1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለ ታንዛንያው ድርድር የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ተስፋ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 29 2016

በኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸነ) መካከል በታንዛንያ ዳረሰላም ተጀምሯል በተባለው የሰላም ድርድር ተስፋመሰነቃቸውን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በኦሮሚያ ለአምስት ኣመታት በዘለቀው የሰላም እጦት በርካታ ፈተናን ያሳለፉ ነዋሪዎች የሰላሙን ዜና በእጅጉ እንደሚሹትም ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4Ydcr
ኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች
ኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምስል Seyoum Getu/DW

ስለ ታንዛንያው ድርድር የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች አስተያየት

የኦሮሚያው የጸጥታ መደፍረስ ያስከተለው ቀውስ

 

የምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳው አርሶ አደር ነዋሪ ጥንትም ተወልደው ባደጉባት አከባቢያቸው ከቀደምቶቻቸው በወረሱት የግብርና ስራ ቤተሰቦቻቸውን ይመሩበታል፤ ያለምንም መሳቀቅም ከዓመት ዓመት ተስፋና እድገትን ከፊትለፊታቸው ይመለከቱበታል፡፡ ላለፉት ሶስት ዓመታት ግን በአከባቢያቸው አይተው የማያውቁት የመከራ አይነቶች ተፈራረቁባቸው፡፡ አንዴ የብሔር ሌላ ጊዜ ደግሞ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች የሚወልዳቸው ያልተቋረጡ ግጭቶች ለዓመታት ያፈሩትን ንብረት አውድሞ ጥንትም የኖሩባት ቀዬያቸውን ወደ ኦናነት ቀይሮባቸው ከማያውቁት የተፈናቃይነት አስከፊ ህይወት ጋር አስተዋወቃቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሚያ ክልል መንግስትን በትጥቅ የሚፋለመው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸነ) ሁለተኛውና ይበልጥ ተስፋ የተጣለበት የሰላም ድርድር ትናንት በታንዛኒያ ዳሬሰላም ሲጀምሩ እንደ እኚ ያሉ ተፈናቃዮች የተደሰተ የለም፡፡ 
ተፈናቃዩ “እውነት ይሆን?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ደግሞ በሳቅ ቀጠሉ፡፡ የደስታ ሳቅ፡፡ “ይቅርታ አድርግልኝ እንጂ እኔ አሁንም አላመንኩም፡፡” ተፈናቃይ አርሶ አደሩ ቀጠሉ፡፡ ዜናውን ትናንት ምሽት ታማኝ ካሏቸው እንደ ዶቼ ቬለ ካሉ መገናኛ ብዙሃን ብሰሙም ከደስታው ብዛት አሁንም ነገሩን ማመን ተሳነኝ ይላሉ፡፡ ነገሩማ ከሰመረ ፈጣሪ ከህዝባችን ጋር ሊታረቅ ነው ብለው የሰላምና እርቅ መውረድ እንኳን ለአከባቢያቸው ለሰፊውም ለመላው ለአገሪቱ ህዝብ ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን አስረዱ፡፡

ዋና አዛዡ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ፊት ለፊት መገናኘታቸው በኦሮሚያ ክልል ለአምስት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት እልባት ለማበጀት ጥርጊያ እንደሚያበጅ ታምኗል። 
ከመንግስት የተደራዳሪ ቡድን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት እንደሚገናኙ የሚጠበቀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ዋና አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ (ጃል መሮ) ከሚገኙበት ምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ በምስራቅ አፍሪቃ በይነ መንግስታት ኢጋድ የአሜሪካ እና የኖርዌይ መንግስታት አስተባባሪነት በአየር በቅድሚያ ወደ ናይሮቢ መወሰዳቸውን ምንጫችን ገልጸውልናል። ምስል Seyoum Getu/DW

የኪረሙው ገጠር ተፈናቃይአርሶ አደር አስተያየት ሰጪው በነዚህ በቀውስ ጊዜያት ደረሱብን ያሉትን የመከራዎች መፈራረቅ አይረሱም፡፡ “ከመፈናቀል ጀምሮ ከፍተኛ እና የየተለያዩ የችግር አይነቶችን ነው ያሳለፍነው፡፡ አሁን ከእርቅ ውጪ እልባት ሚያስገንስ መፍትሄ ከየት ይመጣል” ሲሉም አስተያየታቸውን ያክላሉ፡፡ ቀድሞም መደማመት ብኖር ህን ሁሉ ደም አፋሳሽ ግጭት ባልተከሰተ በማለትም ግጭቱ ያስከተለውን አስከፊ ቀውስ ያስቀምጣሉ፡፡
ሌላውም አስተያየት ሰጪ ከዚያው ከምእራብ ወለጋ ሃሳባቸውን ቀጠሉ፡፡ አስተያየት ሰጪው እንደማንናውም ነዋሪ ዜጋ ከባለፉት ዓመታቱ አስከፊ የጸጥታ ይዞታ ክፉኛ ተፈትነዋል፡፡ ነዋሪው በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ህይወታቸውን ሚመሩት በከተማ ቢሆንም ከመላው ቤተሰባቸው ተቆራርጠው መቆየታቸውንም ያስረዳሉ፡፡ “እኛ አሁን የተጀመረውን የሰላም ድርድር በተስፋ ነው ጓግተን የምንጠብቀው፡፡ ምክኒያቱም እኛ በሰፊ ችግር ውስጥ ነው ያሳለፍነው፡፡ ሰው ብሞት አንቀብርም፡፡ ገቢያ ወጥተን መሸጥ መለወጥ ለኛ ፈተና ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ እናም ከሰላሙ እኛ እንደ ማህበረሰብ ብዙ እናተርፋለን፡፡ሰላም ከመጣልን እንደ አገርም ደም አይፈስም ኢኮኖሚም አይወድምም” ሲሉ ጉጉታቸውን አስረዱ፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ነዋሪነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ በመዲናዋ በሳቸው ላይ የሚደርስ የጸጥታ ስጋቱ ጫና ባይኖርም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ) ዞን ላለፉት ሶስት ዓመታት ሲባባስ እንጂ ሲቀረፍ የማይስተዋለው የጸጥታ መደፍረስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አቆራርጦአቸዋል፡፡ እናም አሁን ተጀመረ የተባለው የሰላም ስምምነቱ ለሳቸውም ሆነ ለበርካቶች ትልቁ እፎታ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ “እንደ አንድ ግለሰብ በተጀመረው ነገር ስኬታማነት ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡ ፈጣሪም የሚወደው ህን ነው፡፡ ነገሩ በስኬት ከተደመደመ ለሁላችንም ትልቅ ደስታ ነው፡፡ ደስታው ወደ ኋላ እንዳይመለስ በዚያ በድርድር ላይ ያሉም ሰዎች የዚህን ሁሉ ሰው መከራ እንደመከራቸው አይተው በስምምነት እንዲደመድሙ ነው የምንጠብቀው” ብለዋል፡፡

አሁን የተጀመረው የሁለተኛ ዙር የሰላም ትረት ለም ተስፋን አሰነቀ?

በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል አሁን ለሁለተኛ ጊዜ የተጀመረው የሰላም ስምምነት ሂደት የተሻለ ተስፋ እንዳለው አስተያየት ሰጪዎች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ከዚህ ቀደም ሁለቱ አካላት ሰላም ለማስፈን ያልሰመረውን ውይይት በዚያው በታንዛንያ ዛንዚባር ወደብ ካደረጉት የመጀመሪያ ዙር የሰላም ስምምነት ለምን በዚህኛው የተሸለን ተስፋ እንደሰነቁ ሲያስረዱም፤ “ለስምምነት የጃል መሮ ከጫካ ወጥተው ወደ ስምምነት ስፍራው ማምራት በራሱ የሚሰጥ ምልክት አለው፡፡ አሁን ከዚያ ያለ ስምምነት ተመልሶ ወደ ጫካ ይመለሳል ሚል ግምት ለኝም፡፡ ከስምምነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በተሸለ ተቀራርበው ይስማማሉ የሚል ጽኑ እምነት አድሮብኛል አሁን፡፡ ስምምነቱም ውጤት ያመጣል ብዬ ነው የማምነው” ብለዋል፡፡

ከስምምነቱ ማግስት የሚጠበቀው የመረጋጋት ተስፋ


ከስምምነቱ ማግስት ነዋሪዎች ተስፋ ያደረጉትን ሰላም እንደሚያጣጥሙ ያምናሉ፡፡ የኪረሙ ገጠራማ አከባቢ ገበረውም ወደ ናፈቀቻቸው ለምለሚቱ ቀዬያቸው ተመልሰው በለመዱት እርሻ ህይወታቸውን ስለመምራት አሻግረው ያያሉ፡፡ “ወደ ለምለሚቱ ቀዬያችን ከመመለስ ሌላ ምንስ ምኞት ኖረናል” ሲሉም የሰላምን ናፍቆት በአጭር ቃል ቋጭተዋል፡፡
ሌላኛውም አስተያየት ሰጪ አከሉ“ህዝብ በማያውቀው ጉዳይ ከቀዬው መፈናቀሉ ያቆማል፡፡” አሉ፡፡ “አሁን ሽፍታም አለ፡፡ የሰውን ቀዬ ሚያቃጥል ንብረት የሚያወድም የሰውን ህይወት እንዲሁ የሚቀጥፍ ሽፍታ፡፡ ትግል ብሎ የምንቀሳቀስም አለ፡፡ አሁን በስምምነት ሰላም ቢያወርዱ የትኛው ታጋይ የትኛውስ ሽፍታ የሚለውን ለመለየት ይረዳል፡፡ ኑሮ በሙሉም ወደ መደበኛ ቦታው ይመለሳል” ሲሉም የሰላም ድርድሩ ብሳካ ያመጣልናል ስላሉት አስተያየታቸውን አብራርተው ሰጥተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማረጋገጫ ለማግኘት ወደ ሚንስትር ለገሰ ቱሉ እና ሚንስትር ዲኤታ ከበደ ዴሲሳ ስልክ ብንደውልም ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካልንም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ መለስ ዓለም ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ዳግም ንግግር ከተጀመረ መንግስት በይፋ እንሚያስታውቅ ተናግረው ነበር።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር በሁለቱ ቡድኖች መካከል ለቀናት ሲደረግ የነበረ ንግግር «በመግባባት» መጠናቀቁ ነገር ግን ከስምምነት ሳይደረስ መቅረቱ መገለጹ ይታወሳል። ታንዛንያ ውስጥ ተጀምሯል በተባለው የመንግስት እና የኦነሰ የሰላም ንግግርን በተመለከተ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም። ምስል Seyoum Getu/DW

በታንዛንያ ስለተጀመረው ሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር ምን የሚታወቅ ነገር አለ?


የኢትዮጵያ መንግስት «ኦነግ-ሸኔ» በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ (ጃል መሮ) የተገኙበት በፌዴራል መንግስት እና በኦነሰ መካከል ሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር ትናንት በታንዛንያ መጀመሩን ዶይቼ ቬለ ዲፕሎማት ምንጭን ዋቢ አድርጎ መዘገቡ ታወቃል፡፡ በመንግስት እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል ሁለተኛ ዙር ንግግር እንዲጀመር ከሁለት ሳምንት በላይ የፈጄ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ለዶይቸ ቬለ የገለጹት የዜና ምንጭ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካንን በመወከል በጄኔራል ጌታቸው ጉዲና የሚመራ የተደራዳሪ ቡድን እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ዋና አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ (ጃል መሮ) ከምክትላቸው የቡድኑ ደቡብ ኦሮሚያ አዛዥ ገመቹ ረጋሳ ድርድሩ ወደ ሚደረግበት ታንዛንያ ዳሬ ሰላም መድረሳቸውም ተሰምቷል።

 
ከመንግስት የተደራዳሪ ቡድን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት እንደሚገናኙ የሚጠበቀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ዋና አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ (ጃል መሮ) ከሚገኙበት ምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ በምስራቅ አፍሪቃ በይነ መንግስታት ኢጋድ የአሜሪካ እና የኖርዌይ መንግስታት አስተባባሪነት በአየር በቅድሚያ ወደ ናይሮቢ መወሰዳቸውን የገለጹልን ምንጫችን ዋና አዛዡ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ፊት ለፊት መገናኘታቸው በኦሮሚያ ክልል ለአምስት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት እልባት ለማበጀት ጥርጊያ እንደሚያበጅ ታምኗል። 


ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር በሁለቱ ቡድኖች መካከል ለቀናት ሲደረግ የነበረ ንግግር «በመግባባት» መጠናቀቁ ነገር ግን ከስምምነት ሳይደረስ መቅረቱ መገለጹ ይታወሳል። ታንዛንያ ውስጥ ተጀምሯል በተባለው የመንግስት እና የኦነሰ የሰላም ንግግርን በተመለከተ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም። በጉዳዩ ላይ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማረጋገጫ ለማግኘት ወደ ሚንስትር ለገሰ ቱሉ እና ሚንስትር ዲኤታ ከበደ ዴሲሳ ስልክ ብንደውልም ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካልንም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ መለስ ዓለም ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ዳግም ንግግር ከተጀመረ መንግስት በይፋ እንሚያስታውቅ ተናግረው ነበር።
ስዩም ጌቱ 
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ