1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2017 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል መልእክቶች

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ መስከረም 1 2017

2017 ዓ.ም "ግጭቶቻችንን በውይይት እና በድርድር ፈትተን፤ የዘመናት ስብራቶቻችንን በምክክርና በሽግግር ፍትሕ ጠግነን፤ በብዙ ነገሮች ራሳችንን ችለን" የምንለወጠበት እንዲሆን ምኞቴ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ። የሃይማኖት መሪዎችም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የሰላም እና የአንድነት ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/4kUe3
አደይ አበባ
አደይ አበባምስል Yohannes Geberegziabeher

የ2017 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል መልእክቶች

በአዲስ ዓመት መልዕክታቸው "ዘመን ዕድል ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያንን መጠቀም ግን "የሥራ ውጤት ነው" ብለዋል፡፡ 

በ2016 ለኢትዮጵያ ምን አሳክተናል? በ2017ስ ለኢትዮጵያ ምን ተዘጋጅተናል? "የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የዘመን መለወጥን ትርጉም ይቀይረዋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ዘመን እየተለወጠብን ነው ወይስ ዘመኑን እየለወጥነው ነው? የሚለውንም ጠይቀዋል።

በ2017 ግጭቶችን በውይይትና በድርድር የመፍታት ፣ስብራት ያሉትን በምክክርና በሽግግር ፍትሕ የመጠገን ምኞት እንዳላቸውም ገልፀዋል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ደግሞ ግጭት ውስጥ ያሉ ተፋላሚ ተዋንያን በዓመቱ ወደ ውይይት እና ድርድር እንዲገቡ ጠይቋል።

የተለያዩ ሐይማኖት መሪዎችም ለሀገሪቱ የሰላም እና የአንድነት ምኞታቸውን ገልፀዋል

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን  ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ "ያልታደሱ ብዙ ዓመታት ተጭነውን አልፈዋል" መገለጫዎቹም የእርስ በርስ ግጭት፣ ረሃብ፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ ኋላቀርነት ሲሆኑ በዓለም ፊት ልዩ መለያችን ሆነዋልም ብለዋል። ዛሬም ከዚህ "ከመላቀቅ ይልቅ አጠናክረን ለመቀጠል ውል የገባን ይመስል አጠናክረን እየቀጠልን ነው" ያሉት ፓትርያርኩ "ለበርካታ ዓመታት የተሸከምነው ደባል የአስተዳደር ስልት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚጣጣም ሆኖ አልተገኘም" ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

መፅሐፍ ቅዱስ እና ቁራን ጎን ለጎን ሆነው
ምስል Pascal Deloche/Godong/picture-alliance/dpa

በ2016 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ ከ6,164 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ያስታወቁ አሥር የሲቪክ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን፣ ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩ፣ ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አስቀድመው ጠይቀዋል። ዓመቱ "መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የተፈፀሙበት ዓመት ነበር" ያሉት የሲቪክ ድርጅቶች ይህ ችግር እንዲቀረፍ የሰላም ጥሪ አድርገዋል።

ሰለሞን ሙጬ
ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ