18 የሲቪክ ድርጅቶች ቁልፍ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ለምክክር ኮሚሽን አስገቡ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 201618 በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ የሲቪክ ድርጅቶችን ያቀፈው የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ሕብረት በሀገራዊ ምክክሩ መነሳት እና መታየት ያለባቸው እና ቁልፍ ያላቸውን አራት የሰብዓዊ መብት አጀምዳዎች ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አቀረበ። ሕብረቱ የ አናሳ የማህበረሰብ ክፍሎች ወይም ህዳጣን መብት መከበርን እና ለፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የሆነው ባለው ጎሳን መሰረት ያደረገ ሥርዓት ውክልና የተነፈጋቸው ህዳጣን ማህበረሰቦች ባሉበት ቦታ የፖለቲካ ውክልና እንዲኖራቸው የሚለው የመጀመርያው ያቀረበው አጀንዳ ነው።
ግለሰቦች የመሬት ባለቤት መሆን አለመቻላቸው "ይህ የእኔ ነው" ፣ "ውጣልኝ" የሚሉየዜጎችን መብት የሚነፍጉ የፖለቲካ ችግሮችን እና ግጭቶችን በማስከተሉ የግለሰቦች የመሬት ባለባትነት ይረጋገጥ የሚለውን ሕብረቱ ሁለተኛ አድርጎ ለምክክር ኮሚሽኑ ያቀረበው የሰብዓዊ መብት አጀንዳ ሲሆን ኢትዮጵያ ከምትከተለው የፓርላሜንታዊ የመንግሥት ዐወቃቀር ወደ ፕሬዝዳንታዊ እንድትሸጋገር ምክረ ሀሳብ መቅረቡም ሌላኛው ነው።
ይህ የሲቪክ ድርጅቶች ሕብረት ተጠያቂነት እንዲሰፍን ፣ የሲቪክ ምህዳሩ እንዲሰፋ እና በየ አካባቢው ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎች የምክክር ሂደቱ ውክልና እንዲኖራቸው ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ቁልፍ በሚል ባቀረባቸው የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ተካተዋል።
የህዳጣን መብት ጥበቃና ውክልና የምክክሩ አጀንዳ እንዲሆን ተጠየቀ
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ሕብረት (ኢሰመድሕ) ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የውይይት ቁልፍ አጀንዳ መሆን ያለባቸው ናቸው በሚል ካቀረባቸው አጀንዳዎች ውስጥ የህዳጣን መብት ጥበቃ ቀዳሚው ነው። የፖለቲካ ውክልና የሌላቸው አናሳ ማህበረሰቦች መብታቸው እንዲከበር በትምህርት፣ በሥራ ፣ በመንግሥት አገልግሎት የማግኘት እና ሌሎች መብቶች ላይ የሚደርስባቸውን ተጨባጭ መገለልን የፈጠሩ እውነታዎችን መቀየር እንዲቻል ጉዳዩ የውይይት ሀሳብ እንዲሆን ምክረ ሀሰብ ሆኖ ቀርቧል ሲሉ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር መሱድ ገበየሁ ገልፀዋል።
የግለሰቦች የመሬት ባለቤትነትን በተጨባጭ ማረጋገጥ የሚለው ሌላኛው ሕብረቱ ያቀረበው አጀንዳ ነው።
"በአብዛኛው ጊዜ ለመብት ጥሰት መነሻ የሚሆነው የመሬት አስተዳደራችን እና የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደራችን ነው። በአብዛኛው መፈናቀሎችን ብናይ ፣ ግጭቶችን ብናይ ይሄ የኔ መሬት ነው፣ ይሄ የኔ ክልል ነው ፣ ክፉ ክልሌ ውጣ ወይም እዚህ ክልል ባለቤት አይደለህም" የሚሉ ችግሮች መነሻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች አንደኛዋ ኮሚሽነር ብሌን ገብረ መድሕን አጀንዳ በተደራጀ መልኩ መቅረቡ ሥራቸውን እንደሚያቀል፣ በዋናነት የዜጎች ዋነኛ ሀሳቦች ሳይታዩ እንዳይቀሩ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው አጀንዳዎቹ ኮሚሽናቸው ባቀረበው ጥሪ መሰረት የቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። ኢሰመድሕ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር መድረኮች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል ሲልም ጠይቋል። የሲቪክ ማህበራት ሁነኛ የልማት አጋር እንዲሆኑ የሚለውም አጀንዳ ለ ምክክር ኮሚሽኑ ከሲቪክ ድርጅቶች ቀርቧል። የመንግሥት ዐወቃቀር ከፓርላሜንታዊ ወደ ፕሬዝዳንትልዊ ሥርዓት እንዲለወጥ ምክረ ሀሳብ ሲቀርብም ሆነ የምርጫ ስርዓቱ እንዲሻሻል ሲጠየቅ የመወያያ አጀንዳ እንዲሆን ከማሰብ እንጂ ውሳኔው የሕዝብ ነው ሲል ሕብረቱ ገልጿል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ
ሰለሞን ሙጬ