1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለው ድብርት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 1 2013

በጀርመን በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመር ላይ ነው። እስካሁን በመላ ሀገሪቱ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 545,027 መድረሱ ነው የሚነገረው። በፍላጎት ምርመራ እንዲደረግላቸው የሚጠይቁ ሰዎች መብዛታቸውንም ሌላው አቅም ፈታኝ መሆኑም ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/3l6wn
Corona-Gipfel  I  Merkel und Ministerpräsidenten
ምስል Hayoung Jeon/Getty Images

«በጀርመን ያገረሸው የኮሮና ወረርሽኝ»

በጀርመን በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመር ላይ ነው። እስካሁን በመላ ሀገሪቱ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 545,027 መድረሱ ነው የሚነገረው። በፍላጎት ምርመራ እንዲደረግላቸው የሚጠይቁ ሰዎች መብዛታቸውንም ሌላው አቅም ፈታኝ መሆኑም ተገልጿል። ተሐዋሲው በስፋት እንዳይዛመት መንግሥት ካለፈው ሳምንት አንስቶ ለቀጣይ አራት ሳምንታት የደነገገው የሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ገደም የሚያደርገው ውሳኔም ለብዙዎች የሌላ በሽታ ምንጭ ሊሆን እንደሚችልም ጥናቶች አሳይተዋል።

«አስቸጋሪ መሆኑን አውቃለሁ። ሆኖም ግን አሁን ይህን በመጠኑ እናድርግ ወይም ያንን ብለን የምናበላልጥበት ወይም ደግሞ የጀርመንን የንጽሕና መጠበቂያ መመሪያዎች ብቻ ተግባራዊ እናድርግ የምንልበት ጊዜ ላይ አይደለንም። ይህ ከሆነ ተሐዋሲውን በግማሽ ልብ ነው ለመከላከል የምንንቀሳቀሰው።» የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኮቪድ 19ን ወረርሽኝ ዳግም ማገርሸት አስመልክቶ መንግሥት የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎችና የሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይ ለአራት ሳምንት የጣለውን ገደብ አስመልክቶ ጀርመናውያን ለሚያሰሙት ቅሬት የሰጡት ምላሽ ነው።  ባለፈው ከየካቲት ማለቂያ አንስቶ የኮቮድ 19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም ፃዕረሞቱን ባጠላበት ወቅት ጀርመናውያን የመንግሥታቸውን ቃል በመቀበል ክፉው ጊዜ ተግ እስኪል የወትሮ ልማዳቸውን በመተው የወሰዱት ርምጃ ሀገሪቱ የተሐዋሲውን ስርጭት በመቆጣጠር ብቃቷ በምሳሌነት እንድትጠቀስ ማድረጋቸው ይታወሳል። ተሐዋሲው እንደማንኛው የጉንፋን አይነት ጠንከር ያለ ጉንፋን ነውና ከመጠን ያለፈ ጥንቃቄ አያስፈልግም የሚሉ ወገኖች በአንድ በኩል፤ የለም ይህ ተሐዋሲ አደገኛ ነውና ጠንከር ያለ የጥንቃቄ ርምጃ ያስፈልጋል የሚሉት ደግሞ በሌላ በኩል ሆነው የሚያደርጉት ክርክር አብዛኛውን ኅብረተሰብ ግር ያጋባው ይመስላል። በዚህም ምክንያት ካለፈው ሰኔ ወር አንስቶ የሰዎች እንቅስቃሴም ሆነ ማኅበራዊ ግንኙነት ላይ ለወራት ተጥሎ የከረመው እገዳ መላላት ሲጀምር ብዙዎች ወደ ወትሮው የበጋ እረፍት ጉዞና መዝናናታቸው ተመለሱ። የሰሜኑን ንፍቀ ክበብ የክረምት ወቅት ተከትሎ በተሐዋሲው የሚያዙት ሰዎች ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨመረ መምጣቱ እንደገና ስጋት እንደገና የሰዎችን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ወደመገደብ ገፋ።

Deutschland Coronavirus Shutdown Lenbachhaus München
ምስል REUTERS

የጀርመን 16ቱም ፌደራል ግዛቶች በዚህ ስጋት በመያዛቸው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ለመፍትሄው መምከር ቀጠሉና ከሁለት ሳምንት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ ግንኙነቱና በእንቅስቃሴው ላይ ገደብ እንዲያደርግ ውሳኔ አሳለፉ። ከጥቅምት 23 ጀምሮ እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ,ም ድረስ ለአራት ሳምንት ምግብና መጠጥ ቤቶች፤ የምሽት ክበቦች፤ የሲኒማና ቲያትር ቤቶች ተዘግተዋል። ከቤት ውጭ ሰዎች የሚኖራቸው ማኅበራዊ መሰባሰብ ከሁለት ቤተሰቤት እንዳያልፍ ያም ከ10 ሰዎች በላይ እንዳይሰባሰቡ ታዝዟል። ላለፉት ስድስት ወራት በሕዝብ መጓጓዣዎችና በገበያ ሥፍራዎች ብቻ ተወስኖ የነበረው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አሁን በመንገድ ላይም ጭምር እንዲደረግ ተወስዷል። ሜርክል ይህ ከዚህ ከኅዳር ወር አያልፍ የሚል ተስፋ ነው የሰጡት፤ ያ ማለት ግን በታኅሣስ ከኮሮና በፊት የሚታወቀው የኑሮ ዘይቤ ይመጣል ማለት አይደለም።

«በፖለቲካው ረገድ ይህ ከኅዳር ወር እንዳያልፍ የምንችለውን ሁሉ እንሞክራለን። ይህ ማለት ግን ከታኅሣስ ወር ጀምሮ ወትሮ የተለመደውና ከኮሮና በፊት የነበረው ነፃ የሕይወት ዘይቤ ዳግም ይኖራል ማለት አይደለም። ሆኖም የጀርመን የንጽህና መጠበቂያ መመሪያ፣ ማናፈስ፣ እንዲሁም የኮሮና መተግበሪያ ተግባራዊ መደረጋቸው ይቀጥላል። ይህም ማለት በሚያሳዝን መልኩ አሁን ተመልሰን ወደመጣንበት የተሐዋሲው ስርጭት ደረጃ  በፍጥነት ደርሰን ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።»

ይህንንም እውን ለማድረግ ብዙሃኑ የኅብረተሰብ ክፍል የሚነገረውን ተግባራዊ በማድረግ የራሱንም ሆነ የሌላውን ሕይወት ማዳን እንደሚገባውም ነው መራሂተ መንግሥቷ ጥሪ ያቀረቡት። የተነገረውን ተግባራዊ ማድረግ ለጀርመናዊ ብርቅ አይደለም ኅብረተሰቡ ሕግና ሥርዓት አክባሪ እንደመሆኑ ባለፈው ዓመት ሚያዝያና ግንቦት ወር ሌላው ዓለም ከኮሮና ተሐዋሲ ፃዕረ ሞት ጋር ሲተናነቅ በዚህ ሀገር ሰዎች በየግላቸው በሚያደርጉት ጥብቅ ጥንቃቄ ክፉውን ቀን ማለፋቸው ታይቷል። የኮሮና ተሐዋሲ ይዞታ አስመልክቶ የጀርመኑ ሮበርት ኮኽ ተቋም ያወጣው መረጃ  እንደሚያሳየው ይህን መሰሉ የኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ላላ ባለባቸው ወራት በተለይም ከመስከረም ወር ጀምሮ ጀርመን ውስጥ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መሄዱን ነው። ያለፉትን ሰባት ቀናት አስመልክቶም በተለይ በብሬመን፣ በርሊን፤ በኖርድ ራይን ቬስትፋለን፤ ሄሰን፤ ባቫሪያ፤ ዛክሰን እንዲሁም ዛርላንድ ፌደራል ግዛቶች በኮሮና የተኢዙት ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ገልጿል።  ተሐዋሲው የተዛመተበትን መንገድም በአብዛኛው ሰዎች በግላቸው በሚያካሂዷቸው የተለያዩ ዝግጅቶችና ድግሶች ላይ በመሰባሰብ፣ በአዛውንቶች መጦሪያ ማዕከላት፤ በሥራ ቦታዎችና በሃይማኖት በአላት መሆኑንም ተቋም አመልክቷል። በዚህም ምክንያት ወደ ፅኑ ሕሙማን መታከሚያ ክፍል መግባት የሚያስፈልጋቸው ቁጥራቸው ሦስት እጅ ከፍ ማለቱን ነው ተቋሙ የገለጸው። አሁን የሚታየው በኮሮና ተሐዋሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥር የመጨመሩ ጉዳይም ብዙዎች የሕመም ስሜት ባይኖራቸውም ምርመራ ለማድረግ ወደሚመለከታቸው የህክምና ተቋማት መሄዳቸው አንዱ ምክንያት መሆኑ ነው የተነገረው። ይህም አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማትን አቅም እየተፈታተነ ነው። ኦሊቨር ሃርሰር ኢንግልስ ሃይም የሚገኘው የባዮሱንቲካ የጤና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

Deutschland Corona-Pandemie | Gesundheitsamt testet
ምስል Waltraud Grubitzsch/picture alliance/dpa

«አቅማችን ከዚህ በላይ አይችልም። ባለፈው ሳምንትም ለምርመራ የሚቀርብልን ጥያቄ ይቀንሳል ብንልም እንደዚያ አልሆነም። በዚህ ሳምንትም ተመሳሳይ አይሆንም ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»

ሮበርት ኮኽ ተቋም ባወጣው መረጃ መሠረት በትናንትናው ዕለት ጀርመን ውስጥ አዲስ በተሐዋሲው የተያዙ  12,097 ሰዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል። ይህም ተሐዋሲው በመላው ዓለም በወርሽኝነት ከተከሰተ ጀምሮ የተያዙትን ሰዎች ቁጥር 545,027 አድርሶታል። እስካሁንም 10,530ው በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። በማይንዝ ከተማ የዮሐንስ ጉተንበርግ ዩኒቨርሲቲ የተሐዋሲያን ተመራማሪው ቦዶ ፕላሽተር እንደሚሉት በኮሮና የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በዚሁ መጠን እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ከጥቂት ሳምንታት በኋላም ለጥንቃቄ ሲባል የተጣለው እገዳ መቀጠሉ ይበጃል።

«ተገቢው ምዘና ሳይደረግ በመጪው ታኅሣስ ከዚህ የተለየ ለቀቅ ያለ ነገር ሊኖር ይችላል ብዬ አላምንም። በእርግጥ ሁላችንም ይህ እንዲሆን ተስፋ እናደርጋለን፤ ሆኖም ዋና ጥያቄ አሁን የወሰድነው ርምጃ ውጤታማ ይሆናል ወይ እንዲሁም ከነአካቴው ተግባራዊስ ሆነዋል  ወይ የሚለው ነው። ከሦስት እና አራት ሳምንታት በኋላ ነው ሠርቷል ማለት የምንችለው።»

መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም ይህኑ ነው የሚሉት። በዚህ ሰሞኑን ተግባራዊ በተደረገው የሰዎች ማኅበራዊ መስተጋብር እቀባና የጥንቃቄ ርምጃ የኮሮና ተሐዋሲን የመዛመት ፍጥነት መግታት ከተቻለ ታኅሣስ ወር ላይ ይዞታው ለቀቅ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል።  

USA New York Coronavirus Krankenhäuser
ምስል picture-alliance/Zumapress/U.S. Navy/S. Eshleman

ለብዙዎች ግን ይህን ለመረዳትም ሆነ ለመቀበል ቀላል እንዳልሆነ እየታየ ነው። በተሐዋሲው የመያዝና እና የመታተም ጉዳይ ብቻይ አይደለም። የሚወሰደው ጥብቅ የጥንቃቄ ርምጃ ከቤተሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳልነበረ ማድረጉ፤ ጓደኞች ወይም ዘመዳሞች በአካል መጠያየቅ ማቆማቸው፣ የሥራ ህልውና ጉዳይ ወይም የገቢ መቀነስ ሁሉ የስጋታቸው ምንጭ እንደሆነ እየተናገሩ ነው። የማኅበራዊ መስተጋብር አጋጣሚዎች ሁሉ መዘጋታቸው በተዘጋ ቤት ውስጥ ለድብርት ዳርጎናልም ይላሉ።  በድብርት የሚሰቃዩት  ሰዎች ደግሞ ኮሮና ተሐዋሲን ሌሎች በሚፈሩት ልክ የሚያሰጋቸው አይደለም። ዛሬ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በኮሮና ምክንያት የተወሰዱት ርምጃዎች ለጭንቀት የዳረጋቸው 75 በመቶ ይሆናሉ። በኮሮና ምክንያት ሥራቸውን ከቤት ለመሥራት ከተገደዱት 80 በመቶው በቀን  በጣም ጥቂት እንደሚንቀሳቀሱ ነው የተናገሩት። በዚህም ምክንያት ከጠቅላላው ሕዝብ 48 በመቶው ለድብርት ህመም መጋለጡን ጥናቱ አመልክቷል።  በድብርት ለሚሰቃዩ ወገኖች ደግሞ ዋናው መፍትሄ አነጋጋሪ ሰው ከጎናቸው መኖሩ ነው። ኮሮና ባስከተለው ርቀትን የመጠበቅ ግዴታ ምክንያትም ሀኪሞችና የስነልቡና ባለሙያዎች በቪዲዮ እና በስልክ በሚያደርጉት ውይይት  እነዚህን ታማጂዎች ለመርዳት እየሞከሩ ነው። ዛሬ ይፋ የሆነው ጥናትም በዚህ መንገድ በሚሰጣቸው የማማከር አገልግሎት 82 በመቶ የሚሆኑት ደስተኞች ነን ማለታቸውን ጠቅሷል። እንዲያም ሆኖ ፊት ለፊት ተገናኝቶ የሚሰጠውን አግልግሎት በምንም መልኩ አይተካም ነው ያሉት። ለአንዳንዶቹ ግን በኮሮና ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ እገዳ በተደረገበት ወቅት ለቤተሰባችን በቂ ጊዜ ኖረን፤ የክረምቱ ቀዝቃዜ ወቅት ሲለወጥ ተፈጥሮም በዙሪያችን ሲፈካ፤ ጨለማውም ቀስበስ ሲገለጥ በፅሞና ለመከታተል ዕድል አገኘን በሚል በአዎንታዊነት እንደተቀበሉት ተናግረዋል። አሁን ወቅቱ በጀርመን የክረምትና የቅዝቃዜ ብሎም የገና ጀንበር በጊዜ የምትጠልቅበት ነው። ከውጪው ብርድ ቤት ውስጥ ያለው ሙቀት ቢመረጥም ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም እንዲል መጽሐፉ የኮሮና ተሐዋሲ ስጋት ታክሎበት ድብርት አሳሳቢ ሆኗል። 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ