የክረምቱ ዝናብ በአማራ ክልል ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል
ማክሰኞ፣ መስከረም 7 2017
በአማራ ክልል አምና ክረምት የጣለዉ ዝናብ ባስከተለዉ ጎርፍና የመሬት መደርመስ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 49ኝ መድረሱን የክልሉ አደጋ መከላከል፣ የምግብ ዋስትና ማስተባባሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።ኮሚሽኑ እንዳስታወቀዉ አደጋዉ ከ6ሺህ 360 በላይ ነዋሪዎች አፈናቅሏል፤ ከ27 500 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ንብረታቸው ወድሞባቸዋል።በአለፈው 2016 ዓም በአማራ ክልል በጎርፍ፣ መሬት መንሸራተትና በከባድ ዝናብ ምክንት 49 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፣ ከ6ሺህ 360 በላይ የሚሆኑት ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል፣ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን እንዳመለከተው ከ27 500 በላይ በሚሆኑት ነዋሪዎች ላይ ደግሞ በአደጋዎቹ ንብረታቸው የወደመባቸው ናቸው፡፡
ጎርፍ በ2016 ዓም በአማራ ክልል፣የአርሶ አደሮች አስተያየት
የዘንድሮው ክረምት በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች ጉዳት አድርሷል፣ በአማራ ክልልም የመሬት መንሸራተት፣ ጎርፍና ከባድ ዝናብ ጉዳት አስከትሏል፡፡ መኖሪያ ቤታቸውና ሰብላቸው በጎርፍ ከተጎዳባቸው ነዋሪዎች መካከል በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ አርሶ አደሮች የሚጠቀሱ ሲሆን የደረሰባቸውን ጉዳት ለዶቼ ቬሌ እንዲህ አስረድተዋል፡፡
“የክረምት ሰብላችን ሩዝ ነበር እርሱም በጎርፍ ወድሟል፡፡” ብለዋል አርሶ አደሮቹ፤ ከዚህ በተጨማሪም የግጦሽ መሬት ደለል በመልበሱ እንስሳቱን ለመመገብ እንደተቸገሩ ነው የተናገሩት፡፡
የዞን የአደጋ መከላከል ኃላፊዎች አስተያየት
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር ለዶይቼ ቬሌ እንደገለፁት በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ጎርፍ፣ ከባድ ዝናብና የመሬት መንሸራተት ጉዳት አድርሷል፡፡
እንደኃላፊው በሰሜን ወሎ ዞን በስድስት ወረዳዎች በሚገኙ 22 ቀበሌዎች ጎርፍ ከ1ሺህ 345 በላይ ሄክታር ማሳ ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ 5ሺህ 184 አርሶ አደሮችም በጎርፍ ሰበብ መፈናቀላቸውን አክለዋል፡፡ በመሬት መንሸራተት በ7 ቀበሌዎች 388 ሄክታር ማሳ ከጥቅም ውጪ ሆኗልም ብለዋል፡፡ 870 አባዎራዎችም የአደጋው ተጎጂዎች እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡
ክረምቱ በክልሉ ደቡብ ወሎ ዞንም በርካቶችን ማፈናቀሉና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሰኢድ ተናግረዋል፡፡
በዞኑ 13 ወረዳዎች በበረዶ፣ በጎርፍና በመሬት መንሸራተት ጉዳት ደርሷል ብለዋል ኃላፊው፡፡ በ4ሺህ 112 ሄክታር ማሳ ላ ተዘራ ሰብል በደረሱ አደጋዎች መበላሸቱን ገልጠዋል፡፡ በ53 ቀበሌዎች የሚኖሩ 14ሺህ 376 ሰዎችም ለጉዳት መጋለጣቸውን አቶ አሊ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ በቅርቡ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት 10 ሰዎች ህወታቸው ማለፉንና 2ሺህ 949 ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት ተናግረዋል፣ በደረሰው አደጋ 1ሺህ 775 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ ሰብልም ወድሟል ነው ያሉት፡፡ በአጠቃላይ በዞኑ 4 ወረዳዎች በናዳ፣ በመሬት መንሸራተትና በከባድ ዝናብ የ23 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስረድተዋል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስተያየት
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳሬክተር አቶ ብርሀኑ ዘውዱ በአማራ ክልል ጎርፍ ያስከተለውን ጉዳት ዘርዝረዋል፡፡
ጎርፍ በ9 ዞኖችና 14 ወረዳዎች በሚኖሩ ከ21 ሺህ በላይ በሚሆኑ ወገኖች ላይ ጉዳት ማስከተሉን አመልክተዋል፣ 560 ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል ብለዋል፡፡19 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው በጎርፍ ምክንት ማለፉን አቶ ብርሀኑ ገልጠዋል፡፡ ጎርፍን ለመከላከል በ2016 ዓ ም መንግስት ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የጎርፍ መቀልበሻና የመገደብ ስራዎችን ቢያከናውንም የክረምቱ ዝናብ ከባድ ስለነበር ችግሩን ሙሉ በሙሉ መከላከል እንዳልተቻለም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡
በአማራ ክልል የመሬት መንሸራተትም ባልተለመደ መልኩ በርከት ያሉ ጉዳቶች ማስከተሉን ዳይሬክተሩ ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል፡፡ ከ270 በላይ ቤቶችና ትምህርት ቤቶችም በደረሰው አደጋ መውደማቸውን ተናግረዋል፡፡
በ16 ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት መከሰቱን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ በ64 ቀበሌዎች በሚኖሩ 2ሺህ 270 ሰዎች በንብረቶቻቸው ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጠዋል፣ 2ሺህ 800 የሚሆኑት ደግሞ በአደጋው ምክንት ተፈናቀሉ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
“30 ሰዎችም በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡” ብለዋል፡፡
ኃይለኛ ነፋስና ከባድ ዝንብ በ3ሺህ 800 ሰዎች ላይ ጉዳት ሲያደርስ 3ሺህ የሚሆኑት ደግሞ መፈናቀላቸውን ነው አቶ ብርሀኑ ያስረዱት፡፡
እስካሁን ያለው መረጃ ከእጃቸው የደረሰው ብቻ መሆኑን ያስረዱት አቶ ብርሀኑ ተጨማሪ ጉዳቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ከተፈጥሮ አደጋው በተጨማሪ በተለያዩ ክልሎች በነበሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖች በአማራ ክልል ተጠልለው በመኖራቸው መንግስት፣ መንግስታዊ ልሆኑ ድርጅቶችና ግብረሰናይ ረጂ ተቋማት ሰብአዊ እገዛ እንዲያደርጉ ባለስልጣናቱ ጠይቀዋል፡፡
በአማራ ክልል የተረጂዎች ብዛት
በአማራ ክልል በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከ2 ሚሊዮን በላይ ወገኖች በየወሩ የእርዳታ እህል የሚሰፈርላቸው እንደሆኑ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከዚህ በፊት ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫቤ