ስልጢ ዞንን ያጠለቀለቀ ጎርፍ 6000 ሰዉ አፈናቃለ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 23 2016የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጢ ዞንን ያጠለቀለቀ ጎርፍ ከ6ሺህ በላይ ነዋሪዎችን አፈናቀለ ፡፡ ከ900 በላይ የመኖሪያ ቤቶችም በዉኃ ተዉጠዋል።ተፈናቃዮቹ በጊዜያዊነት በየትምህርት ቤቶች እንዲጠለሉ መደረጉን የጠቀሱት የአካባቢው ባለሥልጣናት ለሕዝቡ የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ እየተሰጠ መሆኑን አስታዉቀዋል።ሸዋንግዛው ወጋየሁ ከሐዋሳ ዝርዝር ዘገባ አለው
ሺህዎችን ያፈናቀለው የጎርፍ አደጋ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጢ ዞን ጎርፍ ከ6ሺህ በላይ ነዋሪዎችን አፈናቅሏል ፡፡ የጎርፍ አደጋው ነዋሪዎቹን ያፈናቀለው በዞኑ የሥልጢ እና ምሥራቅ ሥልጢ ወረዳዎች ውስጥ ነው ፡፡ ከባለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ በአካባቢው እየጣለ የሚገኘውን ዝናብ ተከትሎ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ አሁን ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ማፈናቀሉ ነው የተነገረው ፡፡
ጎርፉ በወረዳዎቹ በሚገኙ ስድስት ቀበሌያት የመኖሪያ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ መዋጡንና በማሳ ላይ የነበረ ሰብልንም ማውደሙን በሥልጢ ወረዳ የጎፍላላ ቀበሌ ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡ በተለይም ጎፍላላ ቀበሌ አሁን ላይ በውሃ ውስጥ እንደሚገኝ የጠቀሱት ነዋሪዎቹ “ በቀበሌው በመንደር አራት እና አምስት ነዋሪው በሙሉ ነው የተፈናቀለው ፡፡ ሰው መንደሩን ለቆ ወጥቷል ፡፡ አሹቴ በሚባለው አጎራባች ቀበሌም በተመሳሳይ ሁኔታ በውሃ ተጥለቅልቋል “ ብለዋል ፡፡
ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠለያ
የሥልጢ ወረዳ መስተዳድር እንደሚለው ጎርፉ በመኖሪያ ቤቶች ፣ በእርሻ በማሳ እና በንብረት ላይ ካደረሰው ውድመት ባለፈ እስከአሁን በሰው ህይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም ፡፡ “ በእኛ ወረዳ ብቻ 3 ሺህ 700 ሰዎች በጎርፉ ምክንያት ተፈናቅለዋል “ ያሉት የስልጢ ወረዳ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሸይቾ አጢሶ “ አሁን ላይ 864 የመኖሪያ ቤቶች በውሃ ተውጠው ይገኛሉ ፡፡ ከ800 በላይ በሆነ ሄክታር ላይ ተዘርቶ የነበሩ የጤፍ ፣ የበቆሎና ሌሎች የሰብል አይነቶች ወድመዋል ፡፡በአሁኑወቅት ከቀበሌያቱ ለቀው የወጡ ነዋሪዎች በትምህርት ቤቶችና በገበሬዎች ማሠልጠኛ ማዕከላት በጊዜያዊነት እንዲጠለሉ ተደርጓል “ ብለዋል ፡፡
የሰብአዊ ድጋፍ እና ዘላቂ መፍትሄ
ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሥልጢ ዞን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ወሲላ አሰፋ በሁለቱም ወረዳዎች በአደጋው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች አስቸኳይ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል ፡፡ የጎርፍ አደጋው መንሥኤ በአካባቢው ከተገነባ የመስኖ ግድብ ጋር በተያያዘ ተፋሰሱ አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ወረዳዎቹ በመግባቱ መሆኑን የጠቀሱት የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ሃላፊዋ አሁን ላይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ለሚለው ጥናት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል ፡፡
በኢትዮጵያ ባለፍው ሐምሌ እና በተያዘው የነሐሴ ወራት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በሚጥልባቸው የደቡብ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ የኦሮሚያ ፣ የሲዳማ እና የአማራ ክልሎች የጎርፍና መሬት መንሸራተት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲሮዎሎጂ ተቋም ቀደምሲል አስታውቆ ነበር ፡፡ በእነኝህ አካባቢዎች እስከ መጪው መስከረም ወር ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተቋሙ ማሳሰቡ ይታወቃል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ