1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርና የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ስምምነት

ማክሰኞ፣ የካቲት 26 2016

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር (ERCS) እና የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ለቀጣይ ሦስት ዓመታት አብሮ ለመሥራት የሚስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ ። ከ207 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደርግም ተገልጿል ።

https://p.dw.com/p/4dCDT
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር (ERCS) እና የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ለቀጣይ ሦስት ዓመታት አብሮ ለመሥራት የሚስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር (ERCS) እና የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ለቀጣይ ሦስት ዓመታት አብሮ ለመሥራት የሚስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ ። ምስል Seyoum Hailu/DW

«አብሮ የመሥራት ባህላችንን ያጠናክርልናል»

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር (ERCS) እና የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ለቀጣይ ሦስት ዓመታት አብሮ ለመሥራት የሚስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ ። በስምምነቱ መሰረት፦ በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር 2024 የበጀት ዓመት ብቻ ዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተለያዩ የምግብና ምግብ ነክ ድጋፍ የሚውሉ ከ207 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተገልጿል ። ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች ስምምነቱን ሲፈራረሙ በሰብአዊ አቅርቦት ዙሪያ ወደፊትም አብረው እንደሚሠሩም አመልክተዋል ።

በስምምነቱ ወቅት ለመገናኛ ብዙኃን ገለጻ የሰጡት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር (ERCS) ዋና ፀኃፊ አቶ ጌታቸው ተዓ፤ የሁለቱ ሰብአዊ ተቋማት ስምምነቱ በቀጣይ ሦስት ዓመታት እንዴት በትብብር አብሮ መሥራት እንደሚቻል የሚዘረዝርና የጋራ ትብብር እቅዶችን ያስቀመጠ ነው ብለዋል ። የሦስት ዓመታት ስምምነቱ በየበጀት ዓመቱ በሚመደብ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ የሰውን ሕይወት ለማዳንና ኑሮያቸውን ለማቃናት የሚስችሉ ሥራዎች ይሠሩበታልም ነው ያሉት ።

«ወደ 207 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ሥራ እንሠራለን ። ይህን ገንዘብ እነሱ ይሰጡናል ። በ2024 የምንሠራቸው አበይት ሥራዎች፦ ለተቸገሩ ወገኖች፤ ለተጠቁ ወገኖች በተቻለ መጠን የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን፤ እንዲሁም የቀጥታ የገንዘብ ድልድል ወይንም ገንዘብ ሥርጭት እናደርጋለን ። ይሄ ብቻም አይደለም ። አምቡላንስ እንገዛበታለን » ብለዋል ።

የሁለቱ ተቋማት የትብብር ታሪክ ብያንስ ለ45 ዓመታት የዘለቀ ነው

መሰል ውል በሁለቱ ሰብአዊ ተቋማቱ መካከል በየሦስት ዓመቱ የሚደረግ ነው ተብሏል ። የሁለቱ ተቋማት የትብብር ታሪክ ብያንስ ለ45 ዓመታት የዘለቀም ስለመሆኑም ነው የተጠቆመው ። «በጋራ የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ ፤ እነሱ ደግሞ በተናጥል የሚሠሯቸው ሥራዎች በርካታ ናቸው ። በተቻለ መጠን አብረን የምንሠራቸውን ሥራዎች ለማስፋት ነው እየጣርን ያለነው ። በተለይ በተለይ በተለይም በጦርነትም ይሁን፣ በግጭትም ይሁን በተፈጥሮ አደጋም ይሁን የተጠቁት ወገኖችን እና የባሰባቸውን ። በነገራችን ላይ አንድ ሰው ችግር ሲደርስበት ችግሩን ለመቋቋም ያለው ብቃት የተለያየ ነው » ብለዋልም አቶ ጌታቸው በስምምነቱ ወቅት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ ።

የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ  (ICRC) የኢትዮጵያ አስተባባሪ ኒኮላስ ቮንአፕክስ በፊናቸው በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ይህን ስምምነት ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር (ERCS) ጋር መፈራረም ያስፈለገው የትብበር ሥራዎችን ለመለየት ነው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር (ERCS) እና የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ለቀጣይ ሦስት ዓመታት አብሮ ለመሥራት የሚስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር (ERCS) እና የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ለቀጣይ ሦስት ዓመታት አብሮ ለመሥራት የሚስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ ። ምስል Seyoum Hailu/DW

«አብሮ የመሥራት ባህላችንን ያጠናክርልናል»

«ይህን የትብብር ስምምነት የተፈራረምነው ለቀጣይ ሦስት ዓመታት በጋራ መሥራት የምንችለውን ዝርዝር ሥራዎችን ለመለየት ነው ። ይህም ለዘመናት የቀጠለውን የጋራ ዓላማችን የትብብር ሥራችንን የሚያስቀጥልልን ነው ። በዚህም በየአገሪቱ አከባቢዎች አብሮ የመሥራት ባህላችንን ያጠናክርልናል በሚል ስምምነቱን በደስታ እንመለከተዋለን ። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የማኅበረሰብ አካላትን ለማገዝ ስምምነቱ ይረዳናል ። ለዚህ ነው ስምምነቱን አስፈላጊ ብለን የምንመለከተው፡፡ ስምምነታችን የተለያዩ ቦታዎችን ተደራሽ ከማድረግም በላይ አጠቃላይ ግባችንን በጋራ ማስፈጸም የሚያስችለን ነው፡፡ በዚህ ስምምነት በተቀመጠው ገንዘብ አስፈላጊ ሲሆን ለግጭትና ተፈጥሮ አደጋ ተጎጂዎች ምግብ እናቀርብበታለን ፡፡ የንጽህና እቃዎችን ማቅረብ፣ መድኃኒቶችን ለሆስፐፒታሎች ማቅረብ አለያም በግጭትና ድርቅ ምክንያት ከቀዬቸው የተፈናቀሉ  ወይም የተለያዩ ቤተሰብን መልሰን የምናቋቁምበት ሊሆን ይችላል» ብለዋል፡፡

የሰብአዊ ተቋማቱ የተለያዩ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ አስቀድሞ መሥራት የሚስችል አሠራር ስለመኖሩም ተጠቁሟል ። ዛሬ የተፈረመው ስምምነት በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ የሰው ልጅን የሚያሰቃዩ ችግሮችን ለመቋቋም የሚረዳ ተብሏልም ።፡ ባለፈው የጎርጎሳውያን ዓመት 2023 ብቻ በሁለቱ ተቋማት ትብብር ከ400 ሺህ በላይ ዜጎች በኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎች ተጠቃሚ ስለመሆናቸውም ነው የተነገረው ።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ