የወባ በሽታ ስርጭት በወለጋ
ዓርብ፣ ጳጉሜን 1 2016
በምዕራብ ወለጋ ዞን 22 ወረዳዎች ውስጥ የወባ በሽታ መዛመቱን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡ በዞኑ በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አሁንም እጨመረ ቢሆንም በሰው ህይወት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መቀነሱን የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኃለፊ አቶ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ባለፉት ስድስት ሳምንት ወደ ጤና ተቋማት ከሄዱት 6 መቶ ሺህ ሰዎች መካከል ከ349ሺ በላይ ሰዎች በወባ መያዛቸው መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ኃላፊዉ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ወራት ሰባት ሰዎች ሞተዋል፡፡
የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ ተስፋፍተውባቸው ከነበሩት የምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች መካከል በተለይም ቤጊና ቆንዳላ የተባሉ ወረዳዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም ወባ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን ያነገጋርናቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በቆንዳላ ወረዳ የጸረ ወባ በሽታ ኬሚካል ርጭት ከተደረገ ወዲህ በሰው ህይወት ላይ የሚያደረሰው ጉዳት መቀነሱን የነገሩን አንድ የአካቢው ነዋሪ ጀምብላ እና ቆቦ በሚባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ግን የወባ መድሀኒት አቅርቦት ችግር በመኖሩ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡
‹‹ ሹራ ሎጲና ቆቦ ከሚባለው የቤጊ ወረዳ አካባቢዎች፣ከቆንዳ ወረዳ ደግሞ ጅምቢላ ቱዋምቢ እና ጉማ ከሚባሉ ቦታዎች ህጻናትን ጨምሮ ወባ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ በዚህ አካባቢ ጸጥታ ችግርም ስላሉ የመድሀኒት አቅርቦት በቂ አይደለም፡፡ ከባለፈው ዓመት ይልቅ ዘንድሮ የተሻለ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከአንድ በተሰብ እስከ 3 እና 4 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ነበር፡፡ በዚህ ዓመት የበሽታው ስርጭት አለ ነገር ግን የጉዳቱ መጠን ቀንሰዋል ብሏል፡፡‹‹
በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳም እንደዚሁ የወባ በሽታ ስርጭት መኖሩ የተነገረ ሲሆን በዚህ አካባቢ ደግሞ ከሌሎች ወረዳዎች የተሻለ የመድሀኒት አቅርቦት እንዳለ ተገልጸዋል፡፡ በወረዳው አንድ ያነጋገርናቸው ነዋሪም በርካታ ሰዎች በወባ እንደሚያዙ በመግለጽ በሰው ህይወት ላይ የሚደረሰው ጉዳት መቀነሱን አክልዋል፡፡
የምዕራብ ወለጋ ዞን የጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን ጣሴው ባለፉት ሁለት ወራት የኬሚካል ሪጭት በማዳረስ በወባ በሽታ የሚደረሰው ጉዳት መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ክረምት በዞን ደረጃ 7 ሰዎች ህይወት ማለፉንም የተናገሩት ሲሆን በ8 ወረዳዎችና የኬሚካል ርጭት መከናወኑን አብራርተዋል፡፡ በዞኑ ስር በሚገኙት 22 ወረዳዎች ወባ ስርጭት መኖሩን የተናገሩት አቶ መስፍን በአሁኑ ወቅት ወባ የሚደረሰውን ጉዳት በሁሉም አካባቢዎች ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር መቀነሱን ጠቁመዋል፡፡
‹‹በዚህ ዓመት ባጠቃላይ 694ሺ294 ሰዎች በወባ ተይዘው በጤና ተቋማት ህክምና ተደርጎላቸውል፡፡ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ደግሞ 691ሺ775 ሰዎች ወደ ጤና ተቋማት በመምጣት በተደረገላቸው ምርምራ 349ሺ94 ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸው ተረጋግጦ በጤና ጣቢያ እና ጠየና ኬላ ደረጃ ህክምና ተደርጎላቸዋል፡፡‹‹
በ2015 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ውስጥ የወባ በሽ ስርጭትከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች ቤጊ፣ቆንዳና ባቦ ጋምቤል ሌሎች ወረዳዎች ይገኙበታል፡፡ ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተነግረዋል፡፡ በዞኑ በሚስተዋለው ጸጥታ ችግር ምክንያት የጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሳይገቡ በመቆየታቸውን ወባና ተጓዳኝ በሽዎች በመስፋፋት በርካታ ሰው ህይወት ላይ ጉዳት አድረሰዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ