«የ18 ወራት የጡረታ አበላችን አልተከፈለንም»
ሐሙስ፣ የካቲት 21 2016የ18 ወራት የጡረታ አበላችን አልተከፈለን ያሉ በትግራይ የሚገኙ ጡረተኞች ዛሬ በመቐለ የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ። ጡረተኞቹ በሰልፋቸው የ18 ወራት የጡረታ አበል እንዲከፈላቸው በተለያዩ መፈክሮች የጠየቁ ሲሆን፥ የፌደራል መንግስቱ እና የክልሉ አስተዳደር ለጥያቄያቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል። በተለያየ የስራ መስክ ለረዥም ግዜያት አገልግሎት ላይ ከቆዩ በኃላ በጡረታ የተሰናበቱ እነዚህ ሰልፈኞች ያልተከፈለ የጡረታ አበላቸው እንዲከፈል የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ ይህ የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የጦርነቱ ወቅት የ18 ወራት የጡረታ አበላቸው እስካሁን ድረስ እንዳልተከፈሉ የሚገልፁ በመቐለ የሚገኙ ጡረተኞች ዛሬ በከተማዋ የተለያዩ ጎዳናዎች በመዘዋወር እና ወደሚመለከታቸው የመንግስት መስርያ ቤቶች በመቅረብ የተቃውሞ ድምፃቸውን አሰምተዋል። "የአስራ ስምንት ወር የጡረታ አበላችን ይከፈለን" ፣ "ባለውለታ ይከበራል እንጂ በረሃብና በበሽታ አይቀጣም" ፣ "ፍትሕ ለጡረተኞች" የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮች ያሰሙ የነበሩት እነዚህ ከተለያየ የመንግስት ስራ መስክ በጡረታ ተገለው፥ በሚሰጣቸው ወርሓዊ የጡረታ አበል የሚተዳደሩ የዕድሜ ባለፀጎች፥ በሰልፍ ጨምሮ በተደጋጋሚ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ያቀረቡት አቤቱታ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱ በማንሳት ይወቅሳሉ። በሰልፉ ተሳታፊ የነበሩት እና በፖሊስነት ለ35 ዓመታት ካገለገሉ በኃላ በጡረታ በክብር መሸኘታቸውን የሚገልፁት የ72 ዓመት አዛውንት አምሳ አለቃ ሐጎስ መኮንን፥ የሚገባንን ክፍያ አጥተን ለችግር ተዳርገን እንገኛለን ይላሉ።
የትግራይ ክልል ብድር ጠየቀ፣ ደሞዝ መክፍል ተስኖታል
ሌላዋ ያነጋገርናቸው ጡረተኛ ወይዘሮ ትካቦ ገብረኪሮስ በበኩላቸው፥ ከ13 ዓመት በፊት ከነበሩበት የመንግስት ተቋም ቴሌኮምኒኬሽን በጡረታ የተሰናበቱ ናቸው። የቆየ የተደራረበ ዕዳ፣ ኑሮ ውድነት፣ የጡረታ አበሉ ውሱንነት እና ሌሎች ወቅታዊ ችግሮች፥ ጡረተኞቹን እየፈተኑ ያሉ ናቸው ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ለጡረተኞቹ ምላሽ የሰጡት በፌደራሉ መንግስት፥ የመንግስት ስራተኞች ማሕበራዊ ዋስትና አስተዳደር የሰሜን ሪጅን ተወካይ አቶ ተወልደ ለማ፥ ካልተከፈለው የ18 ወር የጡረታ አበል መካከል የአንድ ወር በቅርቡ ለጡረተኞቹ እንደሚሰጥ ቃል የገቡ ቢሆንም፥ በቀረው የበርካታ ወራት ውዝፍ ያልተከፈለ ወርሐዊ አበል ጉዳይ ግን፥ ከክልሉ አስተዳደር እና የፌደራል መንግስት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑ አንስተዋል።መቐለ በሺህዎች የሚቆጠሩ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ
በትግራይ በአጠቃላይ 100 ሺህ ገደማ የሚገመቱ በተለያየ ዘመን ጡረታ የወጡ የቀድሞ ሰራተኞች ይገኛሉ። ከጡረታ አበል ውጭ መምህራንን ጨምሮ በትግራይ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ስራተኞች ያልተከፈለ የተከማቸ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ያቀርባሉ። የክልሉ አስተዳደር ደሞዝና አበሉ ለመክፈል የበጀት እጥረት እንደገጠመው ሲገልፅ ቆይቷል።
ሚሊዮን ኅይለሥላሴ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ