ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለታጣቂዎች ያቀረበው የሰላም ጥሪ ምን ላይ ደረሰ?
ረቡዕ፣ ግንቦት 14 2016ነፍጥ ያነገቡት አካላት ይህንን ከማድረግ የሚከለክላቸው አሠራር የለም ያሉት ኮሚሽነሩ ተቋማቸው ለእነዚህ አካላት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥሪ ውጤቱ ምን ይመስላል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ «ኮሚሽኑ ከመንግሥት እና ከተለያዩ ወገኖች ጋር የሚሠራ እንደመሆኑ መጠን ይሄኛው እንዲረጋገጥ ያደርጋል» ብለዋል። ይህም ማለት «ሀገራችንን ካለችበት ቀውስ ማውጣት አንዱ እና ብቸኛው መንገድ» ነው ያሉት የሥራ ኃላፊው «የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራው አንድንም ወገን ማግለል አይደለም» ሲሉም አብራርተዋል።
ኮሚሽኑ አንድንም ወገን የማግለል ሥራ አይሠራም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነፍጥ አንግበው ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ወደ ምክክር መድረኩ እንዲገቡ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል። የተፈጠረውን እድል ሁሉም የማኅብረተሰብ ክፍሎች ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ተደጋግሞ ተጠይቋል። «እውነትን በሰላማዊ መንገድ በማፈላለግ በሀገራዊ ምክክር በመሳተፍ፣ ሀገራችንን ከግጭት ምዕራፍ ማስወጣት ይቻላል» የሚለውን ይዘን አንድ ላይ መምጣት አለብን የሚሉት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች አንዱ አምባሳደር መሃሙድ ድሪር፤ የእነዚህን አካላት «ሀሳባቸውን የማጥላላት ሥራ አንሠራም"፣ እኛ የምንለው ይሄ መንገድ አያዋጣም የሚል ነው» ብለዋል። አክለውም « የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራው አንድንም ወገን ማግለል አይደለም» ነው ያሉት።
ነፍጥ ያነሱትን አካላት ለማነጋገር «ጥረቶቹ ይቀጥላሉ»
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚገኙት አካላት ወደ ምክክር መድረኩ ቢመጡ «ተገቢውን የዋስትና ጥበቃ» እንደሚያመቻች ከዚህ በፊት አስታውቋል። የዚህ ጥሪ ውጤት ምን ይመስላል? ኮሚሽኑ መሰል ዋስትና የመስጠት ሥልጣንስ በሕግ የተቸረው ነውን? ኮሚሽኑ እነዚህን ቡድኖች እንደሌሎች የማኅበረስብ ክፍሎች በማግኘት ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አለ ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለኮሚሽነር አምበሳደር መሃሙድ ድሪር አቅርበንላቸዋል። እሳቸውም ሲመልሱ፤ «በርካታ ተዋንያን የሚሳተፉበት እና ወደ በጎ ለመመለስ እና ወደዚህኛው ሕጋዊ ከለላ የሚሰጥበት፣ ወደ ምክክሩ ዐውድ የሚገቡበት የሚመቻችበት ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ነው ማለት ነው» ብለዋል። ኮሚሽኑ ታጣቂ ቡድኖችን አግኝቶ አነጋግሮ እንደሆን ለተጠየቁት ሲመልሱ «እንደዚህ አድርገናል፣ እንደዚያ አላደረግንም የሚለውን ወደኋላ ትተን ጥረቶቹ ይቀጥላሉ» በማለት መልሰዋል።
የዘላቂ ሰላም ተስፋ እና ሥጋት
የሀሳብ ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት መሞከር «ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም» የሚለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በብዙዎች ዘንድ ዘላቂ ሰላም ያመጣል በሚል ተስፋ የተጣለበት የመሆኑን ያህል፣ ከመነሻው ከኮሚሽነሮች አሰያየም ጀምሮ እስከ ሂደቱ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች እየተነሱበት ከሂደቱ ራሳቸውን ያገለሉ አካላት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ