ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና የኮሮና ወረርሽኝ
ማክሰኞ፣ የካቲት 2 2013ዓለም በኮሮና ተሐዋሲ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥሎ ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው በተዘጉበት ወቅት አፍሪቃ ውስጥ በርካታ አዳጊ ሴቶች ለግርዛት ሳይጋለጡ እንዳልቀሩ ለመብት የሚሟገቱ ድርጅቶች አመለከቱ። የተመድ በነደፈው ዘላቂነት ያለው የልማት እቅድ በጎርጎሪዮሳዊ 2030 ዓ,ም ይኽን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በመላው ዓለም ለማስቀረት ታስቧል። ሆኖም በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ ተጨማሪ ሁለት ሚሊየን አዳጊ ሴት ልጆች የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ ሰለባ ሊሆኑ እንደሚሉ የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ይገልጻል።
በመላው ዓለም 200 ሚሊየን አዳጊ ሴት ልጆች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የሆነው የግርዛት ሰለባዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በየዓመቱም አራት ሚሊየን የሚሆኑት ለዚሁ ድርጊት መጋለጣቸውም ይነገራል። የተመድ እንደሚለው ይኽ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ይበልጥ ከ30 ሃገራት ጋር የተገናኘ ሲሆን አብዛኞቹም አፍሪቃ ውስጥ ይገኛሉ። በአንጻሩ ጥናቶች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራትም እንደሚፈጸም አልፎ ተርፎም በስደት ወደ ዩናይትድ ስቴትስና የተለያዩ የአውሮጳ ሃገራትም መዛመቱን በማመልከት የሃገራቱን ቁጥር 50 ያደርሳሉ።
ምንም አይነት ሃይማኖታዊ ዳራ እንደሌለው የሚነገርለት የሴት ልጅ ግርዛት ከጤና አኳያ ከባድ እክል የሚያስከትል መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት በተደጋጋሚ ያሳስባል። ሶማሊያ ውስጥ 98 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች የዚህ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሰለባ ሲሆኑ፤ ጊኒ፣ ጅቡቲ፣ ማሊ እና ሴራሊዮንም ከመላው ዓለም በዚህ ረገድ ከሶማሊያ ቀጥለው የሚሰለፉ ሃገራት ናቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም እንኳን ድርጊቱን ለማስቆም የሚደረገው ጥረት በአንዳንድ አካባቢ ከፍተኛ ውጤት ቢያስገኝም ዛሬም በከተሞች ሳይቀር መፈጸም መቀጠሉን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ዕለት ፀረ የሴት ልጅ ግርዛት ቀንን በማስመልከት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ይኽን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትም ሆነ ባጠቃላይ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቀረት ያለሙ ሀገራዊ እቅዶች አፈጻጸም መጓተት የለበትም ሲል አሳስቧል። የኮሚሽኑ የሴቶችና ሕጻናት ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ወይዘሮ ዜናዬ ታደሰ ኮሚሽኑ ባለፈው ኅዳር ወር ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ በብሔራዊ ደረጃ የያዘችው እቅድ የደረሰበትን ለመከታተል መሞከሩን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕጻናት ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ወይዘሮ ዜናዬ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆምም ሆነ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመግታት ኢትዮጵያ ጥሩ የሆነ ብሔራዊ እቅድ እንዳላት ነው ያመለከቱት። ሆኖም አፈጻጸሙን ላይ ያለው ውሱንነት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እንደማያስችል ኮሚሽኑ ባካሄደው ቅኝት መታዘቡን ገልጸውልናል።
ኢትዮጵያ በመጪው 2025 ዓ,ም የሴት ልጅ ግርዛትን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ብታቅድም ይህን ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎችን ግን በአግባቡ እየሄዱ አይመስልም። እንዲህ ያሉ እቅዶች ተግባራዊ እንዲሆኑም በየደረጃው የሚገኙ አስተዳደራዊ መዋቅሮችን ጉዳዩን በአግባቡ የመረዳትና ተቀናጅቶ መሥራትን ይጠይቃል። የተመድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዓለም መሪዎች በተመድ ዘላቂነት ያለው የልማት ግብ አማካኝነት እስከ ጎርጎሪዮሳዊ 2030 ዓ,ም ድረስ ይህን ጎጂ ድርጊት ፈጽሞ ለማስቆም ቢያቅዱም ጥቂት የማይባሉት ሃገራት ዛሬም ከ30 ዓመታት በፊት በነበረው መጠን ድርጊቱን እየተፈጸመባቸው መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይም ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የፈጠረውን የእንቅስቃሴ ገደብ የሴት ልጆች ግርዛትን ማባባስ ብቻ ሳይሆን፤ ለውጥ ማሳየት ጀምሮ በነበረው ለአካለ መጠን ሳይደርሱ የመዳሩን ርምጃም ዳግም ወደኋላ ሳይመልሰው እንዳልቀረ ዘ ላንሰንት ያወጣው ዘገባ ያመለክታል። እንደዘገባው ከሆነም በመላው ዓለም በዚህ ጊዜ ውስጥ 2,3 ሚሊየን የሚሆኑ አዳጊ ሴት ልጆች ያለ ዕድሜያቸው ትዳር ውስጥ ለመግባት ስጋት ተጋልጠዋል። ለሰጡን ማብራሪያ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ሕጻናት ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ወይዘሮ ዜናዬ ታደሰን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ