“ለኦሮሞ ሰላም ይገባዋል” ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ
ዓርብ፣ ግንቦት 23 2016
በኦሮሚያ ሰላም እንዲሰፍን እና የክልሉ ህብረተሰብ ወደ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ህይወት እንዲመለስ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አሳሰቡ፡፡የክልሉ ፕሬዝዳንት በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት ዘለግ ባለው ጽሁፍ ህገወጥነት የሚያስተዳድሩትን ክልል መፈተኑን ጠቁመዋል፡፡ የተለያዩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ግን መንግስት የሚቀርባቸውን የሰላም ጥሪዎች በተግባርም እንዲደግፈው እየጠየቁ ነው፡፡
የሰላም ጥሪው አስፈላጊነት
ሰላም፣ ሰላም፣ አሁንም ሰላም በሚል መልእክታቸውን ዘርዝረው ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሚያስተዳድሩት ክልላቸው እንደ ህዝብ ገዳ የመሰለ ስርዓት እና በተረጋጋ ሁኔታ የመኖር እድል እያለው እነዚህ ነገሮች ነግሷል ባሉት “ህገወጥነት” መፈተኑን አብራርተዋል፡፡
“ዛሬ ትናንት አይደለም” ያሉት ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሞ ህዝብ አረጋግጧል ባሉት እድሉን በራሱ የመወሰን መብት፤ የራሱን ዕድል በአፈሙዝ እና በጫካ ትግል የማረጋገት ምዕራፍ በማለፉ አያስፈልግም፤ የሰላማዊ ትግሉ ምዕዳር ተከፍቷል ሲሉም ሃሳባቸውን ዘርዝረዋል፡፡በኦሮምያ ክልሉ ግጭት የሲቪል ዜጎች ፈተና
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ በመግለጫቸው “ህዝቡ አግኝቷል” ያሉት የነጻነት መንገድ “ባሁን ወቅት ታጥቆ ጫካ ውስጥ በሚንቀሳቀስ” ባሉት አካል መስተጓጎሉን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት በክልሉ የተካሄደው ግጭት አለመረጋጋትን አስከትሎ “ብዙ አሳጥቶናል” ነው ያሉት፡፡
ሰላም ለህዝብ መብት መከበር
“ነገሮች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ተጠናቀው ሰላምና መረጋጋት መስፈን እንዳለበት እናምናለን” ሲሉ የመንግስታቸውን አቋም የገለጹት አቶ ሽመልስ አስከፊ ያሉት ጭቆና በኦሮሞ ህዝብ ላይ መፈጸሙ ቆሞ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በመግባት እራሱን የማልማት መብቱ እንዲከበርለት ያስፈልጋል በማለት ሀሳባቸውን ዘርዝረዋልም፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በህግ ከተሰጠው የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱ ጎን ለጎን በነባር የማህበረሰቡ እሴት መሰረት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተጀምሯል ያሉት የሰላም ጥሪዎችን አሁንም እንደቀጠለ ነው ብለዋልም፡፡
መሰል የሰላም ጥሪዎች መንግስትን በኃይል ለሚወጉት ስቀርብ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ተደጋጋሚ ጥሪዎች ብቻም ሳይሆን የተጀመሩ ፊት ለፊት ተገናኝቶ የመወያየት እድሎችም ሳይሰምሩ ሲከሽፉ ታይተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩ ተከታይ ጥሪ ባሁን ወቅት የተሰማም በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች ግጭቶች አለማቧራታቸው ብቻ ሳይሆን የተዋጊዎች ምልመላዎችም ጎልተው በቀጠሉበት ወቅት ነው፡፡የጠቅላይ ሚንስትሩ የሰላም ጥሪ ፤ ሰላማዊ ምላሽ እንዴት ያግኝ?
የሰላም ጥሪዎች በተግባር እንዲደገፉ ስለቀረበው ጥሪ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ፖለቲከኛ ደስታ ድንቃ በዚሁ ሀሳብ ላይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየትም “በቃል የሚነገሩ መሰል አስተያየቶች በተግባር ልደገፉ ይገባል” ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይሻል ነው ያሉት፡፡
ባለፉት ወራት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማሰማቱን አስታውሰው ዛሬ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ላይ አስተያየት የሰጡት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የውጭ ጉዳይ ሃላፊና የፖሊቲካ ተንታኝ ጀዋር ሙሃመድ ለጦርነት ከመቀስቀስ ሰላምን ማወጅ ጥሩ እምርታ ቢሆንም ጥሪው በተግባር ሊታጀብ ይገባል ብለዋል፡፡ ፖለቲከኛ ጃዋር “በፍርድ ቤት በነጻ የተሰናበቱ” ያሏቸውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ፖለቲከኞችን መፍታት እና በቅርቡ የተገደሉትን የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ዑርጌሳን ፍትህ ማረጋገጥ ለቁርጠኝነቱ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይገባል ሲሉም ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው አቶ ደስታ ዲንቃም ከመንግስት ባሻገር ስለ የፖለቲካ ተቋማት አስተዋጽኦ ተጠይቀው፤ “በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ የሰላም ትሪና ተማጽእኖ ከማቅረብ ቦዝነው አያውቁም” ብለዋል፡፡የኦሮሚያ የተራዘመ ግጭት በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ተስፋፍቶ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች ማድረሱ ተደጋግሞ ተዘግቧል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ፀሐይ ጫኔ
እሽቴ በቀለ