ዩክሬን-የፍልሚያ ምድር
ሰኞ፣ ሐምሌ 17 2015ዋሽግተን፣ ብራስልስ ለንደኖች ሞስኮዎች ላይ ይዝታሉ-ዘመናይ የጦር መሳሪያዎቻቸዉን ለዩክሬን ያስታጥቃሉ።ኪቮች ያቅራራሉ።
«ፖለቲካዊ ዉሳኔ ነዉ።ከዚያ በኋላ ይሕን ጦርነት እናሸንፋለን።»
የዩክሬኑ መከላከያ ሚንስትር ኦሌክሲ ሬዥኒኮቭ ለአሜሪካዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤን ኤን እንደነገሩት።
ሞስኮ-ሚንስኮችም ይፎክራሉ።የዛቻ፣ቀረርቶ ፉከራዉ ንረት ዓለምን ለምግብ እጥረት አጋልጧል።ዩክሬን በርግጥ እየወደመች ነዉ።ዓመት ከመንፈቋ።ሰሞኑን ደግሞ ኦዴሳ እያጠፋች፣ክሪሚያ እየተቦዳደሰች፣ ሞስኮ እየተሸማቀቀች ነዉ።የዓለም ኃያላን የተዘፈቁበት ጦርነት የሰሞኑ ዉድመት-ጥፋት ቅንጭብ ዕዉነት የዝግታችን ትኩረት ነዉ።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።
የሩሲያ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ቃጠሎ፣ የክሪሚያ ድልድይ ፍንዳታ፣ የሞስኮ ህንፃ መጫጫር ምናልባት የሩሲያዊዉ ጋዜጠኛ መገደል ለኪቮች «የድል ብስራት» ሊሆን ይችላል።የዚያች ትልቅ፤ ዉብ፣ ዘመናይ፣ የባሕር ዳርቻ ከተማቸዉን ዉድመት ያካክሳል ማለት ግን በርግጥ ጅልነት ነዉ።
ኦዴሳ።ትልቅ ናት-ሰፊ።የግሪኮችን ጥንታዊ ሥልጣኔ-ከኦርቶዶክስ ክርስትና ዕምነት፣የጥንታዊ ሥነ-ሕንፃ ቅርስን- ከዘመናይ የወደብ አገልግሎት፣ ሥልታዊ የጦር ሰፈርን-ከባሕር ዳርቻ መዝናኛ ጋር የቀየጠች ዉብ ከተማ ።ባንዳዶች አገላለፅ የባሕር ዳርቻ ዕንቁ።ዓመት ከመንፈቅ በደፈነዉ ጦርነት የዩክሬን እሕል ለዉጪ ገበያና ርዳታ የሚላክባት ወደብ ከመሆንዋ ባለፍ የዉጊያዉ ቀጥተኛ ኢላማ የነበረችበት ጊዜ ጥቂት ወይም ምንም ነበር።
የዩክሬን እሕል ለዉጪ ገበያና ርዳታ እንዲቀርብ አምና የተደረገዉን ስምምነት (የጥቁር ባሕር የእሕል ዉልም ይባላል) ሩሲያ አላርዝም ካለች ካለፈዉ ሳምንት ሰኞ ወዲሕ ግን ያቺ ዉብ ዘመናይ ከተማ የሩሲያ ሚሳዬል ይዘረግፍባት ይዟል።በአብዛኛዉ ከሰዉ አልባ አዉሮፕላን የሚተኮሰዉ ሚሳዬል የኦዴሳን ወታደራዊ ተቋማት፣ ወደቦችዋን፣የመስሪያና የመኖሪያ ቤት ሕንፃዎቿን ተራ በተራ አዉድሞ ትናንት ዕዉቁን የኦርቶዶክስ ካቲድራልን ደረመሰዉ።
በ1794 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የተመሠረተዉ ካቲድራል የዩኔስኮ ጥብቅ ቅርስ፣የከተማይቱ ጌጥ፣ የጉብኚዎች መስሕብ፣አንዲት አማኝ እንዳሉት ደግሞ የነዋሪዎችዋ መፀለያ፣ የልጆቻቸዉ መማሪያም ነበር።
«ልጄ የሚማረዉ እዚሕ ነበር።ሁሌም የምንፀልየዉ እዚሕ ካቲድራል ዉስጥ ነበር።ቄሶቹ ጥሩዎች ናቸዉ።ሰዎች ይሕን መሰሉን ጭካኔ ማቆም አለባቸዉ።»
በጥቃቱ ቢያንስ አንድ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሏልም።ሩሲያ ካቲድራሉን አልመታሁም ባይናት።የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪይ ፔስኮቭ እንደሚሉት ካቲድራሉ የተመታዉ የዩክሬን ጦር የሩሲያን ሚሳዬል ለማክሸፍ በተኮሰዉ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል ነዉ።
«በተደጋጋሚ ገልፀናል።አሁንም መድገም እንችላለን።ጦር ኃይላችን ካቲድራል፣ቤተክርስያን ወይም ሌላ መሰል ተቋማትን ቀርቶ የትኛዉንም ሰላማዊ ተቋማትን አያጠቃም።ለዚሕም ነዉ ወቀሳዉን የማንቀበለዉ። በፍፁም እዉነት አይደለም።ይሕን ካቲድራል ያፈረሰዉ ከዚያዉ የተተኮሰ ፀረ-ሚሳዬል ነዉ።»
የዩክሬንና የምዕራብ ተባባሪዎችዋ ባለስልጣናት ሩሲያን ለማዉገዝ የተተኮሰዉን ሚሳዬል ዓይነት፣ የተኳሹን ማንነትም ሆነ ዓላማዉን መመርመር አላስፈለጋቸዉም።የሩሲያን ማስተባበያም አልተቀበሉትም።የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዘለንስኪ በካቲድራሉ ላይ ብቻ ሳይሆን ኦዴሳን የሚያወድመዉን የሩሲያን ጥቃት «ሽብር» ነዉ ያሉት።
ዘለንስኪ «ሽብር» ያሉትን ጥቃት ለመበቀል በዛቱ በሰዓታት ልዩነት ዉስጥ ዛሬ ማለዳ የዩክሬን ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ክሪሚያ ዉስጥ የሚገኝ የሩሲያ የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤትንና ሞስኮ ዉስጥ ሁለት ሕንፃዎችን ደበደቡ።የሩሲያ ባለስልጣናት እንዳሉት ጦራቸዉ ሞስኮ ላይ ካንዣበቡት ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ሁለቱን መትቶ ጥሏል።ሁለቱ ህንጻዎችም ከመጫጫር ባለፍ የከፋ ጉዳት አልደረሰባቸዉም።ይሁንና ጥቃቱና የመከላከያዉ ተኩስ የአካባቢዉን ነዋሪዎች ለማስደንገጥ በቂ ነበር።
«ሌሊቱን ከመኖሪያችን አጠገብ ኃይለኛ ትርምስ ነበር።እርግጥ ነዉ እኔ ከመኝታዬ አልወረድኩም።ልጄና ባለቤቴ ግን ነቅተዉ ሲጠባበቁ ነበር።ሲነጋ የሆነዉን አወቅነዉ።»
የዩክሬን ጦር የሩሲያ ወራሪዎችን ከሐገሩ ለማስወጣት አፀፋ ጥቃት መጀመሩ በይፋ ከተነገረ ካለፈዉ ሰኔ 5 ወዲሕ የዩክሬን ጦር ባለፈዉ ሁለት ሳምንት የተሻለ ድል ያገኘ መስሏል።የዩክሬን ጦር የሩሲያን ዋና ግዛት በኃይል ሩሲያ በኃይል ከያዘቻት ከክሪሚያ ጋር የሚያገናኘዉን ድልድይ በከፊል አፍርሷል።ድልድዩ በርግጥ ባጭር ጊዜ ተጠግኖ አገልግሎት ጀምሯል።
የዩክሬን ጦር ክሪሚያ የሚገኘዉን የሩሲያ የጦር መሳሪያ ማከማቻ መጋዘንን ሁለቴ አጋይቷል። አንድ የሩሲያ ጋዜጠኛ በዉጊያ መሐል ተገድሏል።ዛሬ ሲነጋጋ ደግሞ የሞስኮ ሕንፃዎችን በሰዉ አልባ አዉሮፕላን መጎነጫጨፍ ችሏል።
ከየካቲት ጀምሮ የኪቭ-ዋሽግተን ብራስልስ የጦር አዋቂዎች የተጨነቁ-የተጠበቡለትን የዉጊያ ስልት፣ከፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዘለንስኪ እስከ ዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ብዙ አዉርተዉለት ነበር።የቀድሞዉ የብሪታንያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሪቻርድ ዳናት ዕቅዱን ከማድነቅ አልፈዉ የዩክሬን አፀፋ ጥቃት የሩሲያን ጦር ከዩክሬን ግዛት ጠራርጎ የሚያስወጣ፣ ፑቲንን ከክሬምሊን ነቅሎ የሚያባርር እስከማለት ተመፃድቀዉበት ነበር።
አፀፋ ጥቃቱ በተጀመረ በስድስተኛ ሳምንቱም ሰሞኑን ፑቲን የሚያዙት ጦር የዩክሬን መንደርና ከተሞችን ያወድማል።ሩሲያ የዩክሬን እሕል ለዓለም ገበያ እንዳይቀርብ ማነቆዋን ሸምቅቃዋለች።ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንና የቤሎሩሲያዉ ወዳጃቸዉ አሌክሳንደር ሉካሼንኮም ክሬምሊን ተቀምጠዉ ድል-ገድላቸዉን ያወራሉ።
« ትናንት አስቸጋሪ ቀን ነበር።እንደ እድል ሆኖ በደሕና አበቃ።ባለን መረጃ መሰረት 15 ሊዮፓርድና ከ20 የሚበልጡ ብራድሌይ (ታንኮች) ተደምስሰዋል።በአንድ ቀን ዉጊያ ብቻ።ይህን ያሕል ሆኖ የሚያዉቅ አይመስለኝ።»
ሉካሼንኮ ያሉትን ፑቲንም አረጋገጡ።
«ሆነ።ምናልባት ባንድ ቀን ያን ያሕል የዉጪ መሳሪያ አዉድመን አናዉቅም።እዚያ የሚዋጋዉ የጦር ክፍል ሙሉ በሙሉ የዉጪ ጦር መሳሪያ የታጠቀ ስለሆነ ይሆናል።»
ሉካሼንኮ የዩናይትድ ስቴትስን መረጃ ጠቅሰዉ እንደተናገሩት የዩክሬን አፀፋ ጥቃት ከተጀመሪ ወዲሕ 26 ሺሕ የዩክሬን ወታደሮች ተገድለዋል።
«በጦርነት ወቅት መጀመሪያ የሚሞተዉ እዉነት ነዉ» ባዩን ነባር ብሒል ተቀብለን ሉካንሼንኮ ወይም ፑቲን ያሉት ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነዉ ብንል እንኳን የዩክሬን አፀፋ ጥቃት በስድስተኛ ሳምንቱም ከግብ አለመድረሱን አለመቀበል ግን ከሉካሼንኮ-ፑቲን ዉሸት በላይ ትልቅ ቅጥፈት ነዉ።
የዩክሬንን ጦር የሚያሰለጥኑ፣ የሚያስታጥቁ፣ ሩሲያን በተደራራቢ ማዕቀብ የቀጡት ምዕራባዉያን መንግስታት ብዙ ያወሩ፣ የለፈፉለት አፀፋ ጥቃት ዉጤት አልባነቱን እያዩ፣የሩሲያ ርምጃ ዓለምን ለምግብ እጥረት ማጋለጡን እያወቁ፣ በሺ የሚቆጠሩ የዩክሬን ዜጎች እየተገደሉ፣ሚሊዮኖች እየተሰደዱ፣ የሐገሪቱ ከተማ መንደሮች ተራ በተራ እየወደሙም የዲፖሎማሲ መፍትሔን እንደአማራጭ ለመቀበል አልፈቀዱም።
ዉጊያዉን በዲፕሎማሲ ለማስቆም ቱርኮች፣ ቻይኖች፣ ብራዚሎች፣ አፍሪቃዉያን በተደጋጋሚ የሞከሩት ሽምግልና በኪቭና ባሳዳሪዎቻቸዉ እንቢተኝነት ዉድቅ ሆኗል።የሞስኮና የኪቭ፣ በኪቭ በኩልም የምዕራባዉያን የመነመነች መግባቢያ የምትመስለዉ የእሕል ሽያጭ ዉሉም ፈርሳለች።
በቱርክና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሸምጋይነት ሩሲያና ዩክሬን አምና ባደረጉት ስምምነት መሠረት ባንድ ዓመት ዉስጥ ከ32 ሚሊዮን ቶን የበለጠ የዩክሬን እሕል ለዓለም ገበያ ቀርቧል።የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) እንዳስታወቀዉ የዩክሬን እሕል ለገበያ በመቅረቡ የዓለም የምግብ ዋጋ በ20 ከመቶ ቀንሶ ነበር።ከእንግዲሕ የእሕል ዋጋ መወደድ-አለመወደዱ ገና አልታወቀም።
ሩሲያ ስምምነቱን ለማፍረሷ የሰጠችዉ ምክንያት ግን ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የሩሲያ እሕልና ማዳበሪያ ለገበያ እንዲቀርብ ምዕራባዉያን መንግስታት በሩሲያ ባንኮች ላይ የጣሉት ማዕቀብ በተለይ ስዊፊት የሚባለዉ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ስልት መከፈት ነበረበት።ሞስኮዎች እንደሚሉት አንድ ዓመት ጠበቁ።የተገባዉ ቃል ገቢር አልሆነም።ስምምነቱን አፈረሱ።
ሩሲያ ስምምነቱን በማፍረሷ የዋሽግተ-ለንደን-ብራስልስ መሪዎች በሞስኮ ላይ ዉንጀላ ዉግዘቱን ሲያዥጎደጉዱት የሩሲያ ጦር ኦዴሳ የሚገኘዉን የዩክሬን እሕል ማከማቻ መጋዘንን፣ጎተራን፣ መጫኛና ማራገፊያ ወደብን በሚያሳዬል ያነደዉ ገባ።ቀጥሏልም።የኪቭ ባለስልጣናት የሩሲያ ቦምብ ሚሳዬል ዩክሬኖችን በገደለ፣ከተማ መንደሮቻቸዉን ባወደመ ቁጥር እንደሚሉት ሁሉ አሁንም ይፎክራሉ ድል የኛ ነዉ እያሉ።መከላከያ ሚንስትር ኦሌክሲ ሬዥኒኮቭ እናሸንፋለን ባይ ናቸዉ።
«የኔቶ የምስራቅ ጋሻ ወይም የአዉሮጳ የምስራቅ ጋሻ ሆነናል።የዩክሬኖች ጠንካራ ተዋጊ እንዳለን አስመስክረናል።ሩሲዎችን እንዴት መመከት፣፣መምታትና ማሸነፍ እንዳለብን ጥሩ ልምድ አለን።»
ሩሲያ ክሪሚያ የተባለችዉን የዩክሬን ስልታዊ ግዛት በ2014 ከግዛትዋ ቀይጣለች።ዶኔትስክ፣ኼርሶን፣ ሉሐንስክ፣ ማይኮላዬቭና ዛፖሪዥዥያ ኦብላስት የሚባሉ ግዛቶችን ተቆጣጠራለች።የኪቭ መሪዎች ይኽ ሁሉ ግዛት በጠላታቸዉ ተይዞ ከ10 ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሎባቸዉ፤ መቶ ሺዎች ቆስለዉ፣ ሚሊዮኖች ተሰደዉም «እናሸንፋለን» ይላሉ።መቼ? ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ