1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኒጀር ምን መፍትሄ ይገኝ ይሆን ?

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 2 2015

የአዉሮጳና አፍሪቃ መንግስታት፤ አካባቢያዊና ዓለማቀፍዊ ድርጅቶች፤ በኒጀር ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በማውገዝ ከስልጣናቸው የተወገዱት ፕሬዝድንት ባሙዝ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱና ህገ-መንግስታዊ ስራቱ እንዲከበር ጥሪ ሲያስተላለፉ፤ የቀን ገደብ በማስቀመጥ ዛቻ ቢያሰሙም፤ እስካሁን ግን ሰሚ አላገኙም።

https://p.dw.com/p/4UvI3
Niger, Niamey | General Abdourahmane Tchiani bei einer Kundgebung von Anhängern der Putschisten
ምስል Balima Boureima/AA/picture alliance

«ለፈንረንሳይ ለኒኩሌር ኃይሏ የኡራኒየም ዋናዋ ምጭ ናት፤ ለአሜሪካም ቢሆን ዋና የድሮን መቻ ማዕከል ናት»

የአዉሮጳና አፍሪቃ መንግስታት፤ አካባቢያዊና ዓለማቀፍዊ ድርጅቶች፤ በኒጀር ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በማውገዝ ከስልጣናቸው የተወገዱት ፕሬዝድንት ባሙዝ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱና ህገ-መንግስታዊ ስራቱ እንዲከበር ጥሪ ሲያስተላለፉ፤ የቀን ገደብ በማስቀመጥ ዛቻ ቢያሰሙም፤ እስካሁን ግን ሰሚ አላገኙም። በተለይ  የምራብ አፍሪቃ የኢኮኖሚ ማህብረሰብ «ኢኮዋስ» የተባለውና ኒጀርን ጨምሮ 15 አባል አገሮች የተካተቱበት ስብስብ፤  ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙምን ከስልጣን በማስወገድ ስልጣን የያዙትን ወታደራዊ መሪዎች እስከካለፈው እሁድ ድረስ ወደ መንበራቸው እንዲመልሱና ህገ-መንግስታዊ ስራቱን እንዲያከብሩ፤ ይህ ክልሆነ ግን የኃይል እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀው ነበር። የቀድሞ ቅኝ ገዥዋን ፈረንሳይን ጨምሮ ሊሎች የምዕራብ መንግስታትም  የኢኮኖሚ ትብብሮችንና የፋይናንስ ድጋፎችን በማቆም የኤኮዋስን ጥሪና ማስጥንቀቂያ አስተጋብተውም ነበር። ሆኖም ግን ወታደራዊ ሁንታው እስካሁን  ከሁሉም አቅጣጫ ለመጡት ጥያቀዎችና ወታደራዊ ዛቻዎች የሚበገር አልመሰለም።

ብዙዎቹ ኒጀሮችም የውጭ መንግስታት በወታደራዊ ሀይል ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉትን ሙከራ በጽኑ እንደሚቃወሙ አደባባይ በመውጣት ጭምር ሲገልጹና፤  ለመፈንቅለ መንግስቱ  መሪዎችም ድጋፋቸውን ሲያሳዩ ተውስተውሏል ። ወታደራዊ ሁንታው በበኩሉ ከጎረቤት አገሮችና ከፈረንሳይ ጭምር እየተደረገበት ላለው ጫና ምላሽ፤ ደንበሩን በመዝጋትና ከፈረንሳይ ጋር ያለውን ወታደራዊ ግንኑነት በማቋረጥ የገለጸ  ሲሆን፤ ካለፈው እሁድ ጀምሮም  የአገሪቱ ኣየር ክልል የተዘጋ መሆኑን በወታደርዊው አመራር ቃል አቀባይ ኮሌኔል አማዶ አብድራሜ በኩል በአገሪቱ ቴሌቪዥን ተገልጿል። “ ከጎሬበት አገሮች በወታደራዊ ሀይል ጣልቃ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ስለታወቀ፤  የኒጀር የአየር ከልል ከእሁድ ነሀሴ 6 ጀምሮ ላልተወሰነ ግዜ  ለሁሉም የአየር ማረፊያዎች ዝግ ሆኖ ይቆያል፤ በማለት  ይህንን ክልከላ ተላለፎ የኒጀርን የአየር ክልል በሚጥስ ግን ተገገቢው  እርምጃ የሚወስድበት መሆኑን አስታውቀዋል። የምራብ አፍሪቃ የኢኮኖሚ ማህብረሰብ-ኢኮዋስ፤ ለኒጀር ወታደራዊ መሪዎች አስቀምጦት የነበረው የግዜ ገደብ ባለፈው ዕሁድ ማለፉን ተከትሎ የመሪዎቹ ልዩ ስብሰባ አቡጃ ላይ በሚቀጥለው ሀሙስ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል። ኢኮዋስ ቀደም ሲል በዋናነት የኢኮኖሚ ትብብሮችንና  የንግድ ግንኑነቶችን እንዲያሳልጥ ታስቦ የተቁቋመ ቢሆንም፤ በአካባቢው በሚደረጉ ተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግስቶችና ግጭቶች ምክንያት አላማውን በተፈለገው መጠን ሊያሳካ እንዳልቻለ ነው የሚነገረው። ከዚህ ቀደም በተደረጉ መፈንቅለ  መንግስቶች በወታደራዊ  ኃይል ጭምር ጣልቃ በመግባት የሲቪል አስተዳደሮችን ለመመለስ ጥረት ያደረገ ቢሆንም፤ በኒጀር ጉዳይ ግን በወታደራዊ ኃይል ጣልቃ የመግባቱ ሀስብ፤ ከማህበሩ አባሎች ውስጥ ከማሊና ቡርኪና ፋሶ ብርቱ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፤ በዋናዋ የድርጅቱ አባል ናይጀሪያ ምክር ቤትም ድጋፍ አላገኘም ተብሏል። ከዚህም በቀር የድርጅቱ አባል ካልሆኑ እንደ ቻድና አልጀሪያ የመሳሰሉ የኒጀር ጎረቤት አገሮች፤የሀይል አማራጭን እንደሚቃወሙ ነው የሚታወቀው። ቀድሞ የአሜሪካ ዲፖሎማት የነበሩት ሚስተር ዊሊያም ሎሬንስ አስተያየትም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በአካባቢው ሌላ ሰፊ የጦርነት ሜዳ የሚከፍት ሊሆን ይችላል። “ እዚህ ቦታ አካባቢዊ ጦርነት ሊጀመር ይችላል። ምክኒያቱም በአንድ በኩል ኒጀር ማሊና ቡርኪና ፋሶ ምናልባትም በሩሲያ እየተደገፉ በሌሎቹ የኢኮዋስ አባል አገሮች አንጻር ሊሰለፉ ይችላሉ” በማለት ይህ ደግሞ አደገኛ በመሆኑና  ሰላምዊ መፍትሄ መሻቱ የሚሻል መሆኑን አሳስበዋል።

የኒጀር መፈነቅለ መንግስት ከሁሉ በተለየ ሁኒታ የቀድሞ ቅኝ ገዣዋን ፈረንሳይንና አሜሪካንን እንደሚያያሳስብ ነው በቡዎች ዘንድ የሚታመነው። ሁለቱም አገሮች ጽንፈኞችን ለመዋጋት በሚል ወታደራዊ ሰፈሮች የገነቡባት ሲሆን፤  ለፈንረንሳይ ደግሞ  ለኒውክለር ኃይሏ ግብአት ኡራኒየም ማዕድን ዋናዋ ምጭ ናት። ለአሜሪካም  ቢሆን ዋና የድሮን ቤዝ የሚገኝባት ስትራቴጂካዊት አገር ስትሆን፤ የተከስተውን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ሩሲያ እጇን እንዳታስገባ  የምትሰጋ መሆኑንም የፖለቲካ ተንታኖች ይናገራሉ።

በመሆኑም ሀሙስ የሚሰበሰቡት የምዕራብ አፍሪቃ የኢኮኖሚ ማህብረሰብ አባል አገሮች መሪዎች ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ባይታወቅም፤ ወታደራዊ አማራጩ ግን ለጊዜው እንደሚገቱት ነው የሚገመተው። ጣሊያንን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራብ መንግስታት ኢኮዋስ ያስቀመጠውን የግዜ ገደብ እንዲያራዝም ያሳሰቡ ሲሆን፤ ተስብስቢዎቹ የኢኮዋስ መውሪዎችም በዚሁ መንፈስ የፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎችን ቅድሚያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

ገበያው ንጉሴ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ