የጠቅላይ አቃቤ ህግ የሶማሌ ክልል የምርመራ ውጤት
ዓርብ፣ ጥር 17 2011የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሶማሌ ክልል ተፈጸመ ባለው ወንጀል የቀድሞው የክልሉን ፕሬዝዳንት አብዲ ሙሃመድ ኡመርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች መሳተፋቸውን አስታውቋል። በዚህም ከ58 በላይ የተገደሉ ሲሆን ሰዎቹ ተገድለው በጅምላ የተቀበሩ ናቸው። ከዚህም 50 አስክሬኖች ተቆፍረው የወጡ ሲሆን 8 ቱ በጅግጅጋ ሚካኤል ቤተክርስትያን የተቀበሩ ናቸው።
በምርመራ ሂደቱ ሌሎች 200 በጅምላ ተቀብረው የተገኙ አስክሬኖች መገኘታቸውንና በምርመራ ሂደት ላይ መሆናቸው ተረጋግጧል። በተጨማሪም 10 ሴቶች መደፈራቸው እና 266 ሰዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ፤ 412 ሚሊዮን 468 ሽህ 826 ብር የሚገመት ንብረት መውደሙንና መቃጠሉን ብሎም አብያተ ክርስትያናት፣ ባንኮች፣ የመንግስት ተቋማት በህቡዕ በተደራጁ አካላት ጉዳት ማድረሳቸው ተነግሯል፡፡
ይህንን ተከትሎ የቀድሞውን የክልሉን ፕሬዝዳንት ጨምሮ 6 ተጠርጣሪዎች በእስር ላይ ሲሆኑ 46 ተጠርጣሪዎች ተለይተው ክስ ተመስርቷል፣ ያልተያዙትንም ለመያዝ እየተሰራ ነው ተብሏል። ያልተያዙት ተጠርጣሪዎች የተወሰኑት ከሃገር መውጣታቸውንና ካመለጡበት ሃገር ጋር በመተባበር ለመያዝ በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቅላይ አቃቢ ህግ ያስታወቀ ሲሆን ፡ በሃገር ውስጥ የተደበቁ እንዳሉ፡ የተወሰኑትም ያለመከሰስ መብት ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡ ይሁንና ሁሉንም ለመያዝ በሂደት ላይ ነኝ ብሏል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፡፡
ዜጎችን ከአራዊት ጋር እያሰሩ ከፍተኛ ሰቆቃ መፈጸም የወንጀሉ አካል እንደነበር የገለጠው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ተጠርጣሪዎች ላይ ከሰኞ ጀምሮ ክስ እንደሚመሰርት እና የክስ ዝርዝሩም ህገ መንግስታዊ ስርአትን በመናድ፣ በማነሳሳት፣ በመሳተፍ፣ አስገድዶ በመድፈር እና ንብረትን በማውደም እንደሚሆን አስታውቆ የጅምላ የዘር ማጥፋት ወንጀል አልተፈጸመም ሲል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ መረጃ የማግኘት ሂደቱ ከባድ እንደነበር የገለጸው መግለጫው፤ በዚህ ወንጀል ላይ ከክልሉ ውጭ ያሉ ሌሎች አመራሮች ስለመሳተፋቸው መረጃ እንዳላገኘ፤ አቶ አህመድ ሽዴ ተሳትፎ ይኑራቸው አይኑራቸው እስሁን መረጃ እንዳላገኘ ገልጿል።
የእነ አቶ በረከት ስምኦን ጉዳይ የአማራ ክልል ጉዳይ ስለመሆኑ፣ የአቶ ጌታቸው አሰፋ ጉዳይም በሂደት ላይ ስለመሆኑ ከጋዤጠኞች ለተሰነዘሩ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት መግለጫውን ቋጭቷል፡፡
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ