የነሐሴ 20 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ነሐሴ 20 2016በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማንቸስተር ሲቲ፤ ቸልሲ አርሰናል እና ሊቨርፑል ድል ሲቀናቸው፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ሽንፈት አስተናግዷል ። የጀርመን ቡንደስሊጋ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎችም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተከናውነዋል። ባዬርን ሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጨምሮ ዋነኛ ተፎካካሪዎቹ በመጀመሪያ ግጥሚያቸው አሸንፈዋል። የአትሌቲክስ እና ሌሎች ስፖርታዊ መረጃዎችን አካተናል ።
አትሌቲክስ
ከነገ ማክሰኞ ነሐሴ 21 ቀን እስከ ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን በፔሩ ሊማ በሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ፉክክር የኢትዮጵያ ቡድን ይወዳደራል ። ለውድድሩም የልዑክ ቡድኑ በኢትዮጵያ ስዓት አቆጣጠር እሁድ ጠዋት 2:00 ላይ ፔሩ ሊማ በሰላም መድረሱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዘግቧል ።
አርጀንቲና ቦነስ አይረስ ውስጥ ትናንት በተካሄደው የወንዶች የ21 ኪሎ ሜትር ግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ገርባ ዲባባ አሸናፊ ሆነ ። ከ25,000 በላይ ሰዎች በታደሙበት የግማሽ ማራቶን ዓመታዊ ፉክክር ገርባ አሸናፊ የሆነው ርቀቱን ለ1 ሰዓት ከ26 ሴኮንድ ሮጦ በማጠናቀቀቅ ነው ። ኬንያውያኑ ኮስማስ ሙዋንጊ ቦይ እና ሪቻርድ ያቶር ኪሙንያ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ አግኝተዋል ።
ፕሬሚየር ሊግ
ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕን የተኩት ኔዘርላንዳዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎት አጀማመራቸው የተሳካ ሆኗል ። በሊቨርፑል አዲስ አሰልጣኝነታቸው እስካሁን ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች አሸንፈዋል ። ከኢፕስዊች ጋ ያደረጉትን ቀዳሚውን ግጥሚያም ሆነ የትናንቱን ከብሬንትፎርድ ጋ የተደረገ ጨዋታ ሁለት ለዜሮ አሸንፈዋል። በትናንቱ ግጥሚያ ሉዊስ ዲያዝ እና ሞሐመድ ሳላኅ በድንቅ ሁኔታ ሁለቱን ግቦች አስቆጥረዋል ።
ከማንቸስተር ሲቲ ጋ ባደረገው የመጀመሪያው ግጥሚያ በሜዳው የ2 ለ0 ሽንፈትን ያስተናገደው ቸልሲ ትናንት ዎልቨርሐምፕተንን 6 ለ2 አንኮታኩቷል ። ኖኒ ማዱኬ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትሪክ ሠርቷል ። በርመስ እና ኒውካስል አንድ እኩል ተለያይተዋል። ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች፦ አርሰናል አስቶን ቪላን 2 ለ0 አሸንፏል ። ማንቸስተር ሲቲ ኢፕስዊችን 4 ለ1 ድል አድርጓል ። ኧርሊንግ ኦላንድ ሦስት ግቦችን ከመረብ አሳርፎ ሔትሪክ ሲሠራ፤ ኬቪን ደ ብሩወይነም አንድ አስቆጥሯል ። በመጀመሪያው ግጥሚያ ቸልሲ ላይም ያስቆጠረው ኧርሊንግ ኦላንድ በአራት ግቦች ከወዲሁ ይመራል ። ክሪስታል ፓላስ በሜዳው ተጫውቶ በዌስትሐም የ2 ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል ። ሳውዝሐምፕተን ኖቲንግሀም ፎረስትን 1 ለ0 አሸንፏል ። በመጀመሪያ ጨዋታው ፉልሀምን 1 ለ 0 ማሸነፍ የቻለው ማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት በብራይተን የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል ። ቶትንሀም ኤቨርተንን 4 ለ0 ሸንቶታል ።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ትናንት ባዬርን ሙይንሽን ቮልፍስቡርግን 3 ለ2 አሸንፏል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድም በሜዳው አይንትራኅት ፍራንክፉርትን አስተናግዶ 2 ለ0 ድል አድርጓል። ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች፦ አውግስቡርግ ከቬርደር ብሬመን ሁለት እኩል እንዲሁም ማይንትስ ከዑኒዮን ቤርሊን አንድ እኩል ተለያይተዋል ። ፍራይቡርግ ሽቱትጋርትን 3 ለ1 አሸንፏል ። ሆፈንሀይም ሆልሽታይንን 3 ለ2፤ ኤርቤ ላይፕትሲሽ ቦሁምን 1 ለ0 አሸንፈዋል ። ዐርብ በዘንድሮ የቡንደስሊጋ መክፈቻ ግጥሚያ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በደጋፊዎቹ ፊት በባዬርን ሌቨርሉሰን ሽንፈትን አስተናግዷል ።
የባዬር ሙይንሽኑ አጥቂ ቶማስ ሙይለር ለቡድኑ ለ16 ዓመታት በመሰለፍ ክብረወሰን መስበር ችሏል ። ቶማስ ሙይለር ያም ብቻ አይደለም ፤ ልክ እንደ ሴፕ ማየር ለ709 ጊዜ በመሰለፍም ክብረወሰን መስተካከል ችሏል ።
የሻምፒዮንስ ሊግ
የሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር የደርሶ መልስ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስተያ ይቀጥላሉ ። በነገው ዕለት፦ ጋላታሰራይ ከያንግ ቦይስ፤ ስፓርታ ፕራግ ከማልሞይ፤ ኤር ቢ ላይፕትሲሽ ከዲናሞ ኪዬቭ ይጋጠማሉ ። ከነገ በስተያ በሚኖሩ ጨዋታዎች፦ ቃራባግ ከዲናሞ፤ ሮተር ስቴርን ከቦዶ ግሊምት፤ ስሎቫን ብራቲስላቫ ከሚድትዪላንድ እንዲሁም ስላቪያ ፕራግ ከሎስክ ጋ ይጫወታሉ ።
የሻምፒዮንስ ሊግ ጉዳይ ከተነሳ ለመሆኑ በብዙ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ግንባር ቀደሞቹ ተጨዋቾች እነማን ናቸው?
በአውሮጳ የእግር ኳስ ዘመኑ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፦ ለማንቸስተር ዩናይትድ 59 ጊዜ፤ ለሪያል ማድሪድ 101፤ እንዲሁም ለጁንቱስ ቱሪን 23 ጊዜያት በድምሩ 183 የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ የሚስተካከለው የለም ። ክርስቲያኖ ሮናልዶ ካለፈው ጥር ወር አንስቶ በሣዑዲ ዓረቢያ አል-ናስር ቡድን ተሰልፎ በመጨዋት ላይ ይገኛል ።
ከክርስቲያኖ ሮናልዶ በመቀጠል በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ለበርካታ ጊዜያት በመሰለፍ የስፔን ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረው ኢከር ካሲያስ ይከተላል ። በአሁኑ ወቅት 42 ያመት የሞላው ኢከር ካሲያስ በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ለሪያል ማድሪድ 150፤ ለፖርቶ 27 ጊዜያት በድምሩ 177 ጊዜያት ተሰልፏል ።
አርጀንቲናዊው የኳስ ንጉሥ ሊዮኔል ሜሲ በሦስተኛነት ይከተላል ። ለባርሴሎና 149፤ ለፓሪ ሳንጃርሞ 14 በድምሩ 163 ጊዜያት በአውሮጳ ሻምፒዮንስ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ተሳትፏል። እንደ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሁሉ በሣዑዲ ዓረቢያ የእግር ኳስ ሊግ የአል-ሒላል ቡድን ተሰላፊ ሆኖ ተጫውቷል ። የ36 ዓመቱ አጥቂ በአል-ሒላልየ3 ዓመት ውል እንዲያራዝም የቀረበለትን የ1,5 ቢሊዮን ዩሮ ክፍያ በመተው በአሁኑ ወቅት ለዩናይትድ ስቴትስ ለኢንተር ሚያሚ ተሰልፎ ይጫወታል ። የሳዑዲ ዓረቢያ የቱሪዝም አምባሳደር ሆኖ ግን በማገልገል ላይ ነው ።
ፈረንሳዊው አጥቂ ካሪም ቤንዜማ፦ ለሪያል ማድሪድ 133፤ ለሊዮን 19 በድምሩ 152 ጊዜያት በመሰለፍ ሊዮኔል ሜሲን ይከተላል ። የ36 ዓመቱ አጥቂ በሣዑዲ ዓረቢያ የእግር ኳስ ሊግለአል-ኢቲሀድ ተሰልፎ በመጫወት ላይ ይገኛል ።
በአውሮጳ ሻምፒዮንስ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች በብዛት በመሳተፍ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ስፔናዊው ዣቪ ኼርናንዴዝ ነው ። ዣቪ ለባርሴሎና ቡድኑ ታማኝ ሆኖ 151 ጊዜያት ተሰልፏል ። ያም ብቻ አይደለም ። የ42 ዓመቱ ዣቪ ኼርናንዴዝ የእግር ኳስ ጨዋታ ዘመኑን በፈጀበት ቡድኑ ባርሴሎና በአሁኑ ወቅትም በአሰልጣኝነት በማገልገል ላይ ይገኛል።
ከጀርመን ተጨዋቾች፦ የ34 ዓመቶቹ ቶማስ ሙይለር እና ቶኒ ክሮስ በሻምፒዮንስ ሊግ በብዛት በመሰለፍ ስድስተኛ እና ሰባተኛ ላይ ሰፍረዋል ። በባየርን ሙይንሽን መለያ ብቻ የሚታወቀው ጀርመናዊ አጥቂ ቶማስ ሙይለር አሁንም በሚጫወትበት ባየርን ሙይንሽን ቡድኑ ወክሎ 151 ጊዜያት ተሰልፏል ። ለአንድ ቡድን ብቻ እንዲህ በብዛት በመሰለፍም ቶማስ ሙይለርን የሚስተካከል የለም ። ቶኒ ክሮስ ለባየርን ሙይንሽን 41፤ ከዚያም አሁን ለሚገኝበት ቡድኑ ሪያል ማድሪድ 109 በድምሩ 150 ጊዜያት ተሰልፏል ። በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክም ለ150 ጊዜያት በመሰለፍ ሰባተኛው ሰው ለመሆን በቅቷል ።
የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን በማሰልጠን የመጀመሪያው የውጭ ሀገር አሰልጣኝ የነበሩት ስዊድናዊው ስቬን-ጎራን ኤሪክሰን በ76 ዓመታቸው ዛሬ አረፉ ።
ኢትዮ ለንደን
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1990ዎቹ መጀመርያ ቀካባቢ ጀምሮ በታላቋ ብሪታንያ በለንደን ከተማ በወጣት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተቋቁሞ ለሠላሳ ዓመታት የዘለቀው ኢትዮ ለንደን በመባል የሚታወቀው የእግር ኳስ ቡድን የተመሰረተበትን ሠላሳኛ ዓመትና በዚህ በያዝነው የበጋ ፉትቦል ወይም እግር ኳስ ውድድር ቤልጀም ላይ በተካሄደው ጨዋታ አሸናፊ በመሆኑ ታላቅ የትውወቅያና የሽልማት ስነስርአት እንዲሁም የሰላሳኛ ዓመት በአሉን አክብሯል።
በዚሁ በሰሜናዊ ምእራብ ለንደንቨሚገኘው ፊንችሌ በተባለው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ በተካሄደው ደማቅ ስነስርአት ላይ ኢትዮጵያውያን፤ ትውልደ አኢትዮጵያውያን እና ጥሪ የተደረገላቸው አፍሪቃውያን በበአሉ ላይ ተገኝተዋል።
በዓሉ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከምሽቱ 12 ሰአት ጀምሮ የተለያዪ የሙዚቃ የምግብ የመጠጥ እና እጅግ አዝናኝ የሆኑ ፕሮግራሞች የተካሄዱ ሲሆን አቶ አበበ ቶሎሳ የማኅበሩ ሊቀመንበር ንግግር ከማድረጋቸውም በላይ ለተለያዪ ማኅበሩን ለረዱና በጫወታ ከፍተኛ ግብ ላስመዘገቡ ኮከብ ተጫዋቾች ሽልማትና የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል ።
«ጤናይስጥልኝ እኔ አበበ ቶሎሳ እባላለሁ በእንግሊዝ አገር ወደ 35 አመት ገደማ ሆኖኛል ። የዛሬውን እንግዲህ ኢትዮ ለንደን ጥንታዊ ቡድን በእንግሊዝ አገር ውስጥ ለብዙ ዓመታት የቆየ ቲም በቤልጀም ጌንት ከተማ የተካሄደውን የ 2024 የዋንጫ ባለቤት በመሆኑ ነው እንግዲህ ይህን ፕሮግራም ያዘጋጀነው። »
አቶ አበበ አክለውም ማኅበሩ ለሠላሳ ዓመታት ከመስራችነት ጀምሮ አሁን በሊቀመንበርነት፣ በተጫዋችነት በአሰልጣንነት የመሩ ሲሆን ስለማህበሩ እንቅስቃሴና አሁን ስላለበት ደረጃ እንዲህ ብለዋል ። በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል በዓል (2024)
«አዎ እንግዲህ ኢትዮለንደን ይሄ የመጀመሪያ ዋንጫችን አይደለም ። በአውሮፓ ፉትቦል ፌደሬሽን ዝጅት ላይ ባብዛኛው ዋንጫ የበላ ቡድን ነው ። ከአውሮፓ ካሉ ቡድኖች 6ግዜ የዋንጫ ባለቤትና 9 ጊዜ ለዋንጫ የቀረበ አንድ ቡድን ኢትዮለንደን ብቻና ብቻ ነዉ ። እና ለዚህ ስብስብ ነው በአእንግሊዝ አገር ያሉ እናት ወንድሞች እህቶቶች ልጆቻችንን ጠርተን ዛሬ በታላቅ ክብር ከኢትዮጵያኖች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋራ ያሳለፍነው ። እንግዲህ ይህን ክብረበዓል ዛሬ ከአውሮፓ ከተለያዩ ከተሞች መጥተው ያሳለፉ ወገኖቻችን አሉ ። ይህን አስመልክቶ ነው ይህ ዝግጅታችን እየተካሄደ ያለው።»
ማንተጋፍቶት ስለሺ
መኮንን ሚካኤል