ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለመከላከል ውይይት
ረቡዕ፣ ሰኔ 7 2015በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ መንገድ የተሻለ ሕይወት ወደሚያማትሩባቸው ሀገራት እንደሚሰደዱ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ግምታዊ መረጃ ያመለክታል ። ለአብነት ያህልም የመን ውስጥ ብቻ ከመቶ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ከሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል ። ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ለስደት ከሚዳረጉባቸው መንገዶች ደግሞ ድሬደዋ እና የምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙባቸው መሆኑም ተጠቅሷል ። ችግሩን ለመግታት የሚቻልበት የመከላከል መንገድ ለመቀየድ ድሬደዋ ከተማ ውስጥ ውይይት ተካሂዷል ።
አቶ ሳሙኤል በሕገወጥ መንገድ ወደ የመን ተሰደው ከተመለሱ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው። በአሁን ሰዓት በድሬደዋ ከስደት ለተመለሱ ዜጎች በተመቻቸው የሥራ እድል እየተጠቀመ የሚገኝ ሲሆን ከእርሱ ተመክሮ በመነሳት ሰው ከሀገሩ ባይሰደድ መልካም እንደሆን ይናገራል። በሀገሪቱ ያለው እውነታ ግን ከዚህ በብዙ የተለየ ነው። በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል እና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍ እና ክትትል መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ተግይበሉ ህገወጥ ጉዞው በተለያዩ አካባቢ መንገዶች የሚከናወን መሆኑን ጠቅሰው በግምት ከመቶ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ዜጎች በየዓመቱ በህገወጥ መንገድ እንደሚሄዱ ተናግረዋል። ኃላፊው እንደሚሉት አብዛኞቹ ተሰዳጆች ከአማራ፣ ከኦሮሚያ እና ከትግራይ ክልል መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ድሬደዋን ጨምሮ የምስራቅ ሀገሪቱ አካባቢዎች ዋነኛ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚካሄድበትና በሰው የሚነግዱ ደላሎች የበዙበት እንደሆን ያነሱት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የአካባቢው ተፅዕኖ ፈጣሪ አካላት ድርጊቱን በመከላከል የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል ። ሚንስትሯ ውጭ ሄደው መሥራት ለሚፈልጉ ዜጎች ሕጋዊ መንገድ መመቻቸቱን ተናግረዋል። በሕገወጥ መንገድ ለመሰደድ ወደ ከተማይቱ በሚመጡ አካላት የተለያዩ ችግሮች እያጋጠሙ መሆናቸው በሚነሳባት ድሬደዋ ችግሩን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን በተቀናጀ መንገድ መሥራት መጀመሩ ተገልጿል።
ድርጊቱን ለመከላከል ያስችላል የተባለውን የተቀናጀ ንቅናቄ ለመፍጠር ሰሞኑን በድሬደዋ ከተማ በተካሄደ መድረክ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትር የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር፣ የሀረሪ እና የሶማሌ ክልሎች እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
መሳይ ተክሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ