ነገር ስናይ ውስንነቶችን አያለሁ።» ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ።

የኢጋድ ስበሰባ
የምሥራቅ አፍሪቃ በይነ መንግሥታት ኢጋድ ከአንድ ዓመት በፊት የሱዳንን ጉዳይ የተመለከተው የአዲስ አበባ ጉባኤ ከተሰብሳቢዎች በከፊልፎቶ ከማኅደር ምስል Office of the PM Ethiopia

የአፍሪቃ ሕብረት እና የኢጋድ ሚና ምን ሊሆን ይገባል?

በዚህ ረገድ የአፍሪቃ ሕብረት እና የኢጋድ ሚና ምን ሊሆን ይገባል? የሰሞኑ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ የሶማሊያ ጉብኝት በዚህ ላይ አወንታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ውጤት ይኖረው ይሆን ? ለሚለው ጥያቄያም፤

«እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢጋድን ስናየው ብዙ ንቁ ሆኖ አላየነውም። ፊት ለፊት በሚታይ መልኩ ድርሻውን የተወጣ አይመስለኝም። ሃገራቱ ራሱ ተዓማኒ ነው ብለው ይቀበሉታል ወይ ኢጋድን? የአፍሪቃ ሕብረት ባለው ወቅታዊ ውጥረት ላይ ቀጥተኛ እና ንቁ የሆነ ተሳትፎ እያደረገ አይደለም። ይህ የመጀመርያው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የካይሮ ድንጋጌ ለአፍሪቃ ሃገራት የግዛት አንድነት የቀደመውን የቅኝ ገዢዎቹ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚል ውሳኔ አሳልፈዋል። እና በሃገራት የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ አለመግባት በሚለው ላይ የፀና አቋም ያለው ይመስለኛል።» ብለዋል።

የሶማሊያን ሉዓላዊነት እናከብራለ ሲባል ምን ማለት ነው? 

ኢትዮጵያም፣ ኢጋድም፣ ዩናይትድ ስቴትስም የሶማሊያንሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እናከብራለን ይላሉ። ይህ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ከተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት አንፃር ምን ማለት ነው? «ይህ ግልጽ ነው። በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ እውቅና አንሰጥም ነው። ለተፈራረሙት ስምምነት (ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ) እውቅና አንሰጥም ነው።»

እያደገ የመጣው የግብጽ ተጽእኖ

ግብጽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወቅታዊው የዚህ ቀጣና ጉዳይ ላይ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ምን ትርጉም የሚሰጠው ነው? የሀገሪቱ የስለላ አገልግሎት ኃላፊ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኤርትራ ጉብኝት ማድረጋቸው ከኢትዮጵያ አንፃር ምን እንድምታ አለው? 

«ግብጽ ይህንን ተከትሎ ተስባ መጥታለች። በአካባቢው ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿም በአካባቢውም ካሉት ሃገራት ጋር ጥሩ የሚባል ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖር አካባቢውን በሙሉ ጠላትነት ያለበት እንዲሆን ነው ያደረገችው እና የመክበብ፣ መክበብ ብቻ ሳይሆን አካባቢውንም ደግሞ ለኢትዮጵያ የተመቸ እንዳይሆን በማድረግ ኢትዮጵያን የማስጨነቅ፣ አስጨንቆ ደግሞ እሷ ወደምትፈልገው የድርድር እቅድ እንድትመጣ የማድረግ ስልት ነው እየተከተለች ያለችው።»

እየተካረረ የመጣውን የአካባቢው ሃገራቱ ሁኔታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው ተንታኞች ጉዳዩ ጦርነትን ሊያስከትል እንደሚችል ሥጋታቸውን ሲገልፁ፣ አካባቢው ካለው ዓለም አቀፍ ስልታዊ ጠቀሜታ አንፃር ጦርነት የሚታሰብ አይደለም ሲሉም የተለያዩ አስተያየቶችን ገልፀው ነበር።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ