1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የእስራኤልና ሐማስ ጦርነት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 1 2016

እስራኤል በ2021 ጋዛን በብረት አጥር ዘጋች።አጥሩ ከግብፅ ድንበር ጀምሮ እስከ ሜድትራኒያን ባሕር ጠረፍ 65 ኪሎ ሜትር ይረዝማል።140 ሺሕ ቶን ብረት ተገጥግጦበታል።ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶበታል።የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚያነፈንፉ፣ የሚከታተሉና የሚጠቁሙ አንቴናዎች፣ሬዳሮች፣ ሴንሰሮች ተገጥመዉበታል።

https://p.dw.com/p/4XJsY
የእስራኤል የጦር አዉሮፕላኖች ጋዛን በተደጋጋሚ ደብድበዋታል
የጋዛ ከተማ በእስራኤል አዉሮፕላን ድብደባ ስትጋይምስል Mahmud Hams/AFP

ማብቂያ የሌለዉ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጦርነት

ጥቅምት 6፣1973 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ቅዳሜ።በወታደራዊ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 1405 የግብፅ ጦር ከደቡብ-ምዕራብ፣ የሶሪያ ተባባሪዉ ከሰሜን-ምሥራቅ ሚሳዬል፣ሞርታር፣ታንክና የአዉሮፕላን ቦምባቸዉን በእስራል ጠላታቸዉ ይዞታ ላይ ያዘንቡት ገቡ።ከአንድ ሰዓት በኋላ የአረቦች ጦር ከእስራኤል ግራ ቀኝ የሚገኙትን የእስራኤል ጦርን ጠንካራ ምሽጎች ባርሌቭና የጎላን ኮረብታ ምሽጎችን ሰባበሩ።ባለፈዉ አርብ 50 ዓመቱ።ጥቅምት 7፣2023።ቅዳሜ።ከማለዳዉ 12፣30 አክራሪዉ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ የሮኬት ወዦቦዉን በእስራኤል ከተማ-መንደሮች ላይ ያወርደዉ ያዘ።ዕሁድ የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቡላሕ የእስራኤል ጦርን ይዞታ በመድፍና ሮኬት ደበደበ።አዲስ ዘመን፣ አዲስ ትዉልድ፣ አዲስ ጦር መሳሪያ፣ አዲስ ቡድን፣ አሮጌ ጦርነት።ነባር እልቂት።መካከለኛዉ ምስራቅ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያም ኔታንያሁ  ባለፈዉ ቅዳሜ እስራኤል ላይ የደረሰዉ ጥቃት ከዚሕ ቀደም ታይቶ አይታወቅም ብለዋል።«ዛሬ የሆነዉ እስራኤል ዉስጥ ታይቶ አያዉቅም።ወደፊት ዳግም እንዳይደርስም እናደርጋለን።»

የጋዛዉ ነዋሪ ልጁን ታቅፎ ሲሸሽ
የእስራኤል የብቀላ ድብደባ ለጋዛ ህዝብ መቅሰፍት ነዉምስል REUTERS/Stringer

የወደፊቱን በርግጥ አናዉቅም።ከዚሕ ቀደም ግን ሆኖ ነበር።1973።ልክ እንደ ኔታንያሁ ሁሉ የያኔዋ ጠቅላይ ሚንስትር ጎልዳ ሚርም ከ1972 ማብቂያ ጀምሮ ካይሮና ደማስቆ ላይ የሚቀለጣጠፈዉን ወታደራዊ ዝግጅት በቅጡ አላወቁትም።

በተለይ የግብፅ የጦርና የስለላ ባለሙያዎች አንዴ የጥቅምት 23 የድል ቀን በዓል፣ ሌላ ጊዜ የወታደራዊ ብቃት ልምምድ እያሉ የሰጡት ሽፋን የእስራኤልና የዩናይትድ ስቴትስ ሰላዮችን ለማዘናገት ጠቅሟቸዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ጎልዳ ሚር ኋላ እንዳሉት ግብፅና እስራኤል ጦርነት ለመክፈት መዘጋጀታቸዉን የሰሙት ጥቅምት 5 ለ6 አጥቢያ ከማለዳዉ 10 ሰዓት ነበር።ጎልዳ ሚር የጦርና የስለላ ሹማምንቶቻቸዉን አነጋግረዉ ስብሰባቸዉን እንደጨረሱ የግብፅና የሶሪያ ጦር የእስራኤልን ኢላማዎዎች ያደባዩት ያዙ።ጥቅምት 6፣ 1973።

«ጦርነቱ የፈነዳዉ ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ ነዉ።ይሁንና ከማለዳዉ  10 ሰዓት ላይ  በሁለቱም ድንበሮች በኩል፣ ከሶሪያና በግብፅ በተመሳሳይ ጊዜ ጦርነት እንደሚጀመር እርግጠኛ መረጃ አግኝተን ነበር።»

«የዮም ኩፑር ጦርነት፣የረመዳን ጦርነት፣ 4ኛዉ የእስራኤልና የአረቦች ጦርነት» ወዘተ በሚባለዉ ጦርነት የመጨረሻ መጨረሻዉ ድል አድራጊ  እስራኤል ነበረች።ይሁንና በዉጊያዉ የመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት የአረቦች ኃይል ያስመዘገበዉ የበላይነት ከ1948 ጀምሮ «የማይደፈር» የሚባለዉ የእስራኤል ጦርና የአሜሪካኖች ጦር መሳሪያ ከምድራዊ አረባዊ ኃይል ዉጪ እንዳልሆነ ያስመሰከረ ነበር።

በ50ኛ ዓመቱ ዘንድሮ ለእስራኤል-አሜሪካኖች አስደንጋጩ፣ ለተቀረዉ ዓለም  አስገራሚዉ ጥቃት ከጋዛ ተደገመ።

ሰዉ፣ድግሱ፣መኪኖችም አልተረፉም
የሐማስ ታጣቂዎች የኪቡትስ ከተማን ባጠቁበት ወቅትምስል SOUTH FIRST RESPONDERS / AFP

እርግጥ ነዉ ከዚሕ ቀደም የእስራኤል «ጠላት» የነበሩት የካይሮ፣ የአማን፣ የራባት፣  ያኔ እንደ ነፃ ሐገር የማይታወቁት የአቡዳቢና የማናማ፣ የፍልስጤም ገዢዎች ጭምር  የዋሽግተን-ቴልአቪቭ-ለንደን-ብራስልሶችን ድጋፍ ፍለጋ የእስራኤል የዲፕሎማሲ ሸሪኮች፣ ወይም ወዳጅ ባይባሉ «ጠላት« አይደሉም።

ሪያዶች ፍልስጤሞችን ገለል-ገሸሽ አድርገዉ እነ ካይሮን ለመከተል አንድ-ሁለት እያሉ ነዉ።ቀጠር፤ኩዌት፣ ኦማን የሌሎቹን ዱካ ለመከተል አቆብቁበዋል።ደማስቆ ደክማለች።ኢራቅ፣ሊቢያ፣የመን፣ ሱዳንና ሊባኖስ ከስም ባለፍ ጠላትና ወዳጅ የሚመርጥላቸዉ ጠንካራ መንግስታት የላቸዉም።

በዚሕ ስሌት ኔታንያሁ ልክ ናቸዉ።እስራኤል የምትወጋዉ፣ የምዕራቡ ዓለም በአሸባሪነት የፈረጀዉ፣እንደ ቀንደኛ ጠላት የሚያሳድደዉ፣ መዉጪያ መግቢያዋ በእስራኤልና በግብፅ ጦር ኃይል በታጠረ አንዲት ትንሽ ግዛት ዉስጥ የሸመቀዉ ተራ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የዓለምን አስፈሪ፣ ምሕረት የለሽ፣ጠንካራ ጦርን ከበባና ቁጥጥርን ሰብሮ ያደረገዉን ማድረጉ በርግጥ ለእስራኤሎች አስደንጋጭ፣ለአረቦች አጃኢብ-ምናልባት ለሐበሻ ጉድ ያሰኝ ይሆናል።ብቻ ቅዳሜ-የሆነዉ ሆነ።

 አስደንጋጩ ነገር አስደናቂነቱ ነዉ።ከ1967 ጀምሮ የእስራኤል ወታደሮችና ሰላዮች በፈለጉበት ሰዓት፣የፈለጉትን የሚገድሉ፣ የሚጠረጥሩትን እንደ ዶሮ እያነቁ የሚያስሩ፣የሚያግቱባትን የጋዛ ሠርጥን እስራኤል በ2005 ለቅቃ ወጣች።በ2007 አሸባሪዉ ሐማስ ጋዛን ተቆጣጠረ።

እስራኤል በ2021 የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎችን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ጋዛን በብረት አጥር ዘጋች።አጥሩ ከግብፅ ድንበር ጀምሮ እስከ ሜድትራኒያን ባሕር ጠረፍ 65 ኪሎ ሜትር ይረዝማል።140 ሺሕ ቶን ብረት ተገጥግጦበታል።ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶበታል።የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚያነፈንፉ፣ የሚከታተሉና የሚጠቁሙ አንቴናዎች፣ሬዳሮች፣ ሴንሰሮች ተገጥመዉበታል።

የእስራኤል በጎ ፍቃደኞች ቁስለኞችን ሲረዱ
በሐማስ ጥቃት የቆሰሉ እስራኤላዉያን ሕክምና ሲደረግላቸዉምስል Vita Jablokova/DW

በጥንካሬና ዘመናዊነቱ የዓለም ብቸኛዉ አጥር ታሕሳስ 2021 ሲመረቅ የታዘበ ጋዜጠኛ ጋዘን «በዓለም ትልቁ ጣራ የለሽ እስር ቤት» ብሏት ነበር።ጋዛ 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ተፋፍጎ ይኖርባታል።የሐማስ አሸባሪዎች እስራኤልን ለማጥቃት በዚያች ትንሽ ግዛት ምናልባት ለወራት ሲያቀለጣጥፉ ከሰማይ አሞራ የሚቀልቡት የእስራኤል ወታደሮችና ሰላዮች ይሰሩ የነበረዉን እስካሁን አላወቅንም።

ቅዳሜ ማለዳ የሐማስ ሚሳዬሎች እስከ ቴል አቪቭ የሚገኙ የእስራኤል ከተማ፣ መንደሮች፣ የሠፈራ ጣቢያዎችንና የጦር ሠፈሮችን ይቀጠቅጡ ያዙ።በተኩሱ መሐል ገሚሶቹ ታጣቂዎቹ በዚያ ጠንካራ፣ ዘመናይ የብረት ግርግዳ ላይ የተለጣጠፉ መሳሪዎችን እያፈኑ፤ ብረቱን እየቀረደዱ ተሻገሩ።ሌሎች ባልደረቦቻቸዉ በባሕር፣ ቀሪዎቹ ሰዉነት ላይ በሚገጠም መንሳፈሪያ እየታገዙ በአየር ደረሱላቸዉ።ከዚያማ አሽካሎን፣ጌቪን ኪቡትዝ፣ ሬይም፣ስዴሮት ባጠቃላይ 22 የእስራኤል ከተማ፣ መንደር፣ የሠፈራ መንደሮች ጥይት፣ቦምብ እየተዘራ አስከሬን ይመረትባቸዉ ያዘ።

«ጥቂት ጓደኞቻችን ሞቱ፣ሌሎች ጥቂት ጓደኞቻችን ሆስፒታል ናቸዉ።» ይላል እሱ።እሷ ደግሞ፣ «በየደቂቃዉ ካሁን አሁን ሞትን ገደሉን ስንል ነበር።በሁሉም አቅጣጫ ተኩስ ነበር።እንዴት መግለፅ እንዳለብኝ አላዉቅም።»

ጋዛ በርግጥ ከ1967 ጀምሮ የአዉሮፕላን ቦምብ-ሚሳዬሉን ድምድምታ፣ግድያ፣እልቂቱን ለምዳዋለች።ቅዳሜ፣ ከጠዋቱ 3 ሰዓት 45 አስፈሪዉ የቦምብ ጥልማሞት በበቀል እልሕ እየተገፋ ጋዛ ከተማን፣ጀበሊያ፣ ራፋህና ሌሎችንም አካባቢዎች ያነድዳቸዉ ያዘ።ለጋዛዎች «ቂያማ»

ራፋሕ ዉስጥ ሟች-ቁስለኞችን ከፍርስራሽ ሥር ከሚፈልጉት አንዱ የተነገረን የለም አለ።

«ዜናዉን ሰምተናል።ይሁንና የቦምብ ድደባዉ ግን ድንገት ነዉ የተፈፀመዉ።ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ፣ ምንም ዓይነት ጥቆማ አልደረሰንም።»

ጠንካራ ዛቻና ማስጠንቀቂያዉ በርግጥ በቦምብ ሚሳዬሉ ድንደባ መሐል ደረሰ።ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ።

«ሐማስ የሰፈረባቸዉ፣ የተደበቀባቸዉ ወይም የሚንቀሳቀስባቸዉ ቦታዎች በሙሉ ያ የተረገመ ከተማ ወደ ፍርስራሽ ደሴትነት እንቀይረዋለን።የጋዛ ሰዎች እነዚሕን አካባቢዎች አሁኑኑ እንዲለቁ እነግራቸዋለሁ፤ ምክንያቱም በየትኛዉም ስፍራ እርምጃ እንወስዳለንና።»

ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር «ሐማስ ያለባቸዉን አካባቢዎች ወደ ፍርስራሽ ደሴት እንቀይራቸዋለን»ምስል Richard Drew/AP Photo/picture alliance

የጋዛ ከተማ ነዋሪዉ መሐመድ ሳዴቅ አላሕ «ወዴት?» ዓይነት ይላል።

«ምናልባት ተስፋ እንድንቆርጥ ግፊት ለማድረግ፣ ከፖለቲከኞች ይበልጥ ሰላማዊ ሰዎችን ነዉ ኢላማ የሚያደርጉት።ግን እንነግራቸዋለን።ተስፋ አንቆርጥም።እዚሁ እንኖራለን።ይሕ መሬታችን ነዉ።መሬታችንን ጥለን እንሔድም።»

ከቅዳሜ እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ በተደረገዉ ጥቃትና ግጭት 700 እስራኤላዉያን ተገድለዋል።ከ2 ሺሕ በላይ ቆስለዋል።በደርዘኖች እየተባለ ከመገለፁ በስተቀር ቁጥራቸዉ በዉል ያልተነገረ እስራኤላዉያን ታግተዋል።በፍልስጤሞች በኩል 560 ተገድለዋል።2 900 ቆስለዋል።

ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ቃል አቀባይም የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ማስጠንቀቂያ አጣጥሎ ነቅፎታል።

«የጠላታችን ጠቅላይ ሚንስትር ላሉት የምንሰጠዉ መልስ፣ ልናረጋግጥልዎት እንፈልጋለን።መጀመሪያ የጋዛ ነዋሪዎችንና ተፋላሚዎችን ማስፈራራት የከሰረ ጉዳይ ነዉ።»

የአየር፣የምድር፣የባሕር ድብደባ፣ ጥቃት መጠፋፋቱ ቀጥሏል።ከምክንያት ይልቅ ዉጤትን፣ ከሰላማዊ መፍትሔ ይበልጥ በኃይል ማስገበርን የሚመርጡት የዓለም ኃያል-ሐብታም ምዕራባዉያን መንግስታት አዉሮጳ መሐል እንኳን ሰላም ማስፈን አልቻሉም።በመካከለኛዉ ምስራቅ መተላለቅም ከ1948 ጀምሮ እንደኖሩበት በለዉ፣ግደለዉ፣ አጥፋዉ እናጥፋዉ ከማለት ሌላ የሰዎች እልቂት ፍጅት እንዲቆም እስካሁን የሚፈልጉ አይመስሉም።

«አስተዳደሬ ለእስራኤል ፀጥታ የሚሰጠዉ ድጋፍ ከአለት የጠነከረና የማይናወጥ ነዉ።የሚከተለዉን በተቻለኝ መጠን በግልፅ ልናገር፣ የእስራኤል ጠላት የሆነ ማንኛዉም ወገን ይሕን ጥቃት እንደ ጥሩ አጋጣሚ የሚጠቀምበት ጊዜ አይደለም።ዓለም እየተመለከተ ነዉ።ከዮርዳኖስ ንጉስ ጋር እየተገናኘሁ ነዉ።ከምክር ቤት አባላት ጋር ተነጋግሬያለሁ።እስራኤል የምትፈልገዉ ሁሉ እንዲሟላላት የብሔራዊ የደሕንነት ቡድን አባላት ከእስራኤል አቻዎቻቸዉ ጋር፣ ጦር ኃይሉ ከጦር ኃይሉ ጋር፣ ስለላዉ ከስለላዉ፣ ዲፕሎማቶች ከዲፕሎማቶች ጋር እንዲገኛኙ አዝዤያለሁ።»

ይላሉ።የዓለም ልዕለ ኃያል ሐገር መሪ ጆ ባይደን።የብሪታንያ፣ የፈረንሳይ፣ የሌሎች የምዕራብ ሐገራት መሪዎችና የአዉሮጳ ሕብረት ተጠሪዎችም ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስም ሐማስን በማዉገዝ፣እስራኤልን በመደገፉ ዘመቻ ላይ  ትናንት ጨመሩበት።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንምስል Evan Vucci/AP Photo/picture alliance

«እነዚሕ እርምጃዎች አረሜናዊ ናቸዉ።ያናድዳሉ።በየትኛዉም መንገድ ተገቢ ሊሆን አችልም።ዛሬ ቀትር ላይ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን በስልክ አነጋግሬያቸዉ ነበር።በዚሕ አዛኝ ጥቃት ወቅት ጀርመን በማይናወጥ ፅናት ከእስራኤል ጎን እንደምትቆም አረጋግጬላቸዋለሁ።የእስራኤል ደሕንነት የጀርመን ምንግስት አቋም ነዉ።ይሕ በተለይ ያሁኑን በመሰለ አስቸጋሪ ወቅት እዉን ይሆናል።በዚሑ መሰረት ገቢር እናደርገዋለን።»

በዩክሬን ሰበብ ከምዕራባዉያን መንግስታት ጋር ተዘዋዋሪ ጦርነት የገጠመችዉ ሩሲያ የፍልስጤምና የእስራኤልን  የዘመናት ጠብ፣ ግጭት ጦርነት ለማስቆም አብነቱ የሁለት-መንግሥት የተባለዉን ድርድር መቀጠል ነዉ ትላለች።የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ዛሬ እንዳሉት ያሁኑ ግጭት ከቆመ በኋላ ድርድሩ መቀጠል አለበት።ሩሲያ ባንድ ወቅት ፍልስጤምና እስራኤልን ለማደራደር ተሰይሞ የነበረዉ «አራትዮሽ» የተባለዉ ቡድን አባል ነበረች።የተከረችዉ የለም።የቱርክ ፕሬዝደንት ሬሰፕ ጠይብ ኤርዶኻን ግን መካከለኛዉ ምሥራቅን እስካሁን፣አሁኑም ሆነ ምናልባት ወደፊት የሚያወድመዉ ጦርነትና ግጭት የሚቆመዉ የእስራኤል ፍልስጤም ጠብ ሲፈታ ነዉ ባይ ናቸዉ።

«በአካባቢያችን ላለዉ ችግር መሰረታዊዉ ምክንያት የፍልስጤም ጉዳይ ነዉ።ፍትሐዊ መፍትሔ ካልተገኘ አካባቢያችን ሰላም እንደተጠማ ይኖራል።በመካከለኛዉ ምስራቅ ዘላቂ ሰላም ሊሰፍን የሚችለዉ ለፍልስጤምና እስራኤል ግጭት ዘላቂ መፍትሔ ሲበጅለት ነዉ።አሁንም፣ ሁል ጊዜ እንዳልነዉ፣አካባቢያዊ ሰላምን ለማስፈን  የሁለት-መንግስታት መፍትሔ ሐሳብን ገቢር ማድረግ ነዉ።»

«ጀርመን ከእስራኤል ጎን ትቆማለች» ሾልስ
የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስምስል Fabian Sommer/dpa/picture alliance

ዓለም ሠላም እንዲሆን የዓለም መሪዎች ይሹ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ