1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የመንግሥት ውዝግብ

ሐሙስ፣ የካቲት 2 2015

የኢትዮጵያ መንግሥት "ሀገራዊ መረጋጋትን ለመፍጠር እና የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ጠንካራ ሕግ የማስከበር እርምጃ" እንደሚወስድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለእሁድ ለተጠራው ሰልፍ "መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ" እንዲያደርግ አሊያም ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎችን በአግባቡ እንዲመለስ አሳስቧል።

https://p.dw.com/p/4NJHw
Äthiopien Addis Abeba | vierte Patriarch Äthiopisch-Orthodoxe Tewahedo-Kirche Abune Merkorios
ምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት "ጠንካራ የሕግ ማስከበር" እርምጃ ለመውሰድ ቢያስጠነቅቅም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን ከዚህ ቀደም ባሰራጨችው አዋጅ እንደምትጸና አስታወቀች። የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን ያወጧቸው መግለጫዎች ከሁለት ሣምንታት በፊት የተከሰተውን ውጥረት የበለጠ አባብሰውታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ "የመስዋዕትነት ሰልፍ በሚል የሚደረገው ዝግጅት አጋጣሚውን ለዕኩይ የፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም የሚንቀሳቀሱ አካላት" ያቀዱት እንደሆነ ማረጋገጡን ገልጿል።

ሰልፉን "ከባለሀብቶች፣ ከፖለቲከኞች እና ከመንፈሳውያን የወጣት አደረጃጀቶች የተውጣጣ ቡድን" እያዘጋጁ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ከሷል። መግለጫው አክሎ "በዚህም ተግባር ሆን ብለው የተሰማሩትን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕግ የማቅረብ ተግባር ተጀምሯል" ብሏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ "መንግሥት ከሚያደርገው ጣልቃ ገብነት እና አፈና ወጥቶ ሕግ እንዲያከብር እና እንዲያስከብር የጠራንው የየካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ሰላማዊ ሰልፍ መንግሥት ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ እንድናከናውን መፍቀድ አለዚያም የጠየቅናቸውን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎቻችንን በአግባቡ እና አንድ በአንድ መመለስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ደግመን ደጋግመን ለማሳሰብ እንወዳለን" ብሏል።

አየር ጤና
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያወገዘው የኃይማኖት አባቶች ቡድን ወደ አየር ጤና ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ የሚል መረጃ ደርሶን ነው" ያሉ ምዕመናን ቤተክርስቲያኒቱን ከበው አምሽተዋል።ምስል Seyoum Getu/DW

ጉዳዩ "ቀይ መስመር" ተሻግሯል ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ሰልፍ እንደማይደረግ ገልጿል። "ሀገራዊ መረጋጋትን ለመፍጠር እና የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል መንግሥት ጠንካራ ሕግ የማስከበር እርምጃ" እንደሚወስድ በኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኩል ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል። 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ጴጥሮስ "አዋጅ አውጀናል። ሕገ-መንግሥቱ ይፈቅድልናል። እኛ በተመቻቸልን ጊዜ ሕዝባችንን ይዘን ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እንችላለን ብለን እናምናለን" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ሕገ መንግሥቱ "በዚህ ቀን አይፈቀድም። በዚህ ቀን ይፈቀዳል" የሚል ነገር እንደሌለው የገለጹት አቡነ ጴጥሮስ "ሕገ መንግሥቱ [የሚለው] ማሳወቅ ነው በአዋጅ አሳውቀናል" ሲሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን አቋም አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ከቀኑ ከ7፡30 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አየር ጤና ኪዳነምህረት አካባቢ ውጥረት ነግሶ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያወገዘው የኃይማኖት አባቶች ቡድን ወደ አየር ጤና ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ የሚል መረጃ ደርሶን ነው" ያሉ ምዕመናን ቤተክርስቲያኒቱን ከበው አምሽተዋል። 

Äthiopien Oromia | Nominierung des neuen Erzbischofs Aba Sawiros
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት መካከል እየተባባሰ የሔደው ውጥረት መነሾ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ደሙ ወረዳ ሀሮ በዓለወልድ ቤተ ክርስቲያን ጥር 14 ቀን 2015 የተሰጠ ሲመት ነው።ምስል Seyoum Getu/DW

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዙት የኃይማኖት አባቶች ቃል አቀባይ መምህር ኃይለሚካኤል ታደሰ ግን እቅዳቸው ወደ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ አገረ ስብከት የመሰማራት እንጂ ወደ አዲስ አበባ አየር ጤና ኪዳነ ምህረት መጓዝ እንዳልነበረ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በአካባቢው ተፈጠረ የተባለውን የህዝብ ተቃውሞ መስማታቸውን ገልጸው "መረጃውን ከየት እንዳመጡ አናውቅም" ሲሉ መልሰዋል።

በአየር ጤና ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን አካባቢ በርካታ የፀጥታ ኃይሎች የነበሩ ቢሆንም እስከ አመሻሽ ድረስ የተፈጠረ ግጭት እና የደረሰ ጉዳት የለም።

በዛሬው ዕለት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙት በሰበታ ወለቴ "የአካል ጉዳት እና ሞት" መድረሱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውቋል። ዶይቼ ቬለ ጉዳዩን ለማጣራት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።