ለከፋ ረሃብ የተጋለጡት የአማራ ክልል አካባቢዎች
ዓርብ፣ መስከረም 14 2014
ከጦርነት አካባቢ የተፈናቀሉና በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች አንዳንዶቹ እርዳታ አላገኘንም ሲሉ ሌሎች ደግሞ የእለት ድጋፍ አግኝተናል ብለዋል፣ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ደግሞ ተደራሽልሆኑትን ለመርዳት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ መንግስት የህግ ማስከበር፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የህልውና ዘመቻ ብሎ በጠራቸው ጦርነቶች በአማራና በትግራይ ክለሎች በርካታ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያና በየዘመድ ቤቱ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ዲያቆን ተስፋሁን ባያብል ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በጦርነት ቀጠና ያሉ ነዋሪዎችን መድረስ ባለመቻሉ ለከፍተኛ ርሀብ ተጋልጠዋል፡፡
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ደስታ “በብሔረሰብ አስተዳደሩ 90 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ ለርሀብ አደጋ መጋለጡን ጠቁመው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለዋግኽምራ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም” ሲሉ ከስሰዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደሴና በባሕር ዳር የሚገኙ የሰሜን ወሎና የዋግኽምራ ተፈናቃዮች እርዳታ አላገኘንም የሚል አቤቱታ ሲያቀርቡ ሌሎች ደግሞ በክፍፍል ወቅት የሚፈጠር ችግር ካልሆነ እርዳታ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ለተፈናቃዮች አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ አመልክተዋል፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊውም እርዳታ እየደረሰ እንደሆነ ነው ያረጋገጡት፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገ/ መስቀል በበኩላቸው ከህብረተሰቡና ከመንግስት ድጋፍ እተደረገ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፤
የአማራ ክልል መንግስት በተደጋጋሚ እንዳስታወቀው በህግ ማስከበሩና በህልውና ዘመቻዎች በተደረጉ ጦርነቶች ብቻ ከ500ሺህ በላይ ወገኖች በዋናነት ከሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎና፣ ዋግኽምራ ዘካባቢዎች ተፈናቅለዋል፣ 4 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ለከፋ ረሀብ ተጋልጠዋል፡፡ የዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች የሚያደርጉትን ተሳትፎ በተመለከተ የፌደራል አደጋ ስጋት አመራር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴን በስልክ ጠየቄያቸው ነበር፣ ሆኖም በጉዳዩ ላይ በቅርቡ መግለጫ ሰጥቸበታለሁ በማለታቸው አሁናዊ ሁኔታውን ማካተት አልቻልሁም።
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ