1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደመራ በዓል አከባበር በአዲስ አበባ

ሐሙስ፣ መስከረም 17 2016

በዋናው የመስቀል አደባባዩ ክብረ በዓል ላይ በልዩ ልዩ አልባሳት ያሸበረቁ ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መዘምራን፣ ዲያቆናትና ካህናት ፣ የሃይማኖቱ መሪዎች እንደ ደረጃቸው አሸብርቀው ፣ በያሬዳዊ ዝማሬ ፣ በወረብና መወድሶች ፣ በፀሎትና አኮቴት እንዲሁም በልዩ ልዩ ትምሳሌት ያላቸው መንፈሳዊ ትርዒቶች ታጅበው ፣ መስቀል አደባባይ ተከብሯል።

https://p.dw.com/p/4WvBl
መስቀል አደባባይ-አዲስ አበባ ደመራዉ ሲለኮስ
የደመራ በዓል አከባበር አዲስ አበባ-መስቀል አደባባይምስል Solomon Much/DW

አዲስ አበባ ዉስጥ ለደመራ በዓል ከፍተኛ የፀጥታ ቁጥጥር ነበር

የአዲስ አበባዉን የበዓላት አከባበር የተከታተለዉ ሰለሞን ሙጩ እንደዘገበዉ ትናንት የተከበሩት የመዉሊድና የደመራ በዓላትን የሁለቱም ኃይማኖት ተከታዮች ያከበሩት  በግጭትና ክፍፍሉ ምክንያት የበዓላቱ አከባበር ሥርዓት ይታወካል በሚል ሥጋትና ጥንቃቄ  ነዉ።ይሁንና በዓላቱ በሰላም መጠናቀቃቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ - ኃይል አስታውቋል።

የደመራ ክብረ በዓል 

የመስቀል ደመራበዓል ከዋናው የዓደባባዩ ሥነ ሥርዓት በተጨማሪ ምዕመኑ በየ ቤቱ እና ጎረቤቱ ሰብሰብ እያለ ደመራ እያደረገ አክብሮታል። ሰሞነኛው የችቦ ግብይትም ጎልቶ የተስተዋለ ነበር።
በዋናው የመስቀል አደባባዩ ክብረ በዓል ላይ በልዩ ልዩ አልባሳት ያሸበረቁ ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መዘምራን፣ ዲያቆናትና ካህናት ፣ የሃይማኖቱ መሪዎች እንደ ደረጃቸው አሸብርቀው ፣ በያሬዳዊ ዝማሬ ፣ በወረብና መወድሶች ፣ በፀሎትና አኮቴት እንዲሁም በልዩ ልዩ ትምሳሌት ያላቸው መንፈሳዊ ትርዒቶች ታጅበው ፣  ተከብሯል።

ቁጥራቸው የበዛ ነው ባይባልም የውጪ ሀገራት ጥቂት ጎብኝዎችም በሥነ ሥርዓቱ ላይ ታድመው ተመልክተናል።ምዕመኑ በፌዴራል ፖሊሶች የሚደረገውን ጥብቅ ፍተሻ አልፎ ወደ አደባባዩ ሲገባ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፀጥታ አካላት በተለይ የፌዴራል ፖሊሶች በዓሉን በማስተናበር ላይ ነበሩ።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት  መስቀል የትገኘበትን ታሪክ ተምሳሌት በማድረግ የሚከናወነው የደመራ በዓል ላይ የኢፌዴሪ ርእሠ ብሔር ሳኅለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ታድመዋል።

በዓሉ ስጋት ባይለየዉም ህዝቡ በዚሕ መልኩ አክብሮታል
ለደመራ በአል ድምቀት ከሰጡት መዘምራን በከፊልምስል Solomon Much/DW


የቅዱስ ፓትርያርኩ መልዕክት 

ክብረ በዓሉን አስመልክቶ ታትሞ በወጣውና ለምዕመኑ  በታደለው የቤተ ክርስትያኗ መጽሔት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት "አንድ ሁኑ ስንባል መለያየትን እየመረጥን እንታያለን፣ ሰላም ሁኑ ስንባል መጣላትን እንፈልጋለን፣ ታረቁ ስንባል እምቢ አንቀበልም እንላለን፣ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ስንባል በክንዳችን መመካትን እንመርጣለን። ታዲያ የመስቀሉ ቃል በየትኛው አእምሮአችን ነው ያለው? በሀገራችን ያለው ሀቅስ ይህ አይደለምን"? ሲሉ ጠይቀዋል።
ፓትርያርኩ በቤተ ክርስትያኗ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በተነበበው መልዕክታቸው  አክለው እንዳሉት "ተቀራርበንና ተስማምተን ይቅር ተባብለን በአንድነት ፣ በእኩልነት ፣ በሰላም እና በፍቅር እንኑር። በምድራችን ፍትሕ ፣ ርትዕ ይንገስ፣ ሰብዓዊ መብት ይከበር፣ የተበደለ ይካስ" የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስ ፓትርያርኩ በዚህ የደመራ ክብረ በዓል ላይ  አልታደሙም። ምክንያቱም አልተገለፀም። የባህልና ስፓርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳም የሰላም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ቤተ ክርስትያኗ ከገጠማት የውስጥ ክፍፍል በኋላ ያከበረችው የመጀመርያው የዓደባባይ በዓል 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የባህልና የሳይንስ ድርጅት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የመስቀል ክብረ በዓል ዛሬ እያከበረች ትገኛለች። በመላው ኢትዮጵያ ትናንት የተከበሩት የመስቀል ደመራ እና የመውሊድ በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ - ኃይል አስታውቋል።
ትናንት የተከበረው የደመራ ክብረ በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ባለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ከገጠማት የውስጥ መከፋፈል እና የቀኖና ጥሰት ያስከተለ ችግር በኋላ ያከበረችው የመጀመርያው የአደባባይ ክብረ በዓል ሲሆን በትግራይ ክልል ካሉት የሃይማኖቱ አባቶች ጋር ያለው ልዩነትም እስካሁን አልተፈታም።
ኢትዮጵያ አሁን ከምትገኝበት የሰላምና ፀጥታ መናጋት መነሻ በዓሉ ላይ ችግር እንዳይፈጠር የሚል ሥጋት በብዙዎች ዘንድ ሲደመጥ የነበረ ሲሆን በመላው ሀገሪቱ ትናንት የተከበሩት የመስቀል ደመራ እና የመውሊድ በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ - ኃይል አስታውቋል

የአዲስ አበባዉ የደመራ በዓል በከፊል
ደመራዉ ሲቀጣጠል፣ ምዕመኑ ከብቦ ሲመለከት አዲስ አበባምስል Solomon Much/DW

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር