1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለሰላም በአደባባይ ጥሪ ማስተጋባቱን የቀጠለው የሰላሌ ህዝብ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 21 2016

በሰላም እጦት የተማረረው የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ) ዞን የእግዞታ ጥሪውን በአደባባይ ማስተጋባቱን ቀጥሏል፡፡ በዞኑ አራት ዓመታት ገደማ ያስቆጠረው የሰላም እጦቱ ችግር አርሶአደሩን አፈናቅሎ በርካቶች ህይወታቸውን እንዲያጡም ምክንያት በመሆኑ የሰላም ይምጣ ጥሪው በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች መቅረቡ እየቀጠለ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4jyJN
Nord-Shoa-Gemeinde ruft zum Frieden auf / Addis Ababa
ምስል Seyoum Getu/DW

በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ የሰላሌ ህዝብ ለተፋላሚዎች የሰላም ጥሪ አስተጋብቷል

ለሰላም በአደባባይ ጥሪ ማስተጋባቱን የቀጠለው የሰላሌ ህዝብ
በሰላም እጦት የተማረረው የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ) ዞን የእግዞታ ጥሪውን በአደባባይ ማስተጋባቱን ቀጥሏል፡፡ በዞኑ አራት ዓመታት ገደማ ያስቆጠረው የሰላም እጦቱ ችግር አርሶአደሩን አፈናቅሎ በርካቶች ህይወታቸውን እንዲያጡም ምክንያት በመሆኑ የሰላም ይምጣ ጥሪው በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች መቅረቡ እየቀጠለ ነው፡፡ ማህበረሰቡ በሚያቀርበው ጥሪ በግራም ሆነ በቀኝ ያሉ ሁለቱም ተፋላሚዎች ለፍጹም ሰላም እጆቻቸውን እንዲዘረጉ ነው እየጠየቀም ያለው፡፡

እግዝኦ…አቤት… እንዲህ ሲል በአደባባይ የወጣው፤ ስለሰላም የሚጣራው የሰላሌ ህዝብ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች አሁንም ጽምጼ ይደመት፤ ይሰማ እያለ ነው፡፡ 
በትናንትናው እለት በሱሉልታ ጫንጮ ወረዳ በጫንጮ ከተማና አከባቢው ከሰሞኑ አደባባይ ወጥተው ልመናቸውን ሲያቀርቡ የነበሩትን የዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ህዝብ ፈለግ በመከተል የሰላም ጥሪያቸውን ሲያስተጋቡ ውለዋልም፡፡ 


የማህበረሰቡ ጥሪ ዋና ዓለማ
በዞኑ ጫንጮ ትናንት በተካሄደው የሰላም ጥሪ ላይ ተገኝተው የህዝባዊ የሰላም ጥሪውን ከደገፉት አንዱ አስተያየት ሰጪ ህዝቡን አደባባይ ያወጣው ምሬትና ግቡ አንድና ግልጽ ነው ይላሉ፡፡ “ያው አሁን በግልጽ እንደታየው ሰላም የለም፡፡ ሰላም እንዳይኖር የሆነውና ሊመጣም የሚችለው በሁለት በሚፋለሙ አካላት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ግልጽ ለማድረግ በዚህ ግጭት ውስጥ ያሉት መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ናቸው፡፡ አሁን የዚህ ጥሪና ሰልፍ ኣለማው አንዱን ደግፎ ሌላውን የመንቀፍ ዓላማም የለውም፡፡ ጥሪው ግልጽ ነው፤ በግጭት ላይ ያላችሁ ለሰላም አስተዋጽኦ አድርጉ፡፡ ለፈጣሪ ስትሉ ታረቁ የሚል መልእክት ነው መቶ በመቶ የተስተጋባው” ብለዋል፡፡

የሰላሌ ህዝብ የሰላም ጥሪ
በዞኑ ጫንጮ ትናንት በተካሄደው የሰላም ጥሪ ላይ ተገኝተው የህዝባዊ የሰላም ጥሪውን ከደገፉት አንዱ አስተያየት ሰጪ ህዝቡን አደባባይ ያወጣው ምሬትና ግቡ አንድና ግልጽ ነው ይላሉ፡፡ “ያው አሁን በግልጽ እንደታየው ሰላም የለም፡፡ ምስል Seyoum Getu/DW


የተከበሩ ባህላዊ ቁሳቁስና የሚቀርብ ተማጽእኖ
በሰሞነኛው የሰላሌ ህዝብ ተከታታይ ሰልፍ እና የሰላም ጥሪ ህዝቡ ጫጩና ጦር ይዘው፤ ልጅ እንደ በሬ በቀንበር ጠምደው ተማጽኖውን ሲያስተጋባ ታይቷል፡፡ የአገር ሽማግሌው፣ ሴቶች ወጣት አዛውንት ሳይሉ ያማረራቸው የሰላ እጦቱ እንዲገታላቸውም ተማጽነዋል፡፡  “ሰው በፍጹም መማረሩን ተከትሎ በፍላጎቱ ነው ሁሉም የሚወጣው፡፡ ውጣ አትውጣ የሚለው የለም፡፡ በሰላም እጦቱ ያልመጣብን መከራ ምን አለ? በሰላም እጦቱ ችግር ከጎኔ ብዙ ጓደኞቼ ወድቀዋል፤ ተገድለዋል፡፡ ሰላም በመጥፋቱ ስራ የፈቱትንማ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ አምሽተህ መግባት አትችል ምን ያልደረሰብን ችግር አለ” ብለዋል፡፡
በዞኑ በሰላም ችግሩ በተለይም ከዋና ዋና የዞኑ ከተሞች ገባ ባሉ የገጠር ቀበሌያት በርካታ ትምህርት ቤቶች በጦር መውደማቸውና ጤና ጣቢና ጤና ኬላዎች ኦና መቅረታቸውንም ህብረተተሰቡ ያነሳል፡፡ በዞኑ የያያ ጉሌሌ ወረዳ አስተያየት ሰጪም በግጭቱ ምን ያላጣነው አለ ሲሉ ይጠይቃሉ፤ “በወረዳችን የሚናፍቀን፤ መቼስ ይሆን የሚያቧራልን የምንለው፤ ግጭት ጠፍቶ ፍጹም ሰላም የሚሰፍንበት ቀን ነው፡፡ ይህ የሰላም እጦት ችግር ወደ አራት ዓመታት አስቆጥሮብናል፡፡ ከዚህ የተነሳ ወጥቶ መግባት ገብያ ሄዶ መገበያየት ጸሎት የሚያስፈልገን ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ተኝተን  ስንነሳ መልካም የምንሰማበት ቀን እንደ ህልም ርቆናል” ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው የያያ ጉለሌ ነዋሪ፡፡

የሰላሌ ህዝብ የሰላም ጥሪ
በዞኑ በሰላም ችግሩ በተለይም ከዋና ዋና የዞኑ ከተሞች ገባ ባሉ የገጠር ቀበሌያት በርካታ ትምህርት ቤቶች በጦር መውደማቸውና ጤና ጣቢና ጤና ኬላዎች ኦና መቅረታቸውንም ህብረተተሰቡ ያነሳል፡፡ ምስል Seyoum Getu/DW


የግጭቱ ገፈት ቀማሾች እሮሮ
ህዝቡ በግራም ሆነ በቀኝ ባለቤት አጥቷል የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ በተፋላሚዎች መካከል በሚፈጠረው ግጭት ሰላማዊ ህብረተሰብ ሳይወድ እየታመሰ ነው ብለዋልም፡፡ ዘረፋ፣ ድብደባ፣ የቤት ቃጠሎ በግራም በቀኝም ህዝቡ ላይ በተፋላሚዎች የሚፈጸም በደል ነው ሲሉም አስተያየት ሰጪው አመልክተዋል፡፡ “ወጣቱ ብትል ባለሃብቱ አንድም ያለው ሁለት ለብዙ ስቃይና እንግልት ተዳርገዋል፡፡ የታጠቁና በጫካ ያሉ ወገኖች ሌሊት ወደ ከተማ ገብተው ስለሚተኩሱ በዚህ መሃል ሰላም አግኝቶ ቤቱ ውስጥ የሚያድርን ሰው ማግኘት ከባድ ይሆናል፡፡ እስካሁን ለሰላም ተዘረጉ የሚሉ እጆችም ከአንጀት አይመስሉም፡፡ እርቅ እየተባለ ስድምና ማንቋሸሽ በጎን ስደረግ ይስተዋላል” ብለዋል፡፡


በሰላም እጦቱ ያልተጎዳ ነዋሪ የለም፡፡ ገበሬው፣ ተማሪው፣ የመንግስት ሰራተኛው፤ በከተማ ይሆን በገጠር የሚኖረው ሁሉም ዜጋ የችግሩ ገፈትቀማሽ ሆነዋል፡፡ “በዚህ አገር ስንቱን ማኖር የሚችል መሬት ከሁለት - ሶስት ዓመታት ወዲህ ሳይታረስ ያለ ሰፊ ነው፡፡ ገበሬው አርሶ የሚበላበት በሬው በሁሉም አቅጣጫ እየታረደ እየተበላበት ነው፡፡ ሰው ከገጠር ወደ ከተማ፤ ከከተመማም ወደ ከተማ መንቀሳቀስ ፈተና ሆኗል፡፡ ተንቀሳቅሰህ የሚስፈልግህን ሰርተህ ኑሮ መምራት ብርቱ ችግር ሆኗል፡፡ ይህ ከላይ ባለው የመንግስት መዋቅርም በውል ታውቆ እውነታው ብወጣና መፍትሄ ብመታ ነው የምንለው” ሲሉ አስረድተዋልም፡፡ 


በዚህ ሁሉ የሰላም እጦት ችግር የተማረረው ህብረተሰብ ሰላም ተጠማን ሲል አደባባይ ወጥቶ ድምጹን ለማሰማት መገደዱ ነው የተገለጸው፡፡ ስለዞኑ የጸጥታ ይዞታና እልባቱ ለዞኑ መንግስት ጸጥታና አስተዳደር ኃላፊ በመደወል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ በቅርቡ ግን የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ለዶቼ ቬለ እንደ ተናገሩት የክልሉ መንግስት ውጥን በሰላማዊ መንገድ ዘላቂ ሰላም ማስፈን ብሆንም የሰላም ጥሪውን ባልተቀበሉት ላይ የኃል እርምጃ መወሰዱ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡ በተለያዩ አከባቢዎች ለሚወሰዱ ጥቃቶችም “መንግስት የጸጥታው አካልን በሁሉም ስፍራ ማስቀመጥ ስለማይችል ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በትብብር ልሰራ ይገባል” ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ 

ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ