1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ ሆሮጉዱሩው ጥቃት የፓርቲዎች መግለጫ

ሰኞ፣ ነሐሴ 30 2014

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ በዜጎች ላይ የደረሰውን የጅምላ ግድያ ኦፌኮ አወገዘ። ኦፌኮ በመግለጫው መንግሥት ለዜጎች የሚያደርገው ጥበቃ መላላቱ ለታጣቂዎች ጥቃት ሰለባ እያደረጋቸው ነው ብሏል። ኦነግ በበኩሉ በክልሉና በመላው አገሪቱ ለሚስተዋሉ አለመረጋጋቶች መፍትሄው ሁሉን አካታች ብሔራዊ ውይይት ማድረግ ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/4GRUy
Äthiopien Oromo Federalist Congress
ምስል Seyoum Getu/DW

«ዜጎች ለጥቃት ተጋልጠዋል»

 

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው የአቋም መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ቢያንስ የ55 ንጹሐን ዜጎችን ሕይወት ቀጥፎ 15 ሺህዎችን አፈናቅሏል ያለውን ግጭት አውግዟል። የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ በኦሮሚያ በርካታ አከባቢዎች ተስተውሏል ባሉት ግጭት የኅብረተሰቡን ህልውና ተፈታኗል። አቶ ጥሩነህ በማብራሪያቸው «በኦሮሚያ ውስጥ በተለያዩ ዞኖች በተለይም በአራቱም የወለጋ ዞኖች፣ እንዲሁም በቦራና እና ጉጂም ጭምር በህዝቡ ላይ የሚፈጸሙትን አሳዛን ችግሮች ማን እየፈጸመው እንደሆነ እንኳ ለመለየት አዳጋች እየሆነ ነው» ብለዋል።

ለጥፋቶች አንዱ ሌላው ላይ ጣት ይቀሳሰራሉ የሚሉት ኃላፊው የኦፌኮ ጥያቄ ለሚደርሱት ማኅበራዊ ቀውሶች ምክኒያት የሆኑ «ገለለልተኛ» ባሏቸው አካላት እንዲለዩ መጠየቅ ነው ብለዋል። ፓርቲው በመግለጫው «የክልሉን ድንበር ጥሰው የገቡ ፋኖ በተባሉ ፅንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች» ያሏቸውንም በሰሞነኛው የአሙሩ አገምሳ ከተማ ጥቃት ተጠያቂ አድርጓል። «ግድያዉ የተፈፀመው የተቀናጀና የተናበበ የፖለቲካ ሸፍጥ በሚመስል መንገድ ነው» በማለትም ወቅሷል። «በመጀመሪያው በአካባቢው ሰላምን ለማስጠበቅ የተመደቡ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ» ይህን እንዲል ያስገድደኛልም ብሏል ኦፌኮ።

የፓርቲው መግለጫ እንዳብራራው፤ ጥቃቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ «በኦሮሞ ስም ታጥቆ የሚንቀሳቀስ የሚመስል ኃይል» ወደ ከተማዋ በመግባት ህዝቡ እራሱን የሚከላከልበት የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ነጥቆ ወስዷል። ፓርቲው ከኅብረተሰቡና በአከባቢው ካሉ አባላቱና ደጋፊዎቹ አገኘሁ ባለው መረጃ «ቀጥሎም ፋኖ ብሎ እራሱን የሚጠራ ኃይል ከተማዋን በመውረር ግድያ ፈፀመ፣ ንብረት ዘረፈ ህዝቡንም እንዲሰደድ አድርጓል» ብሏል።

ሰሞኑን በአሙሩ ወረዳ ከተከሰተው ድርጊት ጋር የሚመሳሰል ከዚህ በፊትም በምሥራቅ ሸዋ ቦሰት፣ በምዕራብ ሸዋ ዳኖ እና በምሥራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳዎች ተከስቷል ነው ያለው ኦፌኮ ግድያ እና መፈናቀሉን አውግዞ ባወጣው መግለጫ። ኦፌኮ “የፖለቲካ ደባና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ” ያለውን ግድያውን አጥብቆ እንደሚያወግዝ በመግለጽ፤ ለሟች ቤተሰብ መፀናናትን ተመኝቷል። ህዝብን ያለጥበቃ በማስቀመጥ ጉዳት እንዲደርስ የማድረግ ፍላጎት ተደጋግሞ በኦሮሚያ ተስተውሏል ያሉት የኦፌኮ ዋና ጸሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ፓርቲያቸው መንግሥት ለዜጎች ጥበቃ እንዲያደርግ፤ ወንጀሎች ሲፈጸሙም የማውገዝና ለህግም የማቅረብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይጠይቃል ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በፊናው በሳምንቱ መጨረሻ በክልሉና በአገሪቱ ስለሚስተዋሉ ወቅታዊ ሁኔታ ብሎ ባወጣው መግለጫ የአገሪቱ ዜጎች ከባድ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለመሻገር በጋራ እንዲቆሙና ሁሉን አካታች ውይይት በአገሪቱ እንዲደረግ ጠይቋል። ባለፈው ሳምንት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የተፈጸመው ግድያና መፈናቀል ላይ የአሙሩ ወረዳ አስተዳዳሪ፣ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የጸጥታ እና አስተዳደር ኃላፊዎች እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

 ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ