1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፍልሰትአፍሪቃ

53 ኤርትራዊያን ድንበር ሊሻገሩ ሲሉ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ተያዙ ተባለ

ዓርብ፣ ኅዳር 21 2016

በአገር መከላከያ ኦራል ተሽከርካሪ ተጭነው ድንበር ለመሻገር ሞክረዋል የተባሉ 53 ኤርትራዊያን ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ ። የክልሉ የፀጥታ ኃላፊዎች ለዶቼ ቬለ (DW) እንዳሉት፦ ኤርትራዊያኑ በክልሉ አሌ ዞን ውስጥ የተያዙት ወደ ኬኒያ ለመሻገር በጉዞ ላይ እንዳሉ ነው ።

https://p.dw.com/p/4ZfBG
Äthiopien Armee Truck Migration
ምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

ፍልሰተኞቹ የተያዙት የአገር መከላከያ ኦራል ተሽከርካሪ ውስጥ ነው ተብሏል

በአገር መከላከያ ኦራል ተሽከርካሪ ተጭነው ድንበር ለመሻገር ሞክረዋል የተባሉ 53 ኤርትራዊያን ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ ። የክልሉ የፀጥታ ኃላፊዎች ለዶቼ ቬለ (DW) እንዳሉት፦ ኤርትራዊያኑ በክልሉ አሌ ዞን ውስጥ የተያዙት ወደ ኬኒያ ለመሻገር በጉዞ ላይ እንዳሉ ነው ። ኤርትራውያኑን ድንበር ለማሻገር ሞክሯል ያለውን የመከላከያ ሠራዊት ኦራል ተሽከርካሪ ነጂ በሕግ ቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ ዐስታውቋል ። ኤርትራዊያኑን ደግሞ ለፌዴራል የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ለማስተላለፍ ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ሲል አክሏል ። 

53 ኤርትራዊያን ፍልሰተኞች በፖሊስ ተያዙ 

በአገር መከላከያ ካሚዮን ተጭነው ድንበር ለመሻገር ሞክረዋል ያላቸውን 53 ኤርትራዊያንን መያዙን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዐስታወቀ ፡፡ የክልሉ የፀጥታ ኃላፊዎች ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ኤርትራዊያኑ በክልሉ አሌ ዞን ውስጥ የተያዙት ወደ ኬኒያ ለመሻገር በጉዞ ላይ እንዳሉ ነው ፡፡ ፍልሰተኞቹ  የተያዙት የሠሌዳ ቁጥሩ መሠ 2-2347 በሆነ የአገር መከላከያ ኦራል ተሽከርካሪ ተጭነው ድንበር ለመሻገር በጉዞ ላይ እንዳሉ ነው ተብሏል ፡፡ ሊያዙ የቻሉትም በአካባቢው ሕገ ወጥ ስደተኞች ድንበር እያቋረጡ እንደሚገኙ ለዞኑ ፖሊስ አባላት በደረሰው ጥቆማ መነሻነት በተደረገ ክትትል መሆኑን የዞኑ  ሠላምና ፀጥታ  መምሪያ ኃላፊ አምሳሉ ሀንጋሶ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡ 

የመከላከያ ኦራል አሽከርካሪው 

በአሁኑ ወቅት ፍልሰተኞቹን ጭኖ ለማሻገር ሞክሯል የተባለው የመከላከያ ሠራዊት ካሚዮን አሽከርካሪው በሕግ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ የጠቀሱት የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊው «ፍልሰተኞቹን ደግሞ ለጊዜው በዞኑ ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ አድርገናል ፡፡ ምክንያቱም ከፍልሰተኞቹ መካከል ህጻናት ጭምር ይገኙበታል ፡፡ ከተያዙበት ቀን ጀምሮ ዞኑ ባለው አቅም የምግብ እና ህክምና አገልግሎት አቅርቦላቸዋል  ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ለፌዴራል የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ለማስረከብ እየተነጋገርን  እንገኛለን» ብለዋል ፡፡

ስደተኞች እና ፍልሰተኞች ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ደቡብ አፍሪቃ በተደጋጋሚ አስቸጋሪ ጉዞ ያደርጋሉ
ይህ መስመር ስደተኞች እና ፍልሰተኞች ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚያልፉባቸውን ሃገራት ያሳያል

ዶቼ ቬለ ተያዙ በተባሉት ፍልሰተኞች ዙሪያ ከፌዴራል የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ጥረት አድርጓል ፡፡ ይሁን እንጂ የአገልግሎቱ የሥራ ኃላፊ ጉዳዩን አጣርተን ምላሽ ለመስጠት ከሰዓታት በኋላ መልሳችሁ ደውሉ ባሉት መሠረት ቢደወልላቸውም ሥልካቸው ጥሪ አይመልስም ፡፡ 

ኢትዮጵያ በደቡብዊ የአገሪቱ ክፍል ከኬኒያ በምትዋሰንባቸው የሞያሌ እና የቱርካና አካባቢዎች ዋነኛ የፍልሰተኞች መሸጋገሪያ መስመሮች መሆናቸው ይታወቃል ፡፡ በኢትዮጵያ ባለፈው የ2015 ዓ.ም ብቻ ሱዳንና ሶማሊያን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት የተነሱ ከ110 ሺህ በላይ  ፍልሰተኞች ወደ አገሪቱ መግባታቸውን ከፌዴራል የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ