1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ድርድር ለምን ፈቅ ማለት ተሳነው?

ረቡዕ፣ የካቲት 22 2015

የቡድን 20 አገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በሣምንቱ መጨረሻ የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ “በፍጥነት እንዲጠናቀቅ” ጥሪ አቅርበዋል። ወደ 27 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ዕዳ ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት በአከፋፈል ረገድ ሽግሽግ ለማድረግ ጥያቄ ያቀረበው በሐምሌ 2013 ቢሆንም እስካሁን ድርድሩ ፈቅ አላለም

https://p.dw.com/p/4O8Ed
Indien | Treffen der Finanzminister und Notenbankchefs der G20
ምስል India's Press Information Bureau/via REUTERS

የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ድርድር ለምን ፈቅ ማለት ተሳነው?

የቡድን 20 አገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች እና የማዕከላዊ ባንክ ገዥዎች ባለፈው ሣምንት ያካሔዱትን ስብሰባ ሲያጠናቅቁ በሕንድ በኩል እጅግ ለዘገየው የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ተስፋ የሚሰጥ ዜና ተሰምቷል። አገራቱ በበርካታ ጉዳዮች ላይ መክረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ለመግለጽ በመረጡት ቋንቋ ባለመግባባታቸው የጋራ መግለጫ ባያወጡም ዕዳ ላጎበጣቸው አገሮች መፍትሔ ለመሻት መስማማታቸውን የወቅቱ የቡድን 20 ሊቀ-መንበር ሕንድ በተናጠል ባወጣችው ሰነድ አስታውቃለች።

ሕንድ ይፋ ያደረገችው ሰነድ የቡድን 20 አገራት የኢትዮጵያ እና የዛምቢያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ “በፍጥነት እንዲጠናቀቅ” ጥሪ ያቀረቡበት ነው። የሕንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ኒርማላ ሲታራማን  “ተጋላጭ የሆኑ አገሮች የዕዳ ጫናቸው የሚቃለልበትን መፍትሔ ከቡድን 20 አገሮች እየጠበቁ ነው። አብዛኞቹ ለረዥም ጊዜ ጠብቀዋል። ብዙ ድርድር ካደረግን በኋላ ከዕዳ ጋር በተያያዘ አንድ የጋራ አቋም ላይ ልንደርስ እንችላለን። ስለዚህ አሁን ቡድን 20 ብዙ አገሮች እየገጠማቸው ያለውን የዕዳ ጫና ፈተና ለመቋቋም ዝግጁ ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

በሕንዱ ስብሰባ ጎን ለጎን የዕዳ ጫና ለበረታባቸው አገሮች ሊደረግ በታቀደው የአከፋፈል ማሻሻያ ላይ የሚመክር ውይይት አዘጋጅቶ የነበረው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ ቅዳሜ ለት ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበው ነበር። የካቲት 18 ቀን 2015 በተካሔደው በዚህ ስብሰባው ዓለም ባንክ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና በኢንዱስትሪ የበለጸጉት የቡድን ሰባት አባል አገራት ተሳትፈዋል።

የቡድን 20 አገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች እና የብሔራዊ ባንኮች ገዥዎች ስብሰባ በሕንድ
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ሊፋጠን እንደሚገባ ባለፈው ቅዳሜ ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበዋል። ምስል India's Press Information Bureau/via REUTERS

የቡድን 20 አባል አገራት የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ መፍትሔ እንዲበጅለት ጥያቄ ሲያቀርቡ ይኸ የመጀመሪያቸው አይደለም። ባለፈው ሕዳር 2015 በኢንዶኔዥያ ባሊ የተካሔደው የአገራቱ የመሪዎች ጉባኤ ሲጠናቀቅ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በሚደገፍ መርሐ-ግብር ሥር የኢትዮጵያ ዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ እንዲጠናቀቅ ማበረታቻ ሰጥተው ነበር። ይሁንና ሒደቱ ከነበረበት እስካሁን ፈቅ ማለት ተስኖት ቆይቷል።

ጉዳዩን ከሁለት ሣምንት በፊት በተካሔደው የአፍሪቃ ኅብረት ስብሰባ ላይ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአኅጉሪቱ አገሮች ያለባቸውን የውጭ ዕዳ ዘላቂ የሚያደርግ በቂ የአከፋፈል ሽግሽግ ሳይበጅ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተጎዳውን ኤኮኖሚ ለማነቃቃት እንደማይቻል ተናግረዋል። ዐቢይ በመድረኩ “ተገማች ዓለም አቀፍ የዕዳ ሽግሽግ ማዕቀፍ በፍጥነት” ሊበጅ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበው ነበር።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳፋ

ኢትዮጵያ በቡድን 20 አገራት የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ ጥያቄ ያቀረበችው በሐምሌ 2013 ነው። ለኢትዮጵያ የተቋቋመው በቻይና እና በፈረንሳይ ተባባሪ ሊቃነ-መናብርትነት  የሚመራ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ከመስከረም 2014 ጀምሮ ተከታታይ ስብሰባዎች ቢያደርግም ሒደቱ ግን የገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚለው "እንደሚጠበቀው ወደ ፊት አልተራመደም።"

የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ
ጉዳዩን ከሁለት ሣምንት በፊት በተካሔደው የአፍሪቃ ኅብረት ስብሰባ ላይ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአጉሪቱ አገሮች ያለባቸውን የውጭ ዕዳ ዘላቂ የሚያደርግ በቂ የአከፋፈል ሽግሽግ ሳይበጅ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተጎዳውን ኤኮኖሚ ለማነቃቃት እንደማይቻል ተናግረዋል። ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

በአሜሪካው አትላንቲክ ካውንስል የአፍሪቃ ማዕከል ባልደረባ አቶ ገብርኤል ንጋቱ “ኤኮኖሚያችሁ [የዕዳ አከፋፈል ማሸጋሸጊያ] እንደሚያስፈልገው ብናውቅም ጦርነቱ ካልቆመ እንዲህ አይነት ማሸጋሸጊያ ልናደርግ አንችልም” የሚል ምላሽ ለኢትዮጵያ መሰጠቱን ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይላት በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ ከተፈራረሟቸው ሥምምነቶች በኋላ ጦርነት ቢቆምም የዕዳ ሽግሽጉ የመንቀሳቀስ አዝማሚያ አላሳየም።

በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተመርምረው ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረብ ከጦርነቱ በኋላ ለዕዳ ሽግሽጉ በቅድመ-ሁኔታነት የተቀመጠ ጉዳይ ሆኗል። "መጀመሪያ ይኸ አልነበረም። ይኸ በጭራሽ አልነበረም” የሚሉት አቶ ገብርኤል “የአውሮጳ ኅብረት እና አሜሪካ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክ ያላቸውን ድምጽ ተጠቅመው ሁለቱ ተቋማት ወደ ብድር ማሸጋሸጉ እንዳይሔዱ አድርገዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ሰነድ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ መንግሥት ዕዳ በሰኔ መጨረሻ ከነበረበት 57.4 ቢሊዮን ዶላር በመስከረም ወደ 57.2 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል። የመንግሥት የውጭ ዕዳ በአንጻሩ 26.9 ቢሊዮን ዶላር ነው። የዓለም ባንክ ግን ይኸ የመንግሥት የውጭ ዕዳ 27.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይገምታል። ከኢትዮጵያ አበዳሪዎች ከፍ ያለ ድርሻ ያላት ቻይና ግልጽ መረጃ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሳትሆን መቅረቷ ለድርድሩ መጓተት ሌላው ምክንያት እንደሆነ አቶ ገብርኤል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አቶ ማሞ ምኅረቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን በጥር መጨረሻ በፓሪስ ባደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያ ዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጉዳይ ላይ ከፈረንሳይ ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ተናግረዋል። ፈረንሳይ እና ቻይና የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴን በተባባሪ ሊቀመንበርነት ይመራሉ። ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

“ቻይና ምን ያህል ብድር እንዳለ እና ብድሩ በምን አይነት ሥምምነት እንደተሰጠ አትገልጽም” የሚሉት አቶ ገብርኤል ጉዳዩ “ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ሌሎች ምዕራባውያን አገሮች በጣም አስቸጋሪ ሆኗል” ሲሉ አስረድተዋል። የድርድሩን ሒደት የሚያወሳስበው ሌላው ጉዳይ ኢትዮጵያ ከቻይና ለተበደረችው ገንዘብ በዋስትና ያስያዘችው ነገር ሊኖር ይችላል የሚለው ሥጋት ነው። ምዕራባውያን ተንታኞች “የዕዳ ወጥመድ” ሲሉ ይጠሩታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የዲፕሎማሲ ዘመቻ

የኢትዮጵያን ዕዳ አከፋፈል ለማሸጋሸግ የተጀመረው ድርድር ፈቅ ማለት ቢሳነውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት መፍትሔ ፍለጋ መጀመሩን የሚጠቁም የዲፕሎማሲ ዘመቻ ላይ ይገኛል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ ምክትላቸው ዶክተር እዮብ ተካልኝ እና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ማኅረቱ የተካተቱበት የከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑክ ባለፈው ሣምንት ወደ ቤጂንግ ባቀናበበት ወቅት ከቻይና ቁልፍ የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች እና አበዳሪዎች ጋር ተገናኝቶ ተወያይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸውን አስከትለው ባለፈው ወር ወደ ፓሪስ ብቅ ሲሉ መወያያ ከነበሩ ጉዳዮች እንዱ ይኸው የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጉዳይ ነበር። የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ የኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ተባባሪ ሊቀመንበር ከሆነችው ከፈረንሳይ ባለሥልጣናት ጋር የተደረገ ውይይት "ፍሬያማ" እንደነበር ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

አቶ ማሞ “ፍሬያማ” ያሉት ውጤት በተጨባጭ መቼ እንደሚታይ ለጊዜው የሚታወቅ ነገር የለም። የኢትዮጵያ ሹማምንት ወደ ፓሪስ እና ቤጂንግ ያደረጓቸውን ጉብኝቶች በቅርበት የተከታተሉት አቶ ገብርኤል ግን አዎንታዊ ውጤት ይጠብቃሉ።  አቶ ገብርኤል ኢትዮጵያ ያላት “ምርጫ ቻይና እና ፈረንሳይን በዲፕሎማሲው መስክ መጎትጎት ነው” የሚል አቋም አላቸው።

ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ያቀረበችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ጎምርቶ ወለድ የሚከፈልበትን ጊዜ ከ2024 ወደ 2029 ወይም 2030 እንዲራዘም የቦንዱ ባለቤቶች ሐሳብ ማቅረባቸውን ሬውተርስ ባለፈው ሳምንት ዘግቧል። ይኸ ቦንድ 6.625 በመቶ ወለድ የሚከፈልበት ሲሆን ለሽያጭ የቀረበው በሕዳር 2007 ነበር። ቦንዱ በሚቀጥለው ዓመት ሲጎመራ ኢትዮጵያ ለባለቤቶቹ ብድሯን ከነወለዱ በውጭ ምንዛሪ መክፈል ይጠበቅባት ነበር። ይሁንና የቦንዱ ባለቤቶች የሚጎመራበትን ጊዜ ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት ገደማ ለማራዘም ሐሳብ ማቅረባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። ይሁንና በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ለቀረበለት ምክረ ሐሳብ ምላሽ አልሰጠም።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ