1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀማል ኻሾግጂ አሟሟትና የአፍሪቃ አገሮች አቋም

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 17 2011

ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሞሪታኒያና ደቡብ ሱዳንን የመሳሰሉ የአፍሪቃ አገሮች የጀማል ኻሾግጂ አሟሟት ዓለም አቀፍ ትችት ላይ ለጣላት ሳዑዲ አረቢያ አጋርነታቸውን ገልጸዋል። ለተንታኞች ግን የአፍሪቃ መንግሥታት ከሚፈፅሟቸው ወንጀሎች አንፃር ድጋፋቸው አላስገረማቸውም። አገሪቱ ለአፍሪቃ የምትሰጠው ዳጎስ ያለ ዕርዳታና ብድር ሌላው ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ

https://p.dw.com/p/37GnS
Türkei Protest Journalist Jamal Khashoggi
ምስል picture-alliance/AA/M. E. Yildirim

ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሞሪታኒያና ደቡብ ሱዳን ሳዑዲን ደግፈዋል

የሳዑዲ አረቢያው ጋዜጠኛ ጀማል ከማል ኻሾግጂ በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ በሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ በአሰቃቂ ኹኔታ መገደሉ ከተሰማ በኋላ የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቶ ነበር። ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ የፈጠረውን ጉዳይ ለማቀዝቀዝ ሳዑዲ አረቢያ የተከተለችውን መንገድ ያደነቀው የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያለውን ቁርጠኝነት በመግለጫው አትቷል።

የጋዜጠኛውን አሟሟት ለማስተባበል በተደጋጋሚ ለጣረችው ሳዑዲ አረቢያ ድጋፉን የገለጸው ግን የደቡብ ሱዳን መንግሥት ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ያላትን አቋም በይፋ ባትገልጽም ጉዳዩ በተጋጋለበት ወቅት በሪያድ ከተማ በተካሔደው የባለወረቶች ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ምኒስትር ደመቀ መኮንን ታድመዋል። ምክትል ጠቅላይ ምኒስትሩ ከጋዜጠኛው ግድያ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ስማቸው ከሚነሳው የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ጎን ተቀምጠው ታይተዋል። 

Proteste in den USA nach Mord an Jamal Khashoggi
ምስል picture-alliance/newscom/K. Dietsch

ቱርክን ጨምሮ ከገልፍ አገሮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት እና ገለልተኛ አቋም ለመያዝ ስትታገል የምትታየው ሶማሊያ ለሳዑዲ አረቢያ አጋርነቷን የገለጸች የአፍሪቃ አገር ነች። የሶማሊያው ጠቅላይ ምኒስትር ሳዑዲ አረቢያን ከጎበኙ በኋላ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መግለጫ አውጥቷል። የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መግለጫ ሳዑዲ አረቢያ ያላትን ሚና ለማዳከም የሚጥሩ ያላቸውን ተችቶ አጋርነቱን ገልጿል።

ትንሺቱ ምሥራቅ አፍሪቃዊት አገር ጅቡቲ በበኩሏ ወንድም አገር ያለቻትን "የሳዑዲ አረቢያ ገፅታ ለማጠልሸት የሚደረግ የመገናኛ ብዙኃን ዘመቻ" እንደምታወግዝ አስታውቃለች። ሳዑዲ አረቢያ ጋዜጠኛው በቱርክ ቆንስላዋ መሞቱን፣ ግድያውም ቀድሞ የተቀነባበረ መሆኑን ከመግለጿ በፊት ሞሪታኒያ መግለጫ አውጥታ ሳዑዲ አረቢያን የኮነኑ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ሐሰተኛ ውንጀላዎች ስትል አጣጥላ ነበር። ለመሆኑ እነዚህ የአፍሪቃ አገሮች ለሳዑዲ አረቢያ እንዲያደሉ ያስገደዳቸው ምክንያት ምን ይሆን? በዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ መሰናዶ ገበያው ንጉሴ ጉዳዩን ይዳስሳል።  

ገበያው ንጉሴ

እሸቴ በቀለ