1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች አያያዝ በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 16 2016

ከሦስት ዓመታት በላይ የተቋረጠው የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ምዝገባ በአፋጣኝ እንዲጀመር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ ። ኮሚሽኑ በ4 ክልሎች በሚገኙ 17 የስደተኞች መጠለያ እና መቀበያ ጣቢያዎች ተጠልለው የሚገኙ እና በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የከተማ ስደተኞችን አካቶ የሁለት ዓመታት የዘርፍ ዘገባ ጥናት ይፋ አድርጓል ።

https://p.dw.com/p/4aaGi
የኢትጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አርማ
የኢትጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አርማምስል Ethiopian Human Rights Commission

ኢትዮጵያ ውስጥ የስደተኞችና የጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳዮች አሳሳቢነት

ከሦስት ዓመታት በላይ የተቋረጠው የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ምዝገባ በአፋጣኝ እንዲጀመር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ ። ኮሚሽኑ በአራት ክልሎች በሚገኙ 17 የስደተኞች መጠለያ እና መቀበያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ  እና በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የከተማ ውስጥ ስደተኞችን አካቶ ባወጣው የሁለት ዓመታት የዘርፍ ዘገባ የስደተኞችን ምዝገባ፣ የፀጥታ እና ደኅንነት ሁኔታ፣ ፍትሕ የማግኘትና የመንቀሳቀስ መብት የተመለከቱ ጉዳዮችን ዳስሷል ። በምርመራ ውጤቱ ከስደተኞች ምዝገባ እንዲሁም ሰነድ የማግኘት መብት ጋር ተያይዞ በሚታዩ ችግሮች ምክንያት ስደተኞች ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች ይጋለጣሉ ተብሏል ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከሦስት ዓመታት በላይ ተቋርጦ የቆየው የስደተኞች ምዝገባ በአፋጣኝ እንዲቀጥል፣መታወቂያዎቻቸው እንዲታደስላቸው፣ በየ መጠለያ ጣቢያዎች ያለው የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታ እንዲስትካከል እና የጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኞች የመንቀሳቀስ መብቶች እንዲከበሩ ጠይቋል።

ከ 200 በላይ ኤርትራዊያን ስደተኞች ተገደው ወደመጡበት ተመልሰዋል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ ያደረገው የመጀመርያው የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ  የዘርፍ ዘገባ የከተማ ውስጥ ነዋሪ ስደተኞችን ጨምሮ ከ 650 ሺህ በላይ ስደተኞችን ያስጠለሉ ስፍራዎችን የዳሰሰ ነው ተብሏል። ኮሚሽኑ ዋና ችግር አድርጎ ከለያቸው ጉዳዮች ሰነድ የማግኘት መብት እና የምዝገባ መቋረጥ ይገኙበታል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ ስደተኞች በተለይ ኤርትራዊያን ባለፉት ሦስት ዓመታት ምዝገባ ማድረግ አለመቻላቸውን የጠቀሰው ኢሰመኮ በዚህ ምክንያት የከተማ ውስጥ ስደተኞች ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን፣ ወደ ሌሎች ሦስተኛ ሀገራት መተላልፍ አለመቻላቸው፣ ሰነድ የላችሁም በሚል ለእሥር መዳረጋቸውን እና ከ 200 በላይ ኤርትራዊያን ተገደው ወደመጡበት ሀገር እንዲመለሱ መደረጉ ተጠቅሷል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ ስደተኞች ባለፉት ሦስት ዓመታት ምዝገባ ማድረግ አለመቻሉ ተገልጿል
በአዲስ አበባ የሚገኙ ስደተኞች በተለይ ኤርትራዊያን ባለፉት ሦስት ዓመታት ምዝገባ ማድረግ አለመቻሉ ተገልጿልምስል Solomon Muchie/DW

ሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮች

በኮሚሽኑ ከተለዩት ሌሎች አሳሳቢ የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳዮች ውስጥ ፀጥታ እና ደኅንነት ሁኔታዎች ይገኙበታል። ስደተኞች ከተቀባይ ማኅበረስብ ጋር በሚከሰቱ ግጭቶች ለጉዳት መጋልጣቸው ፣ የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው መሆናቸው፣ በጦርነት ምክንያት ለሰብአዊ መብት ተጋላጭ መሆናቸው ተጠቅሷል።

አብዛኛዎቹ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ከከተማ ርቀው የሚገኙ መሆናቸውን የገለፀው ኢሰመኮ "በሁሉም የመጠለያ ጣቢያዎች ተዘዋዋሪ ችሎት ባለመኖሩ ጉዳያቸው በሕግ ወደተቋቋመ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንደሚቸገሩ" መገንዘቡን ባወጣው ባለ 47 ገጽ የምርመራ ዘገባ ዐስታውቋል።

የኮሚሽኑ ምክረ ሐሳቦች

ኢሰመኮ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠለሉ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰነድ የማግኘት መብታቸው እንዲከበር፣ የተቋረጠው የምዝገባና የልየታ ሥራ እንዲቀጥል፣ ስደተኞች የሚኖሩበት አካባቢ ፀጥታ እና ደኅንነት እንዲሻሻል መጠለያዎቹ "የሲቪል ባሕርይ እንዲኖራቸው" ተገቢ ያለው ርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል።

ኮሚሽኑ አክሎ በስደተኛ ሴቶች ላይ ይደርሳል ያለው ጾታዊ ጥቃት እንዲቆም ትምህርት እንዲሰጥ፣ "በስደተኞች ላይ የሚደርስ እገታ" እንዲቆም ፣ የስደተኞች የምግብ ድጋፍ ፣ የምድኃኒትና የሕክምና አገልግሎት አቅርቦትም እንዲሻሻል ተጠይቋል። ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ መንግሥት ስደተኞች በሥራ ላይ መሰማራት የሚያስችላቸውን ገንዘም በሰፊው እንዲያሰባስብ፣ ስደተኞች በእርሻ ሥራ እንዲሰማሩ ግብዓት እንዲመቻችላቸው ጥሪ ቀርቧል።

የስደተኞ መጠለያ በዋግኅምራ
የስደተኞ መጠለያ በዋግኅምራ ፎቶ ከማኅደርምስል Waghemira communication

የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢነት

ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች "የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱ" በእጅጉ እንዳሳሰበው እና "በስደተኞች ካምፖች ውስጥ የከፋ ሰብዓዊ ሁኔታ እና የምግብ አቅርቦት እጥረት እየጨመረ መምጣቱን" በቅርቡ ባወጣው መግለጫ አመልክቶ ነበር።

በጋምቤላ ክልል ውስጥ ከ30 ያላነሱ ስደተኞች በረሃብና በምግብ እጦት ፣ ጦርነት ሸሽተው በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ሱዳናዊያን ስደተኞች መካከል ደግሞ 9 ያህሉ በኮሌራ ወረርሽኝ መሞታቸውም የተዘገበው በቅርቡ ነው።

በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተምላሾች አገልግሎት የኮሙኒኬሽንና ውጫዊ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ በአካል ንጉሴ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ስደተኞች መኖራቸውንና ከነዚህም ውስጥ 80 ሺህ ያህሉ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚገኙ በቅርቡ ለዶቼ ቬለ (DW) ገልፀው ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ