ማሕደረ ዜና፤የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መዉጣት
ሰኞ፣ ጥር 15 2015የኤርትራ ጦር ከትግራይ ትላልቅ ከተሞች ለቅቆ መዉጣቱ በተለያዩ ወገኖች እየተዘገበ ነዉ።የአስመራ፣የአዲስ አበባና የመቀሌ ባለስልጣናት ግን ጦሩ ለቅቆ ስለመዉጣት-አለመዉጣቱ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።አልሰሙ ይሆን? አናዉቅም።የምናዉቀዉ የአዲስ አበባ መሪዎች በሹም ሽር፣ መቀሌዎች በረጅም ግምገማ እየባተሉ መሆናቸዉን ነዉ።ለነገሩ አዲስ አበቦች የኤርትራ ጦር ኢትዮጵያ ዉስጥ እየተዋጋ መሆኑን ያመኑት ያዉም በግድምድሞሽ ዓለም ጉዳዩን ገርድፎ-ሰልቆ ካበቃ ከ4 ወር በኋላ ነበር።አሁንም የኤርትራ ጦር ከትግራይ ከተሞች መዉጣቱን ያረጋገጡት አሜሪካኖች ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አቶኒ ብሊንከን የጦሩን መዉጣት «ለሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነት «ታላቅ እመርታ» በማለት አወድሰዉታል።የእመርታዉ እስከየትነት፣የኤርትራ ሚና እንዴትነት፣ የአዲስ አበባ፣ መቀሌ፣አስመሮች የወደፊት ግንኙነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።
ለንጉሰ ነገስት አፄ ኃይለ ስላሴ የከፋ ጠላትን ለማደከም እንደወዳጅም፣እንደማይጎዳ ጠላትም የሚታይ ወጣት ነበር።ኢሳያስ አፈወርቂ።
ከ1960ዎቹ ጀምሮ የሚዘከረዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ፣ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የሚነገረዉ የኤርትራ የሐገርነት ታሪክም የሱና የሳቸዉ ሚና ካልታከለበት በርግጥ ጎደሎ ነዉ።ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ።ለኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም አኞ ጠላት ናቸዉ።ገንጣይ።ለመለስ ዜናዊ ግን መላዕክም-ሰይጣናም ብጤ ናቸዉ።
የያኔዉ የኢትዮጵያ የሽግግር ፕሬዝደንት በ1986 አስመራ ላይ ለዉጪ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ «ከኢሳያስ ጋር አንድ ሰዓት ማሳለፍ» አሉ፣ «አስር መፅሐፍት ከማንበብ የበለጠ ጠቃሚና አሳዋቂ ነዉ»
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከተጫረ ከ1990 በኋላ ግን ለመለስ፣ መለስ ለሚመሩት ሕወሓት-ኢሕአዴግም የአስመራዉ ቁጡ አንበሳ ለኢትዮጵያ አይደለም ለአፍሪቃ ቀንድ ተቆርጦ መጣል ያለበት «ጋንግሪንግ» ናቸዉ።
ከመለስ እኩል ባይሆንም ለረጅም ጊዜ በቅርብ የሚያዉቋቸዉ የቀድሞዉ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦነግ) መሪ ሌንጮ ለታ በ2010 ሳነጋግራቸዉ ኢሳያስን «ገዢ» አሏቸዉ።
አቶ ኢሳያስ ገዢ ናቸዉ።የትኛዉም ክፍል፣ አንድ ቤት ብቅ ቢሉ በደንብ የሚታዩና የሚሰሙ ሰዉ ናቸዉ።»
በርግጥም ገዢ ናቸዉ።ኤርትራን ነፃ አወጡ።ነፃ ከወጣች በኋላ ሌላ ገዢ አታዉቅም።ለምዕራባዉያን አምባገነን፣ ጨካኝ፣ ለጠላቶቻቸዉ አረመኔ ሊሆኑ ይችላሉ።ጠቅላይ ሚንስር ዐብይ አሕመድ በ2010 እንዳሉት ወይም በዚያዉ ዘመን ሚሊንየም አዳራሽ ተሰብስቦ ለነበረዉ የአዲስ አበባ ነዋሪም ሰዉዬዉ «ወዲ አፎም» ወይም «ኢሱ» እየተባሉ የሚንቆለጳሱ ዉድ መሪ ናቸዉ።
በ1985 አስመራን የጎበኘዉ የኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ቡድን ፕሬዝደንት ኢሳያስ ባማርኛ መግለጫ እንዲሰጡት ጠየቀ።ፕሬዝደንቱ «አማርኛ በደንብ ስለማልችል---ብለዉ ሳይጨርሱ አንድ ረዳታቸዉ አቋረጣቸዉና «የአ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን (ESLCE)ን ባማርኛ C ነዉ ያመጣኸዉ---ትችላለሕ» ቢላቸዉ፤ ሰዉዬዉ ባማርኛ «ለኔ C የሰጠኝ አስተማሪ ራሱ F ነበረዉ» ብለዉ ጋጠኞቹን አሳቁ።
ከ25 ዓመት በኋላ ግን አዲስ አበባ ላይ የትግርኛ ቅላጼ የተቀላቀለበትን አማርኛን ረጋ-ብለዉ ኢትዮጵያዉያንን አወደሱ፣ «ጠላት ያሏቸዉን» ወገኖች አወገዙ፣ አስጠነቀቁ ዛቱበት።ታዳሚዉን ቁጭ ብድግ እያደረጉ አስጮሁትም።
ለጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድም ከተወዳጅ መሪነት በላይ ለአፍሪቃ ቀንድ አርቆ አሳቢ፣ባለትልቅ ርዕይም ናቸዉ።
«ፕሬዝደንት ኢሳያስ ለሁለቱ ሐገራት ዝምድና ለሁለቱ ሐገራት ዝምድና ብቻ ሳይሆን፣ በሱዳን፣ በሶማሊያ፣በጅቡቲ ጠንካራ መንግስታት ተፈጥረዉ፣ ምስራቅ አፍሪቃ በጠንካራ መንግስታት የሚተጋገዙ እንጂ አንደኛዉ መንግስት፣አንደኛዉን መንግስት የሚያፈርስ እንዳይሆን ሰፋፊ ሐሳብ እንዳላቸዉ መረዳት ችያለሁ።»
ጥቅምት 23 ለ24 አጥቢያ፣ 2013።የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስት እና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጠብ ንሮ የሕወሓት ታጣቂዎች ትግራይ ዉስጥ የሰፈረዉን የፌደራል ጦርን መቱ።ጦርነት።የኤርትራ ጦርም ከዉጊያዉ ተመሰገ።የፕሬዝደንት ኢሳያስ ጦራቸዉን ወደ ኢትዮጵያ ያዘመቱበት ምክንያት ብዙዎች እንደሚሉት ብዙ ነዉ።
ከ3 ዓመት በፊት አዲስ አበባ ላይ እርጋታችንና ዕድገታችን ያዉካሉ ያሏቸዉን፣ ወይም በ1990ዎቹ «ጋንግሪግ» ብለዉ ሊቆርጧቸዉ ብዙ የሞከሩትን ኃይላት ለማጥፋት፣ ወይም የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግስት ደጋፊዎች እንደሚሉት ለአፍሪቃ ቀንድ ሰላም አስበዉ ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።
ዉጊያዉ ከመጫሩ ከጥቂት ቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ግን «ጨዋታዉ አበቃ» ማለታቸዉ ተዘግቧል-Game over።ዘንድሮ ባለፈዉ አርብ የኤርትራ ጦርን ያሳፈሩ፣የጭነት መኪኖችና አዉቶቡሶች የሽረ ከተማን ለቅቀዉ ሲወጡ ያየ አንድ የከተማይቱ ነዋሪ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አንደነገረዉ «አንዳዶቹ መኪኖች ላይ «Game over» የሚል መፈክር ተለጥፎባቸዋል።ጨዋታዉ በርግጥ አብቅቶ ይሆን?
በኢትዮጵያ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደርና በጆርጅ ዋሽግተን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰር ዴቪድ ሺን «እኔም እንዳታዉ ተቃራኒ ዘገባ ነዉ-የደረሰኝ» ይላሉ
«ሁሉም የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል ስለመዉጣት አለመዉጣታቸዉ የደረሰኝ ዘገባ ልክ አንተ እንዳልከዉ የሚቃረን ነዉ።ይሁንና ገሚሶቹ መዉጣታቸዉን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ።ሁሉም ስለመዉጣቸዉ ግን ምንም ማረጋገጪያ አላየሁም።እንደሚመስለኝ የኤርትራ ወታደሮች በሙሉ የኢትዮጵያን ግዛት ለቅቀዉ ካልወጡ የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ መሆኑ ያጠራጥራል።»
የኤርትራ ባለስልጣናት ያዉ እንደ ሁሌዉ ዝም-እንዳሉ ነዉ።ጭጭ።ባለፉት ሁለት ዓመታት የኤርትራን ይሁንና የኢትዮጵያ ጦርን እንቅስቃሴ እግር በእግር እየተከታተሉ ከራሳቸዉ ፍላጎት ጋር እየቀየጡ ለዓለም ለማሳጣት የማይቦዝኑት የሕወሓት መሪዎች ዓለምን ላፍታም ቢሆን ረስተዉ፣ በር ዘግተዉ «እየተገማገሙ ነዉ»-አሉ-የሚያዉቁ።
ከትዊተር የማይጠፉት የሕወሓት ትልቅ ሹም ዛሬ እስከ ቀትር የለጠፉት የመጨረሻ መልዕክት ፓርቲያቸዉ ሹም ሽር አለማድረጉን የሚያስተባብል መረጃ ነዉ።የአዲስ አበባ መሪዎች የመጨረሻ የትዊተር መልዕክት ለቻይኖች አዲስ ዓመት የተላለፈ የመልካም ምኞች መግለጫ፣ ወይም ሮዝመሪ የተሰኘዉ የጥብስ ቅጠል ጠቀሜታን የሚያወሳ ነዉ።
ማን ያረጋግጥ።ዩናይትድ ስቴትስ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊከን ባለፈዉ ቅዳሜ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድን በስልክ አነጋግረዋል።የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚኒቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በትዊተር ገፃቸዉ እንደፃፉት ብሊንከን «የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መዉጣት ለሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ቁልፍ ነዉ» ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት አጣሪዎች አካባቢዉን ይጎበኙ ዘንድ እንዲፈቀድላቸዉም ብሊከን ጠይቀዋልም።
በቅርቡ አዲስ አበባን የጎበኙት የጀርመንና የፈረንሳይ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮችም በጦርነቱ መሐል የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲጣሩና ተበዳዮች ፍትሕ እንዲያገኙ ጠይቀዋል።
የኢትርትራ ጦር በሁለት ዓመቱ ጦርነት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰዋል ተብለዉ ከሚወቀሱ ኃይላት አንዱ ነዉ።
የትግራይ ምክር በክልሉ ዉስጥ የደረሰዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያጣራ ልዩ ኮሚሽን ከሰየመ 8 ወር ሆኖታል።የኮሚሽኑ መሪ ረዳት ፕሮፌሰር የማነ ዘርዓይ እንዳሉት ተፋላሚ ኃይላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሱት ግፍ «ዘግናኝ፣ ድርጊቱ ደግሞ እብደት ነዉ።»የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል እየወጡ ነው ተባለ
«ዘግናኝ የሆኑ ነገሮች ተፈፅመዋል።በዚሕ ጊዜ፣ በዚሕ ሁኔታ፣እኔን የሚመስሉ ሰዎች እንዴት ይፈፅሙታል?እንደምታዉቀዉ አንድ አካባቢ ያለ ማሕበረሰብ አካላት ናቸዉ-ግጭት ዉስጥ የገባዉ እና እኔን የሚመስሉ ብቻ ሳይሆን እኔጋ የነበሩ ሰዎች አካል ብለህ የምትወስደዉ ስለሆነ---ትንሽ ከበድ የሚል ነዉና እኔ የምገልፀዉ ያዉ እብደት ነዉ።»
እንደ ትግራይ ሁሉ በጦርነቱ ክፉኛ በተጎዱት በአማራና በአፋር ክልሎች የደረሱ ግፎችን የሚያጣራ ልዩ ኮሚሽን ይሁን ኮሚቴ ስለመሰየሙ በይፋ የተነገረ ነገር የለም።
የቀድሞዉ ዲፕሎማት ዴቪድ ሽን እንደሚያምኑት ግን በጦርነቱ የደረሰዉን ግፍ ለማጣራትም ሆነ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተፋላሚ ኃይላት መካከል መተማመን መዳበር አለበት።በፌደራሉ መንግስትና በሕወሓት መሪዎች መካከል የሚታየዉን መግባባት ፕሮፌሰር ሺን አበረታች ይሉታል።
«እንደታዘብኩት በትግራይ መከላከያ ኃይልና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት (አዛዦች) መካከል በአንጻራዊነት ጥሩ ግንኙነት እየዳበረ ነዉ።ግንኙነቱ ባለፉት ጥቂት ወራት እየተሻሻለ ነዉ።ይሁንና በትግራይ ኃይላትና በኤርትራ ኃይላት መካከል አሁን ከፍተኛ መጠራጠር አለ።ኤርትራዉያኑ ትግራይ ክልል በነበሩበት ወቅት ከፍተኛ ግፍ ተፈፅሟል።መተማመን ለማስፈን ረጅም ጊዜ ይወስዳል።እዉነቱን ለመናገር ፋኖ ወይም የአማራ ሚሊሺያዎች ባሁኑ ጊዜ ምን እያደረጉ እንደሆን ለኔ ግልፅ አይደለም።»
የኢትዮጵያ መንግስትና ሕወሓት የሰላም ዉል መፈራረማቸዉን የኤርትራ መንግስት እስካሁን በይፋ አልተቃወመም፤አልደገፈምም።አንዳድ ዘገቦች እንደጠቆሙት ስምምነቱን የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ብዙ አልፈቀዱትም።የተወሰኑ የአማራ ታጣቂዎችም ስምምነቱ በጦርነቱ የተጎዳዉን የአማራ ሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት የሚያረካ አይደለም ይላሉ።
በዚሕም ምክንያት ፕሬዝደንት ኢሳያስና የአማራ ታጣቂዎች የጋራ ግንባር ለመፍጠር እያሴሩ ነዉ የሚል መላምት በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ፕሮፌሰር ሺን እንደሚሉት ሥለ አሥመራ-አማሮች ትብብር የሚናፈሰዉ ዘገባ እዉነት ከሆነ ለኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስት ባያሰጋ-ማስቸገሩ አይቀርም።
«ለማዕከላዊዉ መንግስት ወደፊት ስጋት ስለመሆን አለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም።ችግር መፍጠሩ ግን ምንም አያጠራጥርም።ማዕከላዊዉ መንግስት ይህን ሁኔታ መቆጣጠር አለበት።ሚሊሻዎቹ በሙሉ የማዕከላዊዉን መንግስት ጥያቄዎችና መርሆች ማክበር እንደሚገባቸዉ ማሳወቅ አለበት።ኤርትራ ከፋኖ ወይም ከአማራ ሚሊሺያ ጋር ሥላላት ግንኙነት አላዉቅም።ይሁንና ኤርትራዎች ፋኖን የሚደግፉ ከሆነ በኤርትራና በትግራይ ኃይላት መካከል መተማመን ለመፍጠር ያለዉን ዕድል በሙሉ የሚያጠፋ ነዉ።ኤርትራ የሰላም ስምምነቱን ገቢር ለማድረግ ተባባሪ እንዳልሆነች የሚያመለትም ነዉ።»
አንዲት ኢትዮጵያዊት ጋዜጠኛ ባለፈዉ ሕዳር እንዳለችዉ ሁለት ዓመት ያስቆጠረዉ ጦርነት ዋና ተጠቃሚ «አምባገነን» ያለቻቸዉ የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸዉ።
የካናዳ ዕዉቅ ዕለታዊ ጋዜጣ The Globe and mail የኢትዮጵያዊቱን ጋዜጠኛ አባባል ባለፈዉ ሳምንት ደገመዉ።ጋዜጣዉ «አምባገነን« ያላቸዉ ኢሳያስ አፈወርቂ «የጦርነቱ ግልፅ አሸናፊ ናቸዉ» ይላል።የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ «ኢሱ» እንደ ጋዜጣዉ ዘገባ «የኢትዮጵያ ንጉስ አንጋሽም» ናቸዉ።እዉነት-ወይስ---?
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ