የጎሳ ግጭት በኢትዮጵያ
ሐሙስ፣ መስከረም 11 2010ኢትዮጵያ ለጎሳ ግጭት እንግዳ እንዳልሆነች የሚናገረዉ ፈረንሳዊዉ ጋዜጠኛ ረኔ ለፎር የተከሰተዉ ምንድነዉ የሚለዉ መታወቅ አለበት ባይነዉ።
«የጎሳ ግጭቶች ኢትዮጵያ ዉስጥ ከ1983ዓ,ም ወዲህ ህወሀት ስልጣን ይዞም ጭምር ይከሰታሉ። ግጭቱ በአርብቶ አደሮች መካከል ለግጦሽ ወይም ለዉኃ ይከሰታል፤ ወይም መሬት በማጣት ምክንያትም ግጭት ይኖራል። አሁን አዲሱ ነገር፤ ከ1983ዓ,ም ወዲህ ማለት ነዉ ለመጀመሪያ ጊዜ መደበኛ የታጠቁ ኃይሎች በጎሳ ግጭቶቹ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መግባታቸዉ ነዉ።»
ጋዜጠኛዉ የጠቀሳቸዉ የታጠቁ ኃይሎች የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ የሚባሉት መሆናቸዉን በመዘርዘርም በግጭቱ ለመሳተፍ የበቁት የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት ከአዲስ አበባ እና ከትግራይ በኩል በቂ ድጋፍ ስላላቸዉ ነዉ ሲልም ይደመድማል። 45 ሺህ ሠራዊት እንዳለዉ የጠቀሰዉ የሶማሌ ልዩ ፖሊስም ተጠሪነቱ በቀጥታ ለክልሉ ፕሬዝደንት መሆኑንም አመልክቷል ። ችግሩ በተፈጠረበት ስፍራ የሚገኙ ነዋሪዎችም በተደጋጋሚ ለዶቼ ቬለ የገለፁት የታጠቀ ኃይል በግጭቱ መሳተፉን ነዉ። የተፈጠረዉ እንዲጣራ ምንም እንኳን የአሜሪካን ኤምባሲ ግልፅ ምርመራ እንደረግ ቢጠይቅም ጋዜጠኛ ለፎር ግን ይህ እውን ሊሆን መቻሉን ይጠራጠራል። ይህን ለመረዳትም ችግሩ ከመሠረቱ እንዴት እንደተፈጠረ መረዳት እንደሚገባም ያስረዳል።
«ለምን ይህ ሁኔታ ተፈጠረ? የተፈጠረዉ የአዲስ አበባው ፌደራል መንግሥት ለሳምንትም እንበለዉ ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ መጫወት የሚገባዉን ሚና በአግባቡ ባለመጫወቱ ነው። የገዢ ፓርቲ ዋና ሚና ደግሞ ሕግ እና ሥርዓትን ማስጠበቅ ነዉ። እስካሁን ድረስ ግን አዲስ አበባ ይህን ማድረግ አልቻለም። ምክንያቱን አዲስ አበባ ላይ ያለዉ ማዕከላዊ ኃይል እጅግ ጥልቅ በሆነ መልኩ ተከፋፍሏል። ክፍፍሉ አራት ጎሳዎችን ባካተተዉ ገዢ ፓርቲ ዉስጥ ጎሳን ተከትሎ፤ የፖለቲካ ጥያቄዎችን አስመልክቶ እንዲሁም በተራ ስልጣን ሽኩቻ የተከፋፈለ ነዉ። እናም ይህ በዚህ መልኩ የተከፋፈለ ማዕከላዊ ኃይል የተፈጠረዉ ምን እንደሆነ የሚያሳይ ግልፅ ምርመራ ማድረግ ይችላል ብዬ አላስብም።»
ምንም እንኳን ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ የሁለቱ ክልሎች ኃላፊዎች እና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ስለጉዳዩ ሲናገሩ ቢደመጥም፤ የችግሩን ትክክለኛ መንስኤ ከመጥቀስ መቆጠባቸዉንም ጋዜጠኛዉ አመልክቷል። ከሀገር ዉስጥ የሚወጡ መረጃዎች የሚጠቁሙት የጎሳ ግጭቱ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ላይ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ነዉ። እናም ችግሩ እየተዛመተ ይመስላል። ይህን ለመግታት ምን መደረግ ይኖርበታል ለሚለዉ አሁንም ጋዜጠኛ ረኔ ለፎር።
«ትክክል ነው፤ በኦሮሞ እና ሶማሌም ሆነ በወልቃይት ምክንያት በትግሬ እና አማራ ክልል አካባቢ የሚታየዉ ውጥረት ሁሉ የመጣው በእኔ ዕይታ ለረዥም ጊዜ በቆየዉ የብሔራዊነት ጥያቄ ሰበብ ነዉ። በኢትዮጵያ አሁንም የብሔራዊነት ጥያቄው አልተፈታም። በእኔ እምነት እያንዳንዱ ብሔረሰብ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የተወከለበት ሥርዓት እና ሁሉም በፍትሀዊነት የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ተካፋይ የሚሆንበት መንገድ ገና ሊፈጠር ይገባል። የሚታየዉን የጎሳዎች ግጭት ለማስቆምም በአፋጣኝ መወሰድ ካለባቸዉ ርምጃዎች ቀዳሚዉ ይህ ነዉ።»
ግን አሁንም ጋዜጠኛ ለፎር ስልጣን ላይ የሚገኘዉ ገዢዉ ፓርቲ ኢህአዴግ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ፈቃደኛነት እና አቅሙስ አለዉ ወይ? ሲልም ይጠይቃል። አሁን የሚታየዉ የሀገሪቱ ሁኔታ ወዴት ያመራ ይሆን? የመጨረሻዉ ጥያቄ ነበር ለጋዜጠኛዉ ያቀረብኩት።
«ይህ ጥያቄ ለመመለስ አዳግች ነዉ። የተለያዩ ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፤ አንደኛዉ ሁኔታ፤ ኢህአዴግ ሊበታተን ይችላል፤ ሌላኛዉ ሁኔታ፤ የጎሳ ግጭቶቹ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ከፍ ብለዉ ፌደራል ስርዓቱ ሊንኮታኮት እና ሀገሪቱንም ሊለያይ ይችላል፤ ሌላዉ ደግሞ ኢህአዴግ የሀገሪቱ መንግሥት ሊገጥመዉ የሚችለዉን አደጋ በእርግጥ ሊረዳ እና ርምጃ ሊወስድ ይችላል። እናም መጥፎም ሆነ መልካም ሁኔታዎች የመፈጠር ዕድል አላቸዉ። እናም አሁን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረስን ይመስለኛል።»
የአሜሪካን ኤምባሲ መንግሥት በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል መዋሰኛ አካባቢ ለተቀሰቀሰዉ ግጭት መንስኤዉን እንዲያጣራ በጠየቀበት መግለጫዉ፤ ኢትዮጵያን ለወደፊት ጠንካራ፤ የበለፀገች እና ዴሞክራሲያዊ ሀገር አድርጎ የመገንባቱ ርምጃ ግልፅን ሁሉን ያሳተፈ የፖለቲካ ውይይት ሲኖር እና የዴሞክራሲና እና ፍትህ ተቋማት ሲጠናከሩ መሆኑን አመልክቷል። የሰሞኑ ክስተቶችም ፈጣን እና ተጨባጭ ማሻሻያዎች በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ሲደረግ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥቷል።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ