ግጭትና ጦርነቶች፡ የርዳታ ድርጅቶች ላይ ብርቱ ፈተና መደቀናቸው
ረቡዕ፣ መስከረም 8 2017ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ባለባቸው አከባቢዎች የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቶችን ማከናወን ፈታኝ እንደሆነበት የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ዐሳወቀ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪም ግጭት ባለባቸው እንደ ዩክሬን-ሩሲያ ባሉ ጦርነቶች በዚህ ሳምንት ብቻ ሦስት የሰብአዊ ደርጅቱ ሠራተኞች ሕይወት መቀጠፉ በዓለማቀፍም የችግሩ መባባስን የሚያሳይ ተብሏል፡፡ በጎርሪዮሱ 1949 የተፈረመው የጄኔቫ ኮንቬንሽን የተሰኘው በጦርነት ወቅት ተጋላጭ የሆኑ ከተፋላሚነት ውጪ ያሉት ሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ እንዲያገኙ የሚያስገድደው ዓለማቀፍ የሰብአዊነት ሕግ 75ኛው ዓመቱ እየታወሰ ይገኛል፡፡
ከአውዳሚው ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ ዓለም ላይ በየቦታው በሚደረጉ የሣሳሪያ ግጭቶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ዜጎች ዋጋ እከፈሉ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ ደግሞ ዓለም ከከዚህ ቀደም ስህተቱ አለመማሩን ያሳያል በሚል እየተነሳ ነው፡፡ ለዚህም ትልቅ መንስኤ የሆነው ምን ይሆን በሚል ዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የዓለማቀፍ ሰብአዊነት ሕግ የጄኔቫ ኮንቬንሽን 75ኛ ዓመት የምስረታ ማስታወሻን በማስመልከት መንግስታት ቆም ብለው እንዲያስቡ ጠይቋል፡፡
ለዚህም ይመስላል የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) የምስራቅ አፍሪቃ ሪጅን ቃል አቀባይ አልዮና ሺዬንኮ ይህ ዓመት እጅጉን አስፈላጊ ብለው ያነሱት፡፡ ቃል አቀባይዋ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለምልልስ ይህ ዓመት ቆም ብለን ነገሮችን በስክነት የምንመለከትበት ልሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡ "ለኛ ይህ ዓመት እጅጉን አስፈላጊያችን ነው፡፡ ዓለማቀፉ የሰብአዊነት ሕግ በጄኔቫ ረቅቆ ሥራ ላይ ከዋለ እነሆ 75 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህን ወቅት ደግሞ እንደምንመለከተው ጦርነት ግጭቱ ዓለም ላይ እንደ አሸን የፈላበት ነው፡፡ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች በሰውሰራሽ አስተውሎትም ታግዞ ስጋትን ማጫሩ ጊዜው ቆም ብለን የምናስብበት እንዲሆን ያስገድዳል” ብለዋል፡፡ "በግጭትና የእርስበርስ ጦርነቶች፤ ብሎም በመንግስታት መካከል የሚደረጉ ጦርነቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄዎችን ፈተና ውስጥ ከቶታል፡፡ እነዚህ በግጭት ውስጥ ያሉ አካላትም ሆኑ መንግስታት ሰላማዊ ሰዎችን ከአደጋ የምጠብቁበት ስልት መቀየስ ይኖርባቸዋል” ነው ያሉት፡፡
የሰብአዊ ድርጅቶች ሠራተኞች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች
ቃል አቀባይዋ እንደ ዓለማቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ባሉ በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ላይ ተደቅኗል ያሉት ፈተና የሰብዓዊ ተቋማቱ ሰራተኞችን ሕይወት አደጋ ላይ የምጥል ጭምርም ነው፡፡ "እንደ ሰብአዊ ተቋም እየተጋፈጥን ከምንገኘው ፈተናዎች አንዱ በጠመንጃ ግጭት ላይ በተሰማሩ ሰዎች ምክንያት የተጎዱትን ሰላማዊ ዜጎች ተደራሽ የማድረግ ብርቱ ፈተና ነው፡፡ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ እንኳ በዩክሬን ያጣናቸው ሶስት የተቋማችን የእርዳታ ሰራተኞች ፈተናውን የሚያሳይ ሌላው አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ከዓለማቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ እና ማህበራት ጋር የሚሰሩ በጎ ፈቃደኞች ጭምር የሕይወት መስዋእትነት እየከፈሉ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ በሩቅና አስቸጋሪ ስፍራዎች ላይ ያሉ የተቸገሩ ሲቪሎችን ማግኘትና የአንገብጋቢ እርዳታ ተደራሽ ማድረግ ብርቱ ፈተና ሆኖብናል” ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ ያለው ፈተና
ኢትዮጵያ አሁን ላይ መሰል አስቸጋሪ የሲቪሎች የአንገብጋቢ ርዳታ ተደራሽነት ብርቱ ፈተና ውስጥ ከሚገኙባቸው አከባቢዎች አንዱ መሆኑንም ያነሱን ቃል አቀባይዋ፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መስራት ግድ ሆኗል ነው የሚሉት፡፡ "ኢትዮጵያም የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከብርቱ ፈተና ጋር ከሚሰራባቸው አከባቢዎች አንዷ ተደርጋ ነው የምትጠቀሰው፡፡ በኢትዮጵያ በግጭት ላይ ባሉ እንደ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በተጨማሪ የመሳሪያ ድምጽ በማይሰማበት ትግራይ ክልልም ባለፈው ግጭት ለተጎዱት ዜጎች ድጋፋችን እንደቀጠለ ነው፡፡ አሁንም ግጭት ባለባቸው የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችም በየቀኑ ሰላማዊ ዜጎች ለብርቱ ፈተና ተዳርገዋል፡፡ በነዚህ አከባቢዎች ICRC መጠለያን ጨምሮ በንጹ መጠት ውኃ አቅርቦት ላይ አተኩሮ ይሰራል፡፡ እንደ ላሊበላ ባሉ ህብረተሰቡ አደገኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርን በሚጋፈጥበት እነዚህ ስራዎች በትኩረት ይሰራሉ” ብለዋል፡፡
በመሰል አከባቢዎች ድጋፍን ተደራሽ ማድረግ ቀላል አይደለም ያሉት የ ICRC ሪጅናል ቃል አቀባይዋ በነዚህ አከባቢዎች ከአገር በቀል የርዳታ ድርጅቶች እና እንደ ኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ካሉ አጋሮች ጋር ብሎም ከበጎፈቃደኞች ጋር እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሐይ ጫኔ