1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርትራው ፕሬዝዳንት አማካሪ በአሜሪካ የተጣለባቸው ማዕቀብ ተነሳላቸው

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 4 2012

የኤርትራ ፕሬዝዳንት አማካሪ የማነ ገብረዓብ በአሜሪካ የተጣለባቸው ማዕቀብ ተነሳላቸው። በአሜሪካ ግምዣ ቤት የውጪ ንብረት ቁጥጥር ቢሮ በትናንትናው ዕለት የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪ ከተካተቱበት የሶማሊያ ማዕቀብ ስማቸው መሰረዙን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/3f9r5
Eritrea Podiumsdiskussion Yemane Gebreab
ምስል DW/M. Y. Bula

የኤርትራ ፕሬዝዳንት አማካሪ የማነ ገብረዓብ በአሜሪካ የተጣለባቸው ማዕቀብ ተነሳላቸው። በአሜሪካ ግምዣ ቤት የውጪ ንብረት ቁጥጥር ቢሮ (OFFICE OF FOREIGN ASSETS CONTROL) በትናንትናው ዕለት የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪ ከተካተቱበት የሶማሊያ ማዕቀብ ስማቸው መሰረዙን አስታውቋል።

የማነ ስማቸው አሜሪካ በሚያዝያ 2002 ዓ.ም. በሶማሊያ ላይ በጣለችው ማዕቀብ ውስጥ የተካተተው በባራክ ኦባማ ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔ ነበር። ባራክ ኦባማ ፕሬዝዳንታዊውን ውሳኔ የፈረሙት በወቅቱ የሶማሊያ የጸጥታ ሁኔታ ማሽቆልቆል፣ አለመረጋጋት፣ የባሕር ላይ ውንብድና እና በጦር መሳሪያ የታገዘ ዘረፋ ለአሜሪካ ያልተለመደ እና ልዩ የብሔራዊ ደሕንነት እና የውጭ ፖሊሲ ሥጋት ሆኗል ከሚል ድምዳሜ ደርሰው ነበር።  

በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሶማሊያን ሰላም፣ ጸጥታ እና መረጋጋት አደጋ ላይ በሚጥል እንቅስቃሴ ተሳትፈዋል ተብለው በፕሬዝዳንታዊው ውሳኔ የተዘረዘሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ንብረቶቻቸው እንዳያንቀሳቅሱ እግድ ተጥሎባቸው ቆይቷል። ማዕቀብ የተጣለባቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ዝርዝር የተጠናቀረው በአሜሪካ ግምዣ ቤት ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጋር በመመካከር መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት ይፋ ያደረገው እና እርምጃውን የሚያብራራው ሰነድ ይጠቁማል። 

አል ሸባብን ጨምሮ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች እና መሪዎቻቸው እንዲሁም የተለያዩ ግለሰቦች በዚሁ የአሜሪካ ማዕቀብ ውስጥ ተካተዋል። ከእነዚህ መካከል ሐሰን አብዱላሒ ሔርሲ አል ቱርኪ የተባሉ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሶማሊያዊ ግለሰብ ይገኙበታል።

የአሜሪካ ግምዣ ቤት ማዕቀብ ከጣለባቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ዝርዝር ውስጥ የኤርትራው ፕሬዝዳንት አማካሪ የማነ ገብረአብ ስም መሰረዙን ዶይቼ ቬለ አረጋግጧል። 

የ69 አመቱ የማነ ከፕሬዝዳንቱ ቀጥሎ በኤርትራ ተደማጭነት ያላቸው ባለሥልጣን ናቸው። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ባደረጓቸው ጉዞዎች አማካሪያቸው የማነ ገብረአብ እና የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ኦስማን ሳሌሕ አብረዋቸው አብረዋቸው ነበሩ። 

እሸቴ በቀለ