1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት የደመወዝ ቦርድ የሚያቋቁመውን ደንብ እንዲያወጣ ኢሠማኮ ጠየቀ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 26 2014

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ዝቅተኛ ደመወዝ የሚወስነውን ቦርድ የሚያቋቁም ደንብ እንዲያወጣ ለመንግሥት ጥሪ አቀረበ። ደንቡ በቀድሞው የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀ ነው። የኢሠማኮ ፕሬዝደንት ካሳሁን ፎሎ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጉዳይን ጨምሮ በሠራተኞች አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ለዶይቼ ቬለ ማብራሪያ ሰጥተዋል

https://p.dw.com/p/4ApOz
Äthiopien Kassahun Follo
ምስል CETU

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ከኢሠማኮ ፕሬዝደንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ጋር የተደረገ ቃለ-መጠይቅ

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን በ2011 በጸደቀው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ በተደነገገው መሠረት ዝቅተኛ ደመወዝ የመወሰን ሥልጣን የሚሰጠውን ቦርድ የሚያቋቁመውን ደንብ እንዲያወጣ ለጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ጥያቄ አቀረበ። ቦርዱን የሚያቋቁመው ደንብ በቀድሞው የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሁኑ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። 

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በ2013 በአገሪቱ በነበረው አለመረጋጋት እና በአመቱ መጨረሻ የተካሔደው ስድስተኛው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ቦርዱን የሚያቋቁመው ደንብ እንዲዘገይ ማስገደዳቸውን ተናግረዋል።

"አዲሱ መንግሥት እንደተቋቋመ እና ካቢኔ እንደተዋቀረ ይኸ ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ ይታያል" የሚል መልስ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ተሰጥቶ እንደነበር የተናገሩት አቶ ካሳሁን "እስካሁን ድረስ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይኸ ደንብ አልታየም" ሲሉ ተናግረዋል። በጥቅምት 2013 የተቋቋመው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ "ካሁን አሁን" በጉዳዩ ላይ ውይይት ያደርጋል በሚል ይጠበቅ እንደነበር የገለጹት አቶ ካሳሁን ከጥቅምት በኋላ "ለመቆየቱ በእኛ በኩል አሳማኝ የሆነ ምክንያት የለም" ሲሉ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን "የደመወዝ ቦርድ መቋቋሚያ ደንብ በሚንስትሮች ምክር ቤት ባለመውጣቱ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያልተገባ ስለሆነ መንግሥት ልዩ ትኩረት በመስጠት የማቋቋሚያ ደንቡን እንዲያወጣ" የዓለም የሠራተኞች ቀን ሲከበር ጥሪ አቅርቧል። ከኮንፌዴሬሽኑ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥት የሠራተኞችን ዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ለመወሰን እና የደመወዝ ቦርድ ለማቋቋም የጀመረውን ጥረት እንዲያፋጥን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 አሳስቧል።

Äthiopien Textilindustrie Fabrik Näherinnen
በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የመወሰንን ጉዳይ አቶ ካሳሁን "ከአንገብጋቢም እጅግ አንገብጋቢ" ይሉታል። ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ የበረታው እና "ሠራተኛውን ክፍል እጅግ እየተፈታተነ" የሚገኘው የኑሮ ውድነት ዋንኛ ምክንያት ነው።ምስል Jeroen van Loon

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 27 ቀን 2011 ያጸደቀው የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ "የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት፤ የሥራ ገበያ ሁኔታ እና የመሳሰሉትን እያስጠና ዝቅተኛ ደመወዝ የሚወስን" የደመወዝ ቦርድ እንደሚቋቋም ይደነግጋል። በአዋጁ መሠረት "የመንግሥት፤ የአሠሪ እና ሠራተኛ ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት" የሚያካትተውን ቦርድ ማቋቋም፣ ተግባር እና ኃላፊነቱን መወሰን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰጠ ኃላፊነት ነው።  

በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የመወሰንን ጉዳይ አቶ ካሳሁን "ከአንገብጋቢም እጅግ አንገብጋቢ" ይሉታል። ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ የበረታው እና "ሠራተኛውን ክፍል እጅግ እየተፈታተነ" የሚገኘው የኑሮ ውድነት ዋንኛ ምክንያት ነው። የኢትዮጵያ ሠራተኞች የደመወዝ መጠን እና በገበያው የሸቀጦች ዋጋ "ፍጹም የማይገናኝ ሆኗል" የሚሉት አቶ ካሳሁን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቋቋሙ የኢንዱትሪ ፓርኮች ተቀጣሪዎች የሚከፈላቸውን የደመወዝ መጠን በማሳያነት በማንሳት የችግሩን ብርታት ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ አስረድተዋል። 

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ800 እስከ 2000 ብር ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ካሳሁን ነገር ግን "በኢትዮጵያ አምስት ሊትር ዘይት 1 ሺሕ 200 ብር ገብቷል። በአንድ ሺሕ ብር [ሠራተኛው] ምን ይበላል ተብሎ ይታሰባል?" ሲሉ ይጠይቃሉ። "ገበሬው በሚያዋጣው መንገድ ጨምሮ ይሸጣል። ነጋዴው ከገበሬው የገዛውን ሠራተኛው ላይ ገንዘብ ጨምሮ ይሸጣል። ሠራተኛው ምን ይሁን?" ሲሉ የሚጠይቁት የኢሠማኮ ፕሬዝደንት "ሠራተኛው በልቶ ማደር አልቻለም። መኖርም አልቻለም" ሲሉ ጫናውን ዘርዝረዋል። 

Äthiopien Der Industriepark Adama
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ800 እስከ 2000 ብር ደመወዝ የሚከፈላቸው ሠራተኞች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ካሳሁን ነገር ግን "በኢትዮጵያ አምስት ሊትር ዘይት 1 ሺሕ 200 ብር ገብቷል። በአንድ ሺሕ ብር [ሠራተኛው] ምን ይበላል ተብሎ ይታሰባል?" ሲሉ ይጠይቃሉ።ምስል Eshete Bekele Tekle/DW

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ የሠራተኞችን ዝቅተኛ ደመወዝ ለመወሰን የተዘጋጀ የሕግ ረቂቅ ለምኒስትሮች ምክር ቤት እንደቀረበ መረዳቱን አስታውቋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያጸድቀዋል ተብሎ በሚጠበቀው ደንብ ላይ ባለፈው ዓመት ውይይት መደረጉን የሚያስታውሱት አቶ ካሳሁን ግን "ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ስለመቅረቡ እስካሁኑ ሰዓት ድረስ መረጃ የለኝም" ሲሉ ተናግረዋል።

የዓለም የሠራተኞች ቀን ሲከበር የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ባወጣው መግለጫ "የሠራተኛው በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብት በህግ የተደነገገ ቢሆንም አብዛኛው የግል ድርጅቶች አሠሪዎች በተለይም የውጭ ካምፓኒዎች ሠራተኛው እንዳይደራጁ መከልከል፣ ከተደራጁም በኃላ ማህበሩን አለመቀበልና የተመረጡ መሪዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ማህበሩን ማፍረስ፣ አንዳንድ አሠሪዎች ከአንዳንድ ሥነ-ምግባር የጎደላቸው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ አስፈፃሚ አካላት ጋር በመመሳጠር ሠራተኛው መደራደር እንዳይችል እያደረጉ" መሆናቸውን ገልጿል። ለዚህም አሠሪዎች እና የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት "የሠራተኛውን የመደራጀትና የመደራደር መብት እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ" ጠይቋል።

አሠሪዎች "በሥራ ቦታ የሙያ ደህንነት እና ጤንነት መከላከልን አስመልክቶ የወጡ ህጎች በአብዛኛው አሰሪዎች" ባለማክበራቸው ሠራተኞች ለሞት እና ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ ገልጾ ኢሠማኮ "የሥራ ቦታ የሙያ ደህንነት እና ጤንነትን አስመልክቶ የወጡ ሕጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ" ጥሪ አቅርቧል። ኢሠማኮ ሚያዚያ 2ዐ ቀን 2ዐ14 ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ "ግጭት እና ጦርነት ቆሞ ዘላቂ ሰላም የሚመጣበትን ሁኔታ መንግሥት እንዲያመቻች" ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ጉዳይን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ከዶይቼ ቬለ ጋር ቃለ-መጠይቅ አድርገዋል። ቃለ-መጠይቁን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።

እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ